ዛሬ ዶዶላ ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በሌሎች ከተሞችም የተቃውሞ ሠልፉ ቀጥሏል

ባሌ ዶዶላ

በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ዛሬ በነበረ ግጭት አራት ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ ቢዮ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ትናንት በአካባቢው ከጠዋት ጀምሮ ሠልፍ እንደነበር የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ከሰዓት በኋላ ግን ይህ ሠልፍ መልኩን መቀየሩን ይናገራሉ።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ ትናንት ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መምጣታቸውንና ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት ሰዎች ደግሞ ምሽቱን ወደ ሻሸመኔና ሀዋሳ ለህክምና መላካቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደገለፁት የዛሬው ግጭት ሊቀሰቀስ የቻለው "ከሁለት ወር በፊት አንድ ወጣት መሳሪያ በመተኮሱ ለእርሱ በቀል ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

በወቅቱ ምንም አይነት ጉዳት ባይደርስም ትናንት ሰልፉን ተከትሎ ግን ግጭት ተከስቶ ሰዎች መጎዳታቸውን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ሱቆች መዘረፋቸውን ማየቱን ይናገራል።

ዛሬ ማለዳ በአካባቢው ግጭት መቀስቀሱንም አረጋግጠው አራት ሰዎች በዱላ ተመትተው ወደ ሆስፒታል እንደመጡና ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል። በጠቅላላው 6ሰዎች መሞታቸውንና አንዱ ወደ ሐዋሳ ከተላከ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዶዶላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ እንደሚናገሩት ግጭቱ የተከሰተው 02 ቀጠና አምስት በመባል በሚታወቀው ስፍራ ሲሆን ስድስት ቤቶች መቃጠላቸውንና ከብቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ይናገራሉ።

ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን የሚናገሩት ነዋሪው የዛሬው ግጭት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሳይሆን እርስ በእርስ የደረሰ መሆኑን ይናገራሉ።

በአካባቢው ያለው ችግር ከፖሊስ ቁጥጥር በላይ ነው የሚሉት ግለሰቡ መከላከያ ገብቶ ሁኔታዎችን ማረጋጋቱን ይናገራሉ።

ሁኔታው አስፈሪ ስለነበር ለሕይወታቸው የሰጉ ሰዎች በአካባቢው በምትገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው አንደሚገኙ ተናግረዋል።

"እነዚህ ወደ ሆስፒታላችን የመጡ ናቸው" የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ሌሎች የሞቱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ወሬ ከአካባቢው ማህበረሰብ መስማታቸውን ይገልጻሉ።

ዛሬም ተጎድተው ወደ ሆስፒታላቸው ከመጡ መካከል አንድ ግለሰብ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሀዋሳ መላኩን ዶ/ር ቶላ ገልፀው በአሁኑ ሰዓት ወደ ከተማዋ የመከላከያ ሠራዊት መግባቱን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት ወደ በስፍራው መግባቱንና የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን እያረጋጋ መሆኑን አረጋግጠውልናል።

ዛሬ ሐሙስ እስከ ቀትር ድረስ በድምሩ 50 የሚሆኑ ሰዎች ቀላልና መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል እንደገቡና በድምሩ የ6 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል። ተጎጂዎቹ በብዛት ወጣቶች እንደሆኑና በዱላና በድንጋይ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ መሆናቸውን ሰምተናል። ከተጎጂዎች መሀል የ11 ዓመት አዳጊ ይገኝበታል።

ሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች እንደምን አረፈዱ?

ከትናንትናው የቀጠለ ሠላማዊ ሰልፍ ዛሬ ማለዳም በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች መካሄዳቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ድሬዳዋ፣ አምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ቢሾፍቱ፣ ዶዶላን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም የተቃውሞ ሠልፎች የተካሄዱ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱ መንገዶችም መዘጋታቸውን ለማወቅ ችለናል።

የፎቶው ባለመብት, ASHABBIR

የተቃውሞ ሠልፍ የተካሄደባቸው ከተሞች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መገደባቸውን፣ የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ያነጋገርናቸው የከተማዎቹ ነዋሪዎች ገልፀውልናል።

በአምቦ ከተማ ዛሬ ቀጥሎ በዋለው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት ከሰልፈኞች አምስቱ ከጸጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች ሰምተናል።

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር የተጋጩ ሲሆን የከተማዋ ደህንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የከተማዋ ነዋሪ ጨምረው ተናግረዋል።

አሁንም የተኩስ ድምጽ ይሰማል ያሉት ግለሰቡ ከትናንት ጀምሮ ሲካሄድ በነበረው ሰልፍ የሟቾች ቁጥር 4 መድረሱን ገልፀውልናል።

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በዛሬው ሰልፍ አምስት ሰዎች በጥይት ቆስለው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የተናገሩ ሲሆን ሰልፈኞቹ የተመቱት በከተማ አስተዳደሩና መናሃሪያው መካከል ባለው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሾፍቱ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ከትናንትና የቀጠለ ሰልፍ እንደነበር አረጋግጠዋል።

ትናንትን የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ተጻርረው የወጡ ወጣቶች ጋር ግጭት ተፈጥሮ እየበረታ መሄዱን የገለፁት ነዋሪዎች በተጻራሪ ቆሞ የነበረው ቡድን ወደ ቤተ እምነቶች ሄዶ መጠለሉን ለማወቅ ችለናል።

በሰልፉ ላይ አንድ ወገንን ነጥሎ የሚቃወሙ መፈክሮች መሰማታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪ ስለታማ ነገሮችና የጦር መሳሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰልፈኞችንም ማየታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

በከተማዋ ዛሬ ማለዳ ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች ትናንት ከባድ ጉዳት ባይደርስም ዛሬ ያለው ሁኔታ መልኩን ቀይሮ እንዳለና አስጊ እንደሆነ ነግረውናል።

በተያያዘ ዜና በአዳማ ዛሬ ማለዳ ሰልፍ እና የጦር መሳሪያ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ነግረውናል።

ከጃዋር መሐመድ ጥበቃዎች መነሳት ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ትናንት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተካሄዱ ሰልፎችን ተከትሎ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።