በዋግ ኽምራ ከ126ሺ ሰዎች በላይ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለፀ

የዋግ ኽምራ ካርታ Image copyright Googlemap

በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በተከሰተው ድርቅ 126ሺ ዘጠና ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ዝቅተኛ ዝናብ ምክንያት ድርቅ በመከሰቱ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ምንም ዓይነት ዝናብ ያልጣለ ሲሆን፣ ክረምት ዘግይቶ የገባባቸው እንዲሁም የመጠን እና የሥርጭት ጉድለት የታየባቸው አካባቢዎች ለድርቅ እንደተጋለጡ ያስረዳሉ።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ከየት ወደ የት?

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

ምንም እንኳን የዝናብ እጥረቱ የዋግ ኽምራ አብዛኛው ወረዳዎች ላይ ቢከሰትም በተለየ ሁኔታ ግን ሰሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ እንዲሁም ከፊል ሰቆጣ ዙሪያ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በዞኑ ከሚገኙ ስድስት መቶ ሺ ነዋሪዎች መካከል 126 ሺ ዘጠና የሚሆን ሰው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል።

የሰብል ግምገማ እየተደረገ መሆኑን የሚገልፁት አቶ መልካሙ ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ለማወቅ የሚያስችል ቢሆንም ምንም አይነት ዝናብ ያልጣለባቸው አካባቢዎች ግን የከፋ ችግር ከማጋጠሙ በፊት ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

"ዝናብ ባለመጣሉ ችግር የገጠማቸው ወረዳዎች የሰብል ግምገማ ተደርጎ ምላሽ ይሰጣል ከማለት ቀድሞ ለነዚህ ሰዎች መድረስ አለብን፤ አሁን ባለው ሁኔታ 126ሺህ ሰዎች በአፋጣኝ ልንደርስላቸው ይገባል" የሚሉት አቶ መልካሙ በማኅበረሰቡ መካከል ያለው የመረዳዳት እና ያለውን የመካፈል ባህል እስካሁን ቢያቆየውም መንግሥት በአፋጣኝ ካልደረሰ ችግሩ እንደሚከፋ ይገልጻሉ።

"ድርቅ ረሀብ መሆን አይገባውም" ሲሉም ድርቁ አሁን ካለበት ደረጃ የከፋ ሆኖ ወደ ረሀብ ሳይሸጋገር በፊት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ይናገራሉ።

ወመዘክር፡ ከንጉሡ ዘመን እስከዛሬ

ኮሎኔል መንግሥቱን ትግል ለመግጠም ቤተ መንግሥት የሄደው ደራሲ

ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ለክልል እና ለፌደራል መንግሥት ያሳወቁት ከሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ እንደሆነም ያስረዳሉ።

መረጃ በወቅቱ ለማጥራት ባለመቻላቸው ሂደቱ ቢዘገይም ክልሉ ጉዳዩን ለፌደራል መንግሥት አሳውቋል ይላሉ። ከዛ በኋላ የጨረታ፣ የሎጂስቲክ ችግር ገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም አሁን የከፋ ችግር ውስጥ ያሉት ተለይተው እርዳታ ማጓጓዝ ሥራው ተጀምሯል ይላሉ።

126ሺህ ለሚሆኑት ሰዎች ከፌደራል የተደረገው እርዳታ ከመንግሥት መጠባበቂያ የተገኘ ሲሆን፤ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ እርዳታ ጎን ለጎን እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ወደ አካባቢው ገብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ (የፊታችን እሮብ ጥቅምት 12 ድረስ) ወደማከፋፈል እንደሚሄዱም ተናግረዋል።

"አሁን የገጠመን ችግር የመንገድ ነው። እሱን ኀብረተሰቡን በማሰማራት መሠራት ያለበት ሥራ መሠራት አለበት። በዚህ ወር ውስጥ መድረስ ካልተቻለ የሰው ሕይወት ሊያልፍ ይችላል ብለን እንፈራለን" ይላሉ።

