የቲቢ ህክምናን የሚያዘምን ክትባት ይፋ ተደረገ

የቲቢ ህክምናን የሚያዘምን ክትባት ይፋ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቲውበርክሎሲስ ህክምናን የሚያዘምን ክትባት መገኘቱን ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ። ክትባቱ ለረዥም ጊዜ ከቲውበርክሎሲስ (ቲቢ) መከላከል እንደሚችልም ተገልጿል።

በመላው ዓለም በየዓመቱ በቲቢ ሳቢያ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ።

ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ የሚያገኘው ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሲሆን፤ ይፋ የተደረገው ህንድ ውስጥ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የሳንባ ጤና ውይይት ላይ ነው።

በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያ እና ዛምቢያ ከ3,500 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ክትባቱ ተሞክሯል።

የቲቢ ተመራማሪው ዴቪድ ሌይንሶን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ክትባቱ የቲቢ ህክምናን የተሻለ ያደርጋል። "ቲቢን በሚያስከትለው ማይክሮባክቴሪየም ቲውበርክሎሲስ የተያዙ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በማይክሮባክቴሪየም ቲውበርክሎሲስ የተጋለጡ ሰዎች በአጠቃላይ ለቲቢ በሽታ እንደማይጋለጡ የተናገሩት ተመራማሪው "ክትባቱ የሰውነትን የመከላከል ብቃት ያበለጽጋል" ብለዋል።

ክትባቱ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት በሌሎች ሰዎች ላይ ተጨማሪ ሙከራ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ሙከራው በተያዘው እቅድ መሰረት ከተጠናቀቀ ክትባቱ በ2028 ጥቅም ላይ ይውላል።

በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት፤ ባለፈው ዓመት 10 ሚሊየን ሰዎች በቲቢ ተይዘዋል። በዓለም ላይ በብዛት በቲቢ የሚጠቁ ሰዎች ካሉባቸው አገራት ህንድ (27%)፣ ቻይና (9%) እና ኢንዲቬዥያ (8%) ይጠቀሳሉ።

በሽታው በዓመት 400,000 ህንዳውያንን ይገድላል።