አሳሳቢው የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር በኢትዮጵያ

ጠመንጃና ላውንቸር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የባህል ቅርስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቢራራ የዛሬ ስድስት ዓመት በጉለሌ አካባቢ የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ምን እንደሚመስል ጥናት አካሂደው ነበር።

ጥናታቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከእንጦጦ ጫካ ጋር ተያይዘው ባሉ አካባቢዎች እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ እንደተረዱት ሕገወጥ መሳሪያ ዝውውሩ ይደረግ የነበረው ሌሊት ነው።

ይህንንም ማወቅ የተቻለው በጫካውና በተለይ በቀጨኔ መድኃኒያለም የቀብር ቦታዎች አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማባቸው የነበሩ ጊዜያት መመዝገባቸው ነው።

በጫካውና በቀብር ስፍራዎቹ አካባቢ ይሰማ የነበረው ጦር መሳሪያ ተኩስ በመሳሪያ ሽያጭ ልውውጡ ወቅት የሚደረግ ፍተሻ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በወቅቱ በጥናታቸው ውስጥ እንደ ችግር ያነሱት የመሳሪያ ፈቃድ አሰጣጡ የላላ መሆንን ነው።

ፈቃድ ሰጪው አካል የመሳሪያው ምንጭ ከየት እንደሆነ፣ ለምን እንደተፈለገ፣ መሳሪያውም ምን እነደሆነ ሳይታወቅ ፈቃድ እንዲሰጠው የሚፈልግ ሰው የመሳሪያውን ፎቶ ብቻ ይዞ በመሄድ ብቻ ያገኝ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይህ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የትጥቅ ማስፈታት ሳምንት ሆኖ ሲከበር ቆይቷል።

በኢትዮጵያም በተለያየ ወቅት በክልሎችም ሆነ በመዲናዋ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲዘዋወር ተያዘ የሚል መረጃ በተደጋጋሚ ይሰማል።

ይህ የሕገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል የሚናገሩ ባለሙያዎች ይህ ሁኔታ ወደ ከፋ ጉዳት እንዳያመራ ያላቸውን ስጋት ያስቀምጣሉ።

በአንድ ወቅትም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ የደህንት ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዳደ ደስታ፤ በግለሰቦች ወይም በአነስተኛ ቡድኖች ሊያዙ የሚችሉ ሕገ ወጥ መሳሪያዎች መሰራጨታቸው ኃይል መጠቀም የመንግሥት ብቻ የሆነ ስልጣን ሆኖ ሳለ በሌሎች ሰዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች እጅም እየገባ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀው ነበር።

አቶ ዳደ 'አደገኛ ነው' የሚሉትን የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር፤ በክልሎች ከሚነሱ ግጭቶች፣ ከፕሮፓጋንዳ መሳሪያነቱ እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ ድርጅቶች ጋርም ያያይዙታል።

አክለውም የጦር መሳሪያዎች ዝውውሩ ወጥቶ መግባትንም አስጊ እንደሚያደርገው ይናገራሉ። ኅብረተሰቡ መንግሥት ላይ አመኔታ ሲያጣ ቤተሰቡን ለመጠበቅ ወደ ጦር መሳሪያ ሸመታ ሊያመራ መቻሉ ደግሞ ስጋታቸውን ያከብደዋል።

በጉምሩክና በመከላከያ በኮንትሮባንድ የተያዙ የጦር መሳሪያዎች ብዛት

ጉምሩክ በመላው ሀገሪቱ 12 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን በ2011 እና በ2012 ዓ.ም ውስጥ በዘጠኙ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ አይነት ሕገ ወጥ መሳሪያዎችና ጥይቶች መያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በ2011 ዓ.ም ብቻ በጉሙሩክና መከላከያ የተያዙ መሳሪያዎች ብዛት 2020 ሽጉጥ፣ 62 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 4 መትረየስ መሆኑን ከገቢዎችና ጉሙሩክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በዚሁ ዓመት 917 የመትረየስ ጥይት፣ 2ሺህ 983 የብሬን ጥይት፣ 15 ሺህ 717 የብሬን ጥይት፣ 80 ሺህ 764 የሽጉጥ ጥይት መያዛቸውን ተቀምጧል።

