በሶሪያና ቱርክ ድንበር የተወሰነ የአሜሪካ ጦር እንዲቆይ ተወሰነ

በሰሜን ሶሪያ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር Image copyright AFP

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶሪያና ቱርክ ድንበር አቅራቢያ እንዲወጡ ታዝዘው ከነበሩ ወታደሮች መካከል የተወሰኑት እንዲቆዩ መወሰናቸውን ተናገሩ።

የተወሰኑት የነዳጅ ያለባቸውን አካባቢዎች ሲጠብቁ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በእስራኤልና ጆርዳን ድንበር አቅራቢያ ይቆያሉ ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ጦር ከድንበር አካባቢ እንዲወጣ መወሰናቸውን ተከትሎ ከደጋፊዎቻቸው ሳይቀር ትችት ቀርቦባቸው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መፅሐፍ ምን ይዟል?

አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች በወጣቶች መስተጓጎላቸው ተነገሯል

"ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው" አርቲስት ታማኝ በየነ

የአሜሪካ ጦር ለመውጣት መወሰኑን ተከትሎ ቱርክ በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ኩርዶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍታለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ምንም እንኳ አይ ኤስን በመዋጋት ረገድ ትልቅ አጋር የነበሩትን ኩርዶች ከድተዋቸዋል በሚል ቢተቹም ውሳኔያቸው ትክክል መሆኑን ሲገልፁ ቆይተዋል።

"ስለምን ጦራችንን በሁለት ግዙፍ ተቀናቃኞች መካከል፣ በማንኛወም ወቅት ጦርነት ሊገጥሙ በሚችሉ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል እንተዋለን? አይመስለኝም" ካሉ በኋላ " የተመረጥኩት ጦራችንን ወደ ሀገሩ ለመመለስ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን ትራምፕ አክለው እስራኤልና ጆርዳን የተወሰኑ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች "በሌላ የሶሪያ ድንበር አቅራቢያ" እንዲሰፍሩ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ሌላ ክፍል የአሜሪካ ጦር "ነዳጅ የሚገኝበትን አካባቢ አንዲጠብቅ" መፈለጉን ነው የተናገሩት።

ቱርክ ሶሪያ ድንበር ላይ የሚገኙ ኩርዶች ላይ ጥቃት የከፈተችው "ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠና" ለመፍጠርና ሁለት ሚሊየን ያህል ስደተኞችን ለማስፈር ነው ስትል ትከራከራለች።

በቱርክና ሶሪያ ድንበር ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ 300ሺህ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው መሰደዳቸው ታውቋል።

ቱርክ የተወሰኑ በኩርዶች የሚመራ ጦር ስፍራውን ለቅቆ እንዲወጣ ለማስቻል የተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማማች ቢሆንም ስምምነቱ ግን ዛሬ ያበቃል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁሙ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ያሉት ነገር የለም።

የቀድሞ የአሜሪካ መከላከያ ባለስልጣናት ኤን ቢ ሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው እንደተናገሩት የመከላከያ መስሪያ ቤቱ የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ጠቅልሎ የሚወጣበትን እቅድ እየተነጋገረበት እንደሆነ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሶሪያ የአሜሪካ ጦር እንዲወጣ በመወሰናቸው ከፍተኛ ትችት አስተናግደዋል።

ትችቱ የምክር ቤት አባላት ከሆኑ ሪፐብሊካን ጭምር የቀረበ ሲሆን " ትልቅ ስህተት" ሲሉ ቅሬታቸውን የገለፁም ነበሩ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