በአርጀንቲና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተቃዋሚው አሸነፉ

የአልቤርቶ ፈርናንዴዝ ደጋፊዎች በቦነሳይረስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጠች ባለችው አርጀንቲና የግራ ዘመም ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው አልቤርቶ ፈርናንዴዝ አሸናፊ ሆነዋል።

ፈርናንዴዝ ምርጫውን ያሸነፉት ለድል የሚያበቃውን ከ45 በመቶ የሚበልጥ ድምፅ በማግኘት እንደሆነ ተገልጿል።

ምርጫው ሲሶው የአርጀንቲና ህዝብ በድህነት አረንቋ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ የተካሄደ እንደመሆኑ የድምፅ ባለቤት የሆነው ህዝብ ድምፁን የሰጠው ሙሉ በሙሉ የእጩዎችን የኢኮኖሚ አማራጭ ሃሳብ በመመዘን ነው ተብሏል።

ፈርናንዴዝ ያሸፏቸው የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ሙርሲዮ ማርሲ በቅድመ ምርጫ ትንበያዎችም ሽንፈታቸውን ሰምተውት ነበር።

ትናንትናም መሸነፋቸውን በማመን ተቀናቃኛቸው ፈርናንዴዝን 'እንኳን ደስ ያለዎት ሰኞ ቤተ መንግሥት ይምጡና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ስለማድረግ እንነጋገር' ብለዋቸዋል።

አዲሱ ፕሬዘዳንት ፈርናንዴዝም ነገሮችን ሰላማዊ ለማድረግ ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጋር በማንኛውም መንገድ እንደሚተባበሩ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆን ድምፅ ተቆጥሮ ፈርናንዴዝ 47.79 በመቶ ድምፅ ሲያገኙ ማርሲ ደግሞ ያገኙት 40.71 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።