"በመንግሥት መዋቅር ሥር ውስጥ ሆነውም ግጭቶችን የሚያባብሱ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን" ኢዜማ

ኢዜማ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Citizens for Social Justice

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሰሞኑ የተፈጠሩ ግጭቶችን በተመለከተ ትናንት ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ. ም. መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው በተለይ ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ነው ካለው እና ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው "ተከብቤያለሁ" ብሎ ለሕዝብ መረጃ ካሳራጨው ጀምሮ ጥፋት ያደረሱ ሰዎች በሕግ እንዲጠየቁ ይጠይቃል። ስለ መግለጫውና ተያያዥ ጉዳዮች የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀን አነጋግረናል።

ንት ኢዜማ ያወጣው መግለጫ ይዘት ምንድን ነው?

አቶ ናትናኤል፦ ስምንት ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ ነው ያወጣነው። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በተፈጠሩ ሁከቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ እንዲሁም የተለያየ አካል ጉዳት መድረሱን መነሻ በማድረግ የተሰጠ መግለጫ ነው። አገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል። ያ ሽግግር እና የአገር አንድነትን ለማረጋገጥ ዜጎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፍርሀት የፈጠረባቸው ኃይሎች የመጨረሻ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገቡበት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተረድተናል።

ለጠፋ ሕይወትና ለተጎዱ ሰዎች ሀዘናችንን ገልፀን፤ ይህንን ድርጊት በመፈፀም ከመነሻው ጀምሮ ምክንያት የሆኑና በተለያየ ደረጃ ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀናል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለይ እነዚህ ግጭቶችን በማባባስ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ስልጣን ያለው አካል እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀናል። በተለያየ አካባቢ የተፈፀመውን ድርጊት ተከትሎ ሰዎች ቁጭት ላይ ስለሆኑ ወደ አላስፈላጊ ድርጊት እንዲሁም የመልስ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት እንዳለ የሚያሳዩ ጉዳዮች ስላሉ፤ ይህ ፍላጎት በፍፁም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይገባውና በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበናል። በአጠቃላይ በአገር ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም መጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ውይይት በቶሎ መጀመር እንዳለበት ገልፀን፤ እዚህ ውይይትም ውስጥ ለመሳተፍ ያለንን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የገለፅንበት ነው።

በመፈናቀል፣ በድርቅ እና ሰሞኑን ባጋጠመው የአንበጣ መንጋ የተመቱ አካባቢዎች እንዳሉና እነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ማግኘት እንደሚገባቸውና ትኩረት አጥተው የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ በመግለጫችን ጥሪ አስተላልፈናል።

መግለጫው እንደዚህ አይነት ግጭቶች ለመፈጠራቸው ምክንያቱ ባለፉት ጊዜያት ተዘርተው ከነበሩ የዘረኝነትና የአግላይነት ፖለቲካ ለመላቀቅ ሰው በመንቀሳቀሱ ነው ይላል። እውን ምክንያቱ ይህ ነው? ለለውጥና ለአንድነት መንቀሳቀሳቸው ነው ይንን ችግር ያመጣው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ ባለፈው ሳምንት የተፈጠረው ነገር ከሌላው የተለየ ክስተት ነው ብለን አናምንም። ተነጥሎ የሚታይ ድርጊት ነው ብለን አናምንም። በተለያየ አካባቢ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዲደርስ ያደረጉ ግጭቶች ሲነሱ ቆይተዋል።

እነዚህ ሁሉ ተደምረው በአጠቃላይ ትልቁ ምስል፤ በዜጎች መካከል በዘውግ ወይም በሀይማኖት ልዩነት ለመፍጠር የሚደረገው ነገር፤ ዲሞክራሲያዊና ዜጎችን እኩል እድልና እኩል መብት የሚሰጥ ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረገው ጉዞ ያስቀራቸው ኃይሎች በተደጋጋሚ እዚህ ጉዞ ላይ ችግር እየፈጠሩበት እንደሆነ ነው። ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ነገር ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን የዚህ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳንሄድ የማደናቀፍ ሙከራ አንዱ አካል ነው ብለን ነው የምናምነው።

መግለጫውን ለማውጣት አልዘገያችሁም?

አቶ ናትናኤል፦ መግለጫ ለማውጣት ዘግይተናል ብለን አናስብም። ጉዳዩ ተከስቶ ወዲያውኑ የሀዘን መግለጫችንን አስተላልፈናል። ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ የሆነ ከኛ የምርጫ ወረዳ አባላት የሚመጡ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ነበረብን። እንዲሁ ዝም ብሎ በጨበጣ ከሚዲያዎች ላይ በሚነሱ ነገሮች ተነስተን መግለጫ መስጠት አልፈለግንም። ከራሳችን የምርጫ ወረዳዎች የሚመጡ መረጃዎችና ማስረጃዎች ለማሰባሰብ ከወሰደብን ጊዜ ውጪ ዘግይተናል ብለን አናስብም።

