የካሊፎርኒያን ሰደድ እሳት መቆጣጠር አልተቻለም

የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍጥነት ካለው ንፋስ ጋር ይታገላሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በካሊፎርኒያ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት እስካሁን በወይን ምርቷ በምትታወቀው ሶኖማ ግዛት ብቻ ከ10 ሺህ 300 ሄክታር በላይ ማውደሙ ተነገረ።

እሳቱ ለመድረስ አዳጋች በሆኑ ኮረብታዎችና ሸለቆዎች ውስጥ ይነድ ስለነበር ለማጥፋት አዳጋች አድርጎታል ተብሏል።

በአሁኑ ሰዓትም እሳቱ ሊስፋፋ ይችላል ስለተባለ የካሊፎርኒያ ባለስልጣናት በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች እንዲወጡ አዝዘዋል።

በሰሜን ሳን ፍራንሲስኮ በዊንድሰር እና ሄልድስበርግ የሚገኙ 50 ሺህ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ፓሲፊክ ጋዝ እና ኤሌትሪክ የተሰኘው ኩባንያ በ36 ግዛቶች ለ48 ሰዓት የሚቆይ መብራት ሊያጠፋ እንደሚችል ተናገረ።

በዚህ የመብራት መጥፋት ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ተጠቂ ይሆናሉ ተብሏል።

ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ነፋስ ተነስቶ የኤሌትሪክ መስመሮችን ሊጥልና እሳት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ፍራቻ አለ።

በሎስ አንጀለስ እና ሶኖማ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ መከላከል ሰራተኞች ሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር እየተረባረቡ ነው።

እስካሁን ድረስ ከሰደድ እሳቱ መቆጣጠር የተቻለው 10 በመቶውን ብቻ መሆኑ ታውቋል።

ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ነፋስ የሚጠበቅ ሲሆን የሀገሪቱ የአየር ጠባይ ትንበያ የሚከታተለው ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።

የሰደድ እሳቱ የተቀሰቀሰው የኤሌትሪክ ኃይልን ከማማ ጋር የሚያገናኘው ከፍተኛ መስመር ተበጥሶ ሲሆን ለእሳት አደጋው ፓሲፊክ ጋዝ እና ኤሌትሪክ ተጠያቂ ይሆናል የሚል ስጋት አለ።

ድርጅቱ ቀደም ብሎ ኪሳራ ያወጀ ሲሆን ለመስመሩ መበጠስ ያረጁ ገመዶች ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

እስካሁን ድረስ በሰደድ እሳቱ ምክንያት የሞተ ሰው የለም።