ባለንበት ዓመትም 1 መትረየስ፣ 113 ክላሽንኮቭ፣ 382 ሽጉጦች መያዛቸው ተመዝግቧል።

በዚሁ ዓመት 111 የመትረየስ ጥይት፣ 3 ሺህ 581 የብሬን ጥይት፣ 5 ሺህ 231 የክላሽንኮቭ ጥይት 4 ሺህ 910 የሽጉጥ ጥይትና 122 የክላሽ ካዝና መያዛቸውን የጉሙሩክ መረጃ ያሳያል።

ከዘጠኙ የጉሙሩክ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ ወጥ መሳሪያና ጥይት የተያዘው በቃሊቲና ባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆን ዝቅተኛ መሳሪያ የተያዘው ደግሞ በመቀሌው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኩል መሆኑን መረጃው ያሳያል።

በመስሪያ ቤቱ የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትል የሥራ ሂደት መሪ የሆኑት አቶ ዘላለም እንደሚናገሩት በ2011 ዓ.ም በልዩ ሁኔታ በቦሌ አየር መንገድ ሴኪዩሪቲ መጋዘን በተደረገው ፍተሻ 3 ስናይፐር፣ 3 የአደን ጠመንጃ፣ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን የጦር መሳሪያ መለዋወጫ እንደተገኘም ተናግረዋል።

መሳሪያዎቹ መቼ እንደገቡና በማን እንደገቡ አይታወቅም የሚሉት ኃላፊው፣ መጋዘኖቹ ውስጥ አጠቃላይ ፍተሻ ሲደረግ መገኘታቸውን ያስረዳሉ።

በመንገደኞች ጓዝ በኩል ከጀርመን ሲገባ የተያዘ 1 ሽጉጥ በዚሁ መጋዘንም እንደተገኘ ከጉሙሩክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅትም ፈቃድ ሳያገኝ ለጥበቃ ሰራተኞቹ ሊያስገባ የነበረው 59 ሽጉጥና 122 ሺህ ጥይት በጉሙሩክና በድርጅቱ ቁልፍ ተቆልፎ እንደሚገኝም ጨምረው አስረድተዋል።

እነዚህን መሳሪያዎች ውሳኔ ባለማግኘታቸው አሁንም እንደተቆለፈባቸው መሆናቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Police

የምስሉ መግለጫ,

ከወራት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ የተባሉ የጦር መሳሪያዎች

በክልሎች በኩል ያለው ገጽታ

በትግራይ የጸጥታና ደህንነት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃፍታይ መለስ በክልሉ በተለያየ አጋጣሚና አካባቢ የሚዘዋወር ህገወጥ የጦር መሳርያ አለ ይላሉ።

ባለፈው ዓመት 155 ሽጉጥ፣ 16 ክላሽ፣ 22 ቦንብ፣ 10 ሺህ 922 የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር መዋሉን ያስታውሳሉ።

እነዚህ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ትግራይን ከአማራ ክልልና ከሱዳን በሚያዋስኑ አካባቢዎች ሲገቡ የተያዙ መሆናቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ።

ሌሎች በትግራይ ውስጥ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውንም ለቢቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።

እነዚህ የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሮች በአቋራጭ ጥቅም ለማግኘትና ለመበልጸግ በመፈለግ የሚደረግ ተግባር መኖሩን እንደሚያመለክት ገልፀዋል።

ሕገ ወጥ መሳሪያውን ሲያዘዋውሩ የተያዙ አካላት ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን አስረድተው ፍርድ የተሰጣቸው መኖራችውንም ያስረዳሉ።

ከኦሮሚያ፣ ከአማራ ክልልና ከፌደራል ፖሊስ የሕገወጥ መሳሪያዎችን በሚመለከት መረጃ ለማግኘት ደጋግመን ብንሞክርም ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ሊሳካልነን አልቻለም።

