በዚምባብዌ 55 ዝሆኖች በረሃብ ምክንያት ሞቱ

በዝምቧብዌ ሁዋንጌ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝ ዝሆን Image copyright Getty Images

በዚምባብዌ ቢያንስ 55 ዝሆኖች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው ተሰማ። ዝሆኖቹ የሞቱት መጠለያቸው በነበረው ሁዋንጌ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት የተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ለሞታቸው ምክንያት ነው ተብሏል።

" ያለው ሁኔታ የከፋ ነው" ያሉት የፓርኩ ቃል አቀባይ ቲናሼ ፋራዎ "ዝሆኖቹ በጠኔ ምክንያት እየሞቱ ነው፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው" ብለዋል።

በዚምባብዌ የተከሰተው ረሃብ የሰብል ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

"ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው" አርቲስት ታማኝ በየነ

የዛሬዋን አዲስ አበባ በፎቶ መሰነድ ለምን አስፈለገ?

"ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች እባካችሁ ውሃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ" ጠ/ሚ ዐብይ

በዚምባብዌ ከጠቅላላው የሀገሪቱ ዜጎች አንድ ሶስተኛው ከፍተኛ የምግብ እህል ርዳታ ድጋፍ የሚሻ ሲሆን፣ ሀገሪቱም በከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

በነሐሴ ወር 2 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ረሃብ እንደተጋለጡና የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ገልጾ ነበር።

አንዳንዶቹ ዝሆኖች ሞተው የተገኙት ከውሃ ኩሬ 50 ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን፣ ረዥም ርቀት ውሃ ፍለጋ መጥተው ከመድረሳቸው በፊት መሞታቸው ተገምቷል።

በዚምባብዌ ትልቅ የሆነው ሁዋንጌ ፓርክ ያለበት ችግር የዝናብ እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች በአንድ ስፍራ መገኘታቸው ጭምር ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ዝሆኖቹ በፓርኩ ያለው ምግብ ስለማይበቃቸው በአቅራቢያው ወዳለ መንደር በመሄድ ሰብል ያወድማሉ።

ቃል አቀባዩ ፋራዎ እንደሚሉት ከሆነ ዝሆኖቹ በአካባቢው ሰብል ላይ" ከፍተኛ ውድመት" አድርሰው ነበር።

ፓርኩ 15 ሺህ ዝሆኖችን ብቻ የመያዝ አቅም ቢኖረውም በአሁኑ ሰዓት በውስጡ 50 ሺህ ዝሆኖች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ ዓመት ብቻ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰብሉን ያወደሙ 22 ዝሆኖችን መግደሉ ታውቋል።

ፓርኩ የመንግሥት ድጎማ የማይደረግለት ሲሆን የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ቢሞክርም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