የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ንብረት የሆኑ በርካታ የግንባታ ማሽኖች በመራህ ቤቴ ተቃጠሉ

የመንገድ ሥራ ማሽነሪ

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us

የምስሉ መግለጫ,

የመንገድ ሥራ ማሽነሪ

ንብረትነታቸው የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህብረ ንብረት የሆኑ የመንገድ ሥራ ማሽነሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን መራህ ቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ውስጥ መቃጠላቸውን የድርጅቱ ባለቤት ለቢቢሲ ተናገሩ።

በንብረታቸው ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያረጋገጡት ለቢቢሲ አቶ ገምሹ በየነ ሲሆኑ "ፖሊሶች ይህን ለማስቆም ሞክረው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ነው የሰማሁት" ሲሉ ስለክስተቱ የተነገራቸውን ገልጸዋል።

የመራህ ቤቴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ አስፋውም በወረዳቸው ትናንት ችግሩ ተፈጥሮ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ችግሩ የተፈጠረውም የተወሰኑ የድርጅቱ ሰራተኞች ከድርጅቱ ጋር ባለመግባባታቸው መሆኑንም ገልጸው።

አቶ ገምሹ በአካባቢው ሁለት የመንገድ ሥራ ፕሮጄክቶች እንዳሏቸው በመጥቀስ አጠቃላይ የፕሮጄክቱ ዋጋም 2.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ወደ ስፍራው ለመንገድ ሥራው የተሰማሩት የማሽነሪዎች ብዛት በቁጥር ከ140-150 ይሆናሉ። ምን ያክሉ እንደተቃጠለ፤ ምን ያክሉ ደግሞ እንደተረፈ እስካሁን አላወቁሁም" ያሉት አቶ ገምሹ አጠቃላይ የማሽነሪዎቹ ዋጋ ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር እንደሚተመን ጠቅሰዋል።

ለንብረቱ መቃጠል ምክንያት ምንድነው? ተብለው የተጠየቁት ገመሹ ገበየ፤ "የክልሉ እና የፌደራል መንገሥት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እያጣሩ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ውጪ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌላ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ሰራተኛ እቀንሳለሁ በማለቱና የደሞዝ ጥያቄ ባለመመለሱ ሰራተኞቹ ትናንት በድርጅቱ የግባታ ማሽኖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

አቶ ተሾመ አክለውም "ሠራተኞቹ ለግንባታ ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፤ እኛም ጥያቄያቸውን መልስ እንዲያገኝ ጥረት አድርገን ነበር፤ ይህ ጥያቄ ባለመመለሱ ነው ወደዚህ ችግር የተገባው" ብለዋል።

በፕሮጄክቱ አማካኝነት ቢያንስ 1500 ለሚሆኑ የአካበቢ ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ገምሹ፤ "ሰው እየሰራ የሚበላበትን ማቃጠሉ አለማወቅ ነው ብዬ ነው የማምነው። የእራሳቸውን ንብረት ነው ያቃጠሉት። ይሄ ነው የምለው ነገር የለኝም" ብለዋል።

አቶ ገምሹ በተለይ ከአዲስ አበበ ወደ ሥፍራው ያቀኑ የመንገድ ሥራ ባለሙያዎች አከባቢውን ጥለው መሸሻቸውን ጨምረው ተናግረዋል። የፕሮጄክቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል እና ከአስተዳደራቸው ጋር የሚመክሩበት ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ተሾመ አስፋው ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ለጊዜው በቁጥጥር ስር የዋለ አካል አለመኖሩን ገልጸው በጉዳዩ ላይ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአካባቢው ወጣቶች ጋር እየመከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ገብቶ ችግሩን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተፈጠረው ችግር በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው የጉዳት መጠኑ እየተጣራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ድርጅቱ በትግራይ፣ በአማራ፣ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች ውስጥ በርካታ ግዙፍ የግንባታ ሥራዎች ማከናወኑን የጠቀሱት አቶ ገምሹ፤ በአከባቢው ያላቸው ፕሮጄክት በአጠቃላይ የ132 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት ግንባታ እንደሆነ ገልፈዋል።