የተወሰዱ ርምጃዎች

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኑ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እንዲህ በስፋት የሚዘዋወርባቸውን ምክንያት ሲያስረዱ አሁን ያለው የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀጥል ለማድረግ እንደሆነ በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ።

በተለይ ደግሞ ይህ የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር የሕዝብን አንድነትና ሰላም በማይፈልጉ አካላት መሆኑን በመጥቀስ፤ የገንዘብ አቅማቸውን ለማደለብ የሚሰሩ የተደራጁ ቡድኖችም በዚህ ድርጊት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በሚፈጠር ስጋት ጋር ተያይዞ የጦር መሳሪያ ለመግዛት ያለ ፍላጎት እየጨመረ ያለበት ሁኔታ እንደሚታይም ይናገራሉ።

በተደጋጋሚ ወደ ሀገር ውስጥ ሕገወጥ መሳሪያ ለማስገባት የሚሞክሩ አካላትን የጸጥታ መዋቅሩ እየተከታተለ በቁጥጥር ስር እንደሚያውል የሚናገሩት አቶ ዝናቡ፤ ሕገወጥ መሳሪያ ዝውውሩ እየጨመረ መምጣቱንም የሚያመላክቱ ነገሮች መኖራቸውን አልሸሸጉም።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተሳተፉት ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን፤ በተጨማሪም መሳሪያዎቹ ሲጓጓዙባቸው የነበሩ መኪኖችም በቁጥጥር ስር ውለው በሕግ ውሳኔ መሰረትም የተወረሱ እንዳሉ ገልፀዋል።

መሳሪያዎቹ ድንበርን አቋርጠው አንደሚመጡ የሚናገሩት አቶ ዝናቡ፤ ከድንበር አልፈው ንግድ እንቅስቀሴ በስፋት በሚካሄድባቸው በሰሜን በኩል ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ በምትዋሰንባቸው፣ በምሥራቅ በሶማሌ ድንበር በኩል፣ በደቡብ ደግሞ በሞያሌ ኬኒያ በኩል እንደሚገቡና ንግድ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጠጠር አዲስ ሕግ

የመሳሪያ አያያዝ አጠቃቀምና ፈቃድ አሰጣጥን ሂደትን ትኩረት ሰጥቶ የህግ ማሻሻያ ቢደረግ በማለት የጦር መሳሪያ መያዝ ያለበት ማን ለምን አንደሆነ ቁርጥ ያለ አቅጣጫ ተቀምጦ ማስተካከያ ቢደረግ ሲሉ በጥናታቸው መጠቆማቸውን አቶ ደሳለኝ ቢራራ ያስታውሳሉ።

ከዚህ አንጻርም ሕገ ወጥ መሳሪያውን ለመቆጣጠር በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ተገቢ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ጠንከር ያለ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ለቢቢሲ ጠቁመዋል።

በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች ያልሸፈኗቸው ጉዳዮች በመኖራቸውም ይህንን ህግ ማርቀቅና ወጥነት ያለው ሥርዓትን መዘርጋት አስፈልጓል የሚሉት አቶ ዝናቡ፤ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በባህል የተነሳ መሳሪያ መታጠቃቸውን በማስታወስ በምን ዓይነት ሁኔታ መተዳደር ይቻላል የሚለውንም መወሰን ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ያለው ሕግ የተያዙ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች እንዲወረሱ ቢያዝም አዘዋዋሪዎቹ ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት እንደማይጣል ገልጸው ያለው ሕግ አስተማሪ አልሆነም ይላሉ።

እየተዘጋጀ ያለው ረቂቅ ሕግ ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ እየተረቀቀ መሆኑን አስታውሰው በውስጡ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም፣ የተከለከሉ ተግባራት፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የተከለከለባቸው ስፍራዎች፣ ጦር መሳሪያ ፈቃድ የማይሰጥባቸው ተቋማት፣ የጦር መሳሪያ ፍቃድንም ማስተዳደርን የተመለከቱ ጉዳዮች በረቂቁ ውስጥ መካተታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አዲሱ ረቂቅ ሕግ እነማን ምን አይነት መሳሪያ ይታጠቃሉ፣ በተቋማት ደረጃ ምን አይነት መሳሪያ መታጠቅ ይቻላል የሚሉ ጉዳዮችም ተካተዋል ብለዋል።

