በእዳ ተይዞ የነበረው ብቸኛው የዚምባብዌ አውሮፕላን በረራ ጀመረ

ኤይር ዚምባብዌ በአንድ አውሮፕላን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ብቸኛ መዳረሻውም ጆሃንስበርግ ከተማ ነው

የፎቶው ባለመብት, Air Zimbabwe

የምስሉ መግለጫ,

ኤይር ዚምባብዌ በአንድ አውሮፕላን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ብቸኛ መዳረሻውም ጆሃንስበርግ ከተማ ነው

ባሳለፍነው ሳምንት በእዳ ተይዞ የነበረው ብቸኛው የኤይር ዚምባብዌ አውሮፕላን በረራ ጀመረ።

ይህ ብቸኛ አውሮፕላን ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ በረራ ካደረገ በኋላ ነበር ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት መክፈል የነበረበትን እዳ እስኪከፈል ተይዞ የቆየው።

የዚምባብዌ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ኤይር ዚምባብዌ፤ በጆሃንስበርግ አየር ማረፊያ የአገልግሎት ክፍያዎች ውዝፍ እዳ አለበት ተብሏል።

አየር መንገዱ ያለበት የዕዳ መጠን እና አውሮፕላኑን ነጻ ለማውጣት ምን ያክል ክፍያ እንደፈጸም አልተገለጸም።

ባለቤትነቱ የዚምባብዌ መንግሥት የሆነው ኤይር ዚምባብዌ፤ በአንድ አውሮፕላን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ብቸኛ መዳረሻውም ጆሃንስበርግ ከተማ ነው።

"በረራችንን ዛሬ ጀምረናል። አውሮፕላኑ ዛሬ ጠዋት ወደ ጆህንስበርግ በረራ አድርጓል" ሲሉ የኤይር ዚምባብዌ ኮርፖሬት አግልግሎቶች ኃላፊ የሆኑት ታፋደዘዋ ማንዶዜ ለሄርልድ ኒውስ ተናግረዋል።

"በረራ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ፍቃድ አግኝተናል። የሚጠበቅብንን ክፍያዎችም ፈጽመናል" ብለዋል።

ኤይር ዚምባብዌ እአአ 2017 ላይ በተከማቸበት ከፍተኛ ውዝፍ እዳ ከግማሽ በላይ ሠራተኞቹን ለማሰናበት ተገዶ ነበር።

ይህም ብቻ ሳይሆን ኤይር ዚምባብዌ በደህንነት ስጋት ምክንያት በአውሮፓ አገራት አየር ክልል የመብረር ፍቃድ የለውም።