እስካሁን የሞተ ሰው እንደሌለ አቶ መልካሙ ገልፀው ነገር ግን አፋጣኝ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ በቀጣይ ዐሥር ቀናት መድረስ ባለበት ቦታ ሁሉ መድረስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ጥናት ፍላጎት ጨምሯል

በዝቋላ ወረዳ በ01 ቀበሌ ነዋሪና የአራት ልጆች አባት አቶ በርሄ እያሱ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከተጎዱ አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው።

"ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። ድሮ ዋግ ህምራ ወይም በዝቋላ ወረዳ ችግር ሲከሰት ወደ በለሳ፣ ደንቢያ ወይም ወደ ሱዳንም ይኬድ ነበር። አሁን ግን የተረጋጋ ስላልሆነ አልተቻለም" ይላሉ።

በቀበሌያቸው የክረምት ዝናብ ያገኙት ሐምሌ 29፣ 2011 ዓ.ም መሆኑን ገልፀው ከዚያ በኋላ ግን ዝናብ የሚባል ነገር በቀበሌው እንደሌለና ድርቁ ሰዎችንም ብቻ ሳይሆን እንስሳትን እያጠቃ መሆኑንም አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ።

"ኑሮ በጣም ከብዷል። የቀን ስራ እንዳንሰራም የምንሰራው ነገር ግራ አጋብቶናል። በግልም ያው ዕቃ የሚያሸክምም የለም። ያው ከእግዚአብሔር በታች ያለው መንግሥት ነው፤ የሚያደርገንን ለማየት በጉጉት እየጠበቅን ነው" ይላሉ።

ከእርሻቸው ውጭ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ በርሄ " ከተለያዩ ከተሞች ነጋዴ የሚያመጣው ቀይ ማሽላ አለ። ያው እሱን 15፣ 20 ኪሎ በብድር ሸምተን ነው የምንበላው፤ ያው የሰው ሕይወት በረሀብ ማለቅ ስለሌለበት" ይላሉ።

የእሳቸው ቀበሌ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ቀበሌዎችም በድርቁ እንደተጠቁና በአካባቢውም ስር የሰደደ ድህነት እንዳለ ይናገራሉ።

ችግሩ የከፋ ከመሆኑ አንፃር ለመንግሥት ማሳወቃቸውን የሚገልፁት አቶ በርሄ "ዞሮ ዞሮ ተረጋጉ ሰው ወደ ስደት እንዳይሄድ አረጋጉት የሚል ነው ምላሽ የተሰጠን፤ ስደትስ ቢሆን የት ይሄዳል? አሁን ግን የተረጋጋ ሁኔታ ስለሌለ ወደየት እንሄዳለን?" ይላሉ።

ሌላው በዝቋላ ወረዳ የሚኖሩት የሰባት ልጆች አባት የሆኑት የ40 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ አደሩ ወልዴም አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚሹ ይናገራሉ። ያጋጠማቸውንም ድርቅ በኢትዮጵያ ለብዙ ሰዎች እልቂት ካደረሰው ከ1977 ረኃብ ያላነሰ ድርቅ ነው ይላሉ።

"ህዝቡ በጣም ተቸግሮ ነው ያለው፤ እንሰሳትም እየሞቱብን ነው ያሉት። አሰቃቂ ሁኔታ ነው የገጠመን " በማለት አክለውም "ሳለ እግዚአብሔር የሞተ ሰው የለም፤ በቀጣይም እርዳታ ካልተደረገ የሰው ህይወት ሊጠፋ ይችላል" በማለት ይናገራሉ።

