በግጭት ለተፈናቀሉት የተሰበሰበው አስቸኳይ እርዳታ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

አስቸኳይ እርዳታ

የፎቶው ባለመብት, YARED SHUMETE FACEBOOK

ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ግጭቶች ለተፈናቀሉት የአስቸኳይ እርዳታ ማሰባሰብ በዛሬው እለት በሐገር ፍቅር ቴአትር ተጀምሯል።

ይህንን እርዳታ በማስተባበርም ላይ ያለው ከተለያዪ ቡድኖችና ግለሰቦች የተውጣጣውና ሃያ አምስት አባላትን የያዘው የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት የተባለ ኮሚቴ ነው።

በርካታ ቦታዎች ላይ የድረሱልን ጥሪዎችን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዘመቻ የተጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከጥዋት ሁለት ሰዓት ጀምሮ ለአስቸኳይ እርዳታ የሚውሉ ቁሳቁሶች ተሰብስበዋል።

ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ያሬድ ሹመቴ ለቢቢሲ እንደገለፀው የማይበላሹ፣ ማደር መዋል የሚችሉ፣ የምርት ጊዜያቸው ያላለፈባቸው፣ እዛው ሊዘጋጁ የሚችሉ የእህል አይነቶች ስንዴ፣ ፓስታ፣ ፍርኖ ዱቄት፣ ማኮሮኒ፣ ሩዝ የመሳሰሉ የምግብ ጥሬ እቃዎችና የዘይት እርዳታ ተለግሷል።

በተጨማሪ ደግሞ ተፈናቃዮቹ ለመኝታ የሚሆን ምንም ነገር ስለሌላቸው ብርድ ልብሶችና አልባሳትም ወደ ሐገር ፍቅር በተመሙ ነዋሪዎች ተሰጥቷል።

ለህፃናት አልሚ ምግቦች፣ የንፅህና መገልገያ ቁሳቁሶች በእርዳታው ከተካተቱ ቁሶች መካከል ናቸው።

በዛሬው እለትም የተሰበሰሰው ሶስት ጭነት መኪና የሚያክል ንብረት እንደሆነ ያሬድ ይናገራል።

"በጣም በአስገራሚ ፍጥነት ነው ህዝቡ አለኝታ መሆኑን እያሳየ ያለው፤ በጣም የሚያኮራ ነው። አንዱ እንግዲህ ገፅታችን ይኸኛው ነው ማለት ነው። ማፈናቀሉንም እኛው ነን አፈናቃዮች፤ በደል የምንፈፅመውም እኛው ነን። በተጨማሪም ደግሞ እንዲህ እርዳታ ላይ የምንሳተፈው እኛው ነን የሚለውንም የሚያሳይ ስለሆነ ትንሽ ተስፋ የሚሰጥ ነው።" በማለት ያሬድ ያስረዳል።

ኮሚቴው ተወያይቶ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያላቸው ስድስት ቦታዎች መርጧል። እነዚህም ምሥራቅ ሐረርጌ ጎሮ ጉቱ ወረዳ በሮዳና ካራሚሌ፣ በባሌ ሮቤ፣ በምዕራብ አርሲ ዶዶላ እና ኮፈሌ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰበታ ናቸው።

በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉና አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸው ግለሰቦች ቁጥር የሚቀያየርና መረጃው ክፍተት ሊኖረው ቢችልም ሲሆን እስካሁን ባለው መረጃ ከአስራ አምስት ሺ የማያንስ ተፈናቃይ እንዳለ ያሬድ ያስረዳል።

ምስራቅ ሐረርጌ ላይ መጀመሪያ የደረሳቸው ቁጥር 3ሺ ሰባት መቶ የነበረ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ ወደ አምስት ሺ እንዳደገ መስማታቸውን ይናገራል።

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ለሁለት ወይም ለሶስት ቀን የሚሆን አስቸኳይ እርዳታ እንደተላከ ያሬድ ጠቅሶ ከነሱ በኩል የተሰበሰበው ደግሞ ከነገ ማምሻውን ጀምሮ የሚሰራጭ ይሆናል።

አስቸኳይ እርዳታውን ለማሰራጨት የመንገዱ ደህንነትና ፀጥታ ምን ያህል አስተማማኝ ነው በሚል ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ያሬድ ሲመልስ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲሁም የደህንነት ከለላ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንደሚያገኙና በነሱም አማካኝነት እርዳታው ይላካል ይላል።

እስካሁን ባለው መከላከያ አጀባ በመስጠት በመተባበር ላይ እንደሆነም ያሬድ ይናገራል።

"በዚህ በኩል ብዙ ስጋት ይገጥመናል ብለን አናስብም። እነዚህን ስጋቶቻችንን ለመቅረፍ በሚል ሊያግዙንና ሊረዱን የሚችሉ አካላትን የኮሚቴያችን አባላት አድርገን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው" ብሏል

ኮሚቴው እስከ ረቡዕ ባለው ድረስ እርዳታውን ለመቀጠል ያቀደ ሲሆን፤ በርካታ ሰው ጥያቄ እያቀረበ በመሆኑም እስከ አርብ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ገልጿል።