ኤዜማ እንዲህ አይነት ክስተቶች ሲፈጸሙ መግለጫ ለማውጣት ድፍረት ያጣሲባል ይሰማል። እውን ድፍረት ታጣላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ እውነት ለመናገር ምንም የምንፈራው ነገር የለንም። የሚፈራው የሚመስለኝ እስር፣ መሞት ወይም ከአገር መሰደድ ነው። ኢዜማ ውስጥ ያለው ስብስብ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ ብሎ የሚፈራ እንዳልሆነ በተግባር የታየ ነው።

ከዚህ በፊት የታሰሩ፣ የተሰደዱ፣ ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠባቸው ሰዎች ያሉበት ነው። ለነጻነትና ለእኩልነት እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ትግል ሲባል። ኢዜማ ውስጥ ያሉት በተግባር የተፈተኑ ሰዎች ናቸው። የሚነሳው ወቀሳ አግባብ ነው ብዬ አላምንም።

እኛ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው የአገር ሰላም፣ አንድነትና እኩልነትን ነው። ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገው ሽግግር ትዕግስተኛነትና የሰከነ የፖለቲካ ጉዞ ይፈልጋል ብለን በማመን፤ ግጭትን ከሚያነሳሱ እና ኃይለኝነት ከሚያሳዩ ንግግሮች እንቆጠባለን። ያ ምናልባት በስህተት ከፍርሀት ተወስዶ ከሆነ መታረም አለበት ብለን ነው የምናምነው።

የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በተደጋጋሚ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ተጋብዘው እንደሚወያዩና ከመንግሥት ጋር ያለው ቅርርብ ፓርቲውን ድፍረት እንዳሳው ይነገራል።

አቶ ናትናኤል፦ ፕ/ር ብርሀኑ ከዚህ በፊት የፖለቲካ ታሪካቸው ምን እንደነበረ ለሚያውቅ ሰው አንድም ውሀ የሚቋጥር አይደለም። በተደጋጋሚ እንዳልነው ኢዜማ እንደ ፓርቲ ከመንግሥት ጋርም ይሁን ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ጋር አገርን በማረጋጋትና ሰላም እንዲመጣ እንዲሁም ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር ሰላማዊ እንዲሆን ከሁሉም አካላት ጋር ይሠራል። የአገር አንድነት ላይ አደጋ ሲመጣ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር አደጋ ውስጥ ሲወድቅ፤ ምንንም፣ ማንንም ፈርተን ወደ ኋላ የምንል አይደለም። የፓርቲያችን መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ለዚህ ጉዳይ በተግባር የተፈተነ ተሞክሮ ያላቸው ሰው ናቸው።

በመግለጫው ላ ካስቀጣችሁት ነጥብ አንዱ "ተከብቤለሁ" ብሎ ለሕዝብ መረ ካሰራጨው ጀምሮ ሌሎች ጉዳት ደረሱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ነው። እነዚህ አካላት እነማን ናቸው?

አቶ ናትናኤል፦ ይሄ ችግር ሲነሳ ከምን እንደተነሳ ሁሉም ሰው ያውቃል። በማኅበራዊ ድረ ገጽ አደጋ ሊደርስብኝ ነው የሚል መረጃ ያሰራጩ ሰው አሉ። ከዛ ግለሰብ አንስቶ ይህንን ጥሪ ተከትሎ በየደረጃው የወንጀል ተግባር የፈጸሙ በሙሉ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ነው ጥያቄ ያቀረብነው።

ይሄ ለግጭቱ መነሻ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ ሌላ ምንም የተከሰተ ነገር የለም። ይሄ ነገር ከተከሰተ በኋላ ነው በቀጥታ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች የተነሱትና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ የደረሰው። ምንም ቢሆን ደህንነቴ አደጋ ውስጥ ገብቷል ብሎ የሚያስብ ሰው በየደረጃው ላሉ የመንግሥት አካላት ማሳወቅ እንጂ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ግጭትን በሚያነሳሳ ሁኔታ እንደዚህ አይነት ጥሪ ማድረግ አለባቸው ብለን አናምንም። ስህተት ነው። ለዛ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል ብለን ነው የምናምነው።

ማንን ነው የምትሉት?

አቶ ናትናኤል፦ እሱ በጣም ግልጽ ነው ብለን ነው የምናምነው። ግን በተጠየቅን ጊዜ የመንግሥት አካል ማንን ነው ያላችሁት? ብሎ ካለን ከማስረጃ ጭምር ለማቅረብ ዝግጁ ነን።

አሁን ላይ ስም መጥቀስ አልፈለጋችሁም?

አቶ ናትናኤል፦ አዎ። ይቆየን።

የኢዜማ የወጣቶች አደረጃጀት አዳማ ላይ ቄሮ የተባውን ቡድን ለመመከት ጉዳት አድርሷል የሚል ክስ ይቀርባልህ አይነት አደረጃጀት አላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ እኛ በ400 የምርጫ ወረዳዎች በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረው የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ የሚሠሩ የምርጫ ወረዳ አደረጃጀቶች አሉን። አዳማ የተለየ አይደለም። በማንኛውም መልክ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚደረጉ ነገሮች እኛ አደረጃጀት ውስጥ አይሳተፉም። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ፓርቲያችን ከመመስረቱ በፊት በ312 የምርጫ ወረዳዎች በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈራረሙበትን የሥነ ምግባር የቃል ኪዳን ሰነድ ጭምር አሰልጥነናል።

ኢዜማ በጣም ብዙ ነገር ነው የሚባለው። ግጭት አስነሳ የተባለው የቅርብ ክስ ከነዚህ አንደኛው ነው። መሰረተ ቢስ የሆነ ክስ ነው። ከዚህ በፊትም የተለያዩ ነገሮች የተባለ ፓርቲ ነው። ይህ ለምን እንደሆነ እናውቃለን። ምን ፈርተው እንደዚህ አይነት ክስ እንደሚያቀርቡ እናውቃለን። በዋነኛነት ማኅበረሰቡ እንዲረዳ የምንፈልገው እኛ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተወዳድረን ስልጣን መያዝ ነው አላማችን። ከዛ በፊት ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው ለአገር መረጋጋትና ሰላም ነው። አባሎቻችን ለሰላምና መረጋጋት ይሠሩ እንደነበር በማስረጃ አስደግፈን ማቅረብ እንችላለን።

ስለዚህ አልተሳተፋች?

አቶ ናትናኤል፦ በፍጹም እንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ተሳትፎ አልነበረንም።

ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት የሰው ሕይወት ለፈባቸው ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች ነበሩኢዜማ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው ይላል?

አቶ ናትናኤል፦ በየቦታው ለተፈጠሩ ችግሮች የየራሱ የሆነ ተጠያቂ አካል ይኖራቸዋል። በተለይ ድርጊቱን በመፈጸም የተሳተፉ አካላት የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በዋነኛነት ተጠያቂ የሚሆኑት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ የፖለቲካ ሥርዓት መመስረት ሂደት ላይ እንቅፋት ለመጣል የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው። መንግሥትም ይሄን ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ አለበት ብለን ነው የምናምነው።

በመግለጫው መንግሥት አለበት ያላችሁትን ክፍተት ስላነሳችሁ ነው ይህንን ጥ ያነሳሁት

አቶ ናትናኤል፦ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግርና ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ የፖለቲካ ሥርዓት እንዳይመሰረት እንቅፋት የሚሆኑት የውጪ ኃይሎች ማለት ከመንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን፤ በመንግሥት መዋቅር ሥር ውስጥ ሆነውም ግጭቶችን በማባባስ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ጉዞ ለማስተጓጎል ሙከራ እያደረጉ ያሉ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን።

እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ከዚህ በፊት ማኅበተሰቡን ሲበድሉ የነበሩና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢመጣ ማኅበረሰቡ ሥልጣን እንደማይሰጣቸው ያረጋገጡ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች የሚያባብሱት ግጭት ራሳቸውን ችግር ውስጥ ከመክተቱ በፊት፣ ራሳቸውን አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት እንዲያቆሙ ነው መልዕክት ያስተላለፍነው።

እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው?

አቶ ናትናኤል፦ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ኃይሎች ናቸው።

በመግለጫው ለግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸው ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሚዲያዎችን የተመለከተ ሀሳብ አንስታችኋል። የለያችኋቸው ሚዲያዎች አሉ?

አቶ ናትናኤል፦ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ነው የጠየቅነው። ይህ አካል በጠየቀን ጊዜ አሁንም በማስረጃ አስደግፈን የምንሰጥ ይሆናል።

ኢዜማ መግለጫ ከማውጣት ባሻገር በተግባር ምን እየሠራ ነው?

አቶ ናትናኤል፦ በሚቀጥለው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረን አሸንፈን የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ አደረጃጀታችንን በማስፋትና በማጠናከር ሂደት ላይ ነው የምንገኘው። በየጊዜው በምርጫ ወረዳዎቻችን ባደራጀንባቸው ቦታዎች ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠን፤ አደረጃጀት በሌለባቸው ቦታዎች ደግሞ ተደራሽነታችንን እያሰፋን እየሄድን ነው።

የፖሊሲ አማራጭ የሆኑ ዶክመንቶችን እየቀረጽን ነው የምንገኘው። ከዚህ ባለፈ ግን ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ነው። አባላቶቻችን እና አባላቶቻችን የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ያሉ የማኅበረሰብ አካላትን ከማንኛውም ሰላምና መረጋጋትን ከሚያውክ ተግባር ራሳቸውን እንዲያቅቡና እንዲከላከሉ፤ ማኅበረሰቡንም አስተባብረው እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ እያስተባበርን፣ እያስተማርን፣ እያደራጀን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለማቆየት፣ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው የሙያ ማኅበራት፣ የሀይማኖት ተቋሞች፣ መንግሥት እና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ውይይት ማድረግ አለብን ብለን እናስባለን። ያንን ውይይት በቅርቡ አዘጋጅተን የምናደርግ ይሆናል።