በረቂቅ ሕጉ ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ተቀምጧል በማለትም "የጦር መሳሪያ የያዘ፣ ያከማቸ፣ ያዘዋወረ፣ ያደሰ/የጠገነ፣ እየተዘዋወረ አይቶ ዝም ያለ ላይ ሁሉ ቅጣት ይጣላል" ይላሉ።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ቅጣት ከ10 ዓመት ጀምሮ ሲሆን የገንዘብ ቅጣትም አንደሚኖረው ተናግረዋል።

መሳሪያዎቹ በድንበር አካባቢዎች መግባታቸውን በማስታወስም ይህንኑ ለማስቀረትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያው ሩብ አመት ከወንጀል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በርካታ ንብረቶች በፍርድ ቤትና ከፍርድ ቤት ውጭ (በጉምሩክ ባለሰልጣን መ/ቤት) ለመንግሥት ገቢ መደረጋቸውን የገለጹት አቶ ዝናቡ ከእነዚህም ውስጥ የጦር መሳሪያዎች ይገኙባቸዋል።

እነሱም 4 ከባድ መትረየስ፣ 42 ክላሽ፣ 1 ማካሮቭ፣ 20‚996 የተለያዩ አይነት ጥይቶች፣ 27 ካዝና፣ እንዲሁም 10‚676 የክላሽና የሽጉጥ ጥይት፣ 1 ባለሰደፍ ክላሽ ፣ 6 ሽጉጥ፣ በአቃቤ ህግ ውሳኔና በጉምሩክ አዋጅ እንዲወረሱ ለፖሊስ ትዕዛዝ መተላለፉን ያስረዳሉ።

ከዚሁ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቀረቡ 8 ክሶች መነሻ የሁሉም ተከሳሾች የዋስትና መብት ታግዶ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ ዝናቡ አክለውም ሦስት አይሱዙ መኪኖች እንዲሁም ሌላ ተሽከርካሪ የጦር መሳሪያ ሲያጓጉዝ በመያዛቸው እንዲወረሱ መወሰኑን ተናግረው፤ አይሱዙ የጭነት መኪናው በሀሰተኛ ሰነድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በመያዙ መወረሱንም ገልጸዋል።

ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳደ የሕገ ወጥ መሳሪያዎቹ በዘራፊዎች ወይም ሕገ ወጥ የፖለቲካ አላማ ባላቸው ሰዎች እጅ ሊገቡ የሚችሉበት እድል መኖሩን በመግለጽ፤ መንግሥትን ኃይል ከማሳጣቱ ባሻገር ህብረተሰቡን አደጋ ላይ የሚጥልም እንደሆነ ይገልፃሉ።

አቶ ዳደ ዝውውሩ ወጥቶ መግባትንም አስጊ እንደሚያደርገው ይናገራሉ። ኅብረተሰቡ መንግሥት ላይ አመኔታ ሲያጣ ቤተሰቡን ለመጠበቅ ወደ ጦር መሳሪያ ሸመታ ሊያመራ መቻሉ ደግሞ ስጋታቸውን ከፍ ያደርገዋል።

አቶ ዳደ ሕግና ሥርዓት ማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን አስረግጠው፤ "መንግሥት ሳይዘገይ አስፈላጊ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። አስፈላጊውን ንቅናቄ ማድረግም አለበት" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ተራው ዜጋ በድብቅ መሳሪያ ከታጠቀ ብቸኛ ምክንያቱ ሊሆን የሚችለው ፖለቲካዊ ነው" ብለው፤ ይህ ደግሞ አገርን አደጋ ላይ እንደሚጥል ያስረዳሉ። በተለይም የጦር መሳሪያ ስርጭቱ በተደራጀ ኃይል ቁጥጥር ስር የሚውል ከሆነ ወደ እልቂት ማምራቱ አይቀርም ብለዋል።