አደጋ የተጋረጠበት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት

ኢትዮጵያውያን ዛሬም ከአለት አብያተ-ክርስትያናትን ያንፃሉ

ከፌደራል መንግሥት ተወክለው የመጡ ሰዎችም በአካባቢው ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ። ከሰሞኑ እንዲሁም የቀበሌ አስተዳዳሪዎች ሲያወያዩዋቸው የነበረ መሆኑን ጠቅሰው "ሕዝቡ በአጠቃላይ የሚበላው የለም። ምን እናድርግ? ምን እንብላ" ብለው እንደጠየቁና ከአደጋና መከላከልና ምግብ ዋስትና መልስ ጠብቁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ወረዳው ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች የብር እርዳታ ቢያደርግላቸውም "ለሌላው ለተቸገረው ህዝብ ምንም አይነት እርዳታ አልደረሰውም" ይላሉ።

በቀድሞው ጊዜ እንዲህ አይነት ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት አርሶ አደሩ ወደሌላ አካባቢዎች ተሰዶ አጠራቅሞ የሚያመጣበት ሁኔታ ነበር አሁን ያ ሁኔታ በመቆሙ ለተደራረበ ችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

"ቀድሞ ወደ ጎንደር፣ መተማ ይሰድድ ነበር። ባለው አለመረጋጋት ሁኔታ መሰደድ አልቻልንም። አርሶ አደሩ መሔጃ አጥቶ በጣም ተቸግሮ ነው ያለው" ይላሉ

የቀን ስራ በመፈለግም የዕለት ጉርስ ለማግኘትም እየታገሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

አቶ መልካሙም በአርሶ አደሮቹ ሃሳብ ይስማማሉ "ከዚህ በኋላ ወር ወይም ሁለት ከዘገየ የከፋ ችግር ሊመጣ ይችላል" ይላሉ።

በቅዳሜው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ምግባሩ ከበደ አረፉ

አቶ ታደሰ ካሳ፡ "…ወሎዬ ነኝ፤ መታወቂያዬም አማራ የሚል ነው"

እንስሳትን በተመለከተ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መኖ በማቅረብና መስኖ ተከትሎ በመዝራት ለእንስሳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ያክላሉ።

እንስሳት ወደ አጎራባች ቀበሌና ወረዳ እንዲሄዱ ቢደረግም ሌላ ቦታም እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ስጋት አላቸው።

አሁን እየተደረገ ያለው የሰብል ግምገማ ውጤት ከ10 ቀን በኋላ እንደሚታወቅና ይፋ እንደሚደረግም ይገልጻሉ።

ከድርቁ ጋር በተያያዘ በሰዎች እና በእንስሳት ላይም በሽታ ሊከሰት ስለሚችል አስቀድሞ መከላከል አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል። ለእንስሳት መኖ ከመሰጠቱ በፊት ክትባት እንሚሰጣቸውም ይናገራሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዝናብ እጥረት ምክንያት በዞኑ አስቸኳይ ድጋፍ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እታገኘሁ አደመ እንደተናገሩት ድጋፍ የሚያስፈልገውን ህዝብ ችግር መንግሥት ሊፈታው የሚችል ነው ብለዋል።

ችግሩን መጠን ለማጥናት የተለያዩ ባለሙያዎች ወደ አካባቢው በማቅናት ጥናት ማድረጉን አስታውቀዋል።

በዚህ መሠረትም "የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለሚኖሩ የየዕለት ቀለብ ድጋፍ እንዲቀርብ ጠይቀን እየተጓጓዘ ይገኛል" ብለዋል።

"ከመስከረም ወር ጀምሮ ችግር ይኖራል በሚል እየተሠራ ነው" ያሉት ኮሚሽነሯ "ለ12 ወር የሚሆን ድጋፍ ለመጠየቅ ዕቅድ ተይዟል" ሲሉ ገልጸዋል።

የተጠየቀው ድጋፍ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመው የሌሎች ድጋፍ በሚያስፈልግበት ወቅት በተቀናጀ መልኩ በቀጣይ ሊሠራ እንደሚችል አስረድተዋል።

በዞኑ የተሻለ ዝናብ ያገኙ አካባቢዎች በመኖራቸው ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ የሚፈልጉ አለመሆናቸው ታውቋል።