በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር በስማቸው ማህበራዊ ሚድያ ላይ የወጣ መረጃን ውድቅ አደረጉ

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, Ambassador Estifanos/twitter

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስቲፋኖስ አፈወርቂ 'የኤርትራ ህዝብ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ትግራይ እንዲሄዱ አይፈልግም' ብለዋል በሚል ማህበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ በስማቸው የተሰራጨው መረጃ የእርሳቸው እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናገሩ።

"እኔ እንደዛ ብዬ አልተናገርኩም፣ አላሰብኩም አልጻፍኩምም። ሶሻል ሚድያ ብዙ ሰዎች ስለሚጠቀሙበት፣ የሆነ አካል ያደረገው ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወደ ትግራይ ጉዞ የማድረግ ፍላጎት አላቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ሰጥተው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመቀለ ጎዳናዎች መዘዋወር እንሚፈልግ በተደጋጋሚ ገልጾልኛል . . . ይህም እንዲሳካ በጸሎት አግዙን" በማለት ተናግረው ነበር።

ይህን ተከትሎ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ "የክልሉ ህዝብና መንግሥት በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው የሰላም ሂደት የተሳካ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው" ገለጸዋል።

የሰላም ሂደቱ ሙሉ በሙሉ መሳካት የሚችለው ግን ፕሬዝዳንቱ በአውሮፕላን ሳይሆን የተዘጉ ድምበሮች ተከፍተው በእግር ወይም በመኪና ወደ ትግራይ መምጣት ሲችሉ መሆኑን በሰጡት ማብራርያ ላይ ተናግረው ነበር።

አምባሳደር እስቲፋኖስ በእሳቸው ስም በማህበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ ስለወጣው መልዕክት ለቢቢሲ ሲናገሩ "ይህን ሆን ብለው የሚያደርጉ በኢትዮጵም በምሥራቅ አፍሪካም የተጀመረውን የሰላም እንቅስቃሴ ማስተጓጎል የሚፈልጉ አካላት ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

"በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያም ይሁን በአፍሪካ ቀንድ፤ ማለትም በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በኤርትራና በሱዳን፣ እንዲሁም በሶማሊያና በኤርትራ መካከል እየተፈጠረ ያለውን የሰላም እንቅስቃሴ የሚጻረሩ አካላት ናቸው" ብለዋል አምባሰደሩ።

ይህ ፍላጎታቸውም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ "በቀጠናችን ያለውን ህዝብ ለማጋጨት የሚፈጥሩት ዘዴ ነው" በማለት አብራርተዋል።

አምባሳደር እስቲፋኖስ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉዞን በተመለከተ የሚሰጡ ሐሳቦችን "የቃላት ጨዋት" ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ።

"ብዙ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም። በቃላት ዙርያ የሚደረግ ጨዋታ ወደ ምንም ሊያደርስ አይችልም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በእግር ወይስ በአውሮፕላን እያሉ ወሬ ማብዛቱ ትርጉም አልባ ነው። በዚህ ላይ ብዙ ጊዜያችንን ማጥፋት ያለብን አይመስለኝም። የሰላም ሂደት ስለተጀመረ 'ሂደቱን ትደግፋለህ ወይስ አትደግፍም?' የሚል ነው ዋናው ጉዳይ" በማለት አስረድተዋል።

የሰላም ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ እንዲሁም የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እንደሆነም ገልጸዋል።