የሽንት ቤት ውሃ ለመጠጣት የተገደዱት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ከሊቢያ ስደተኞች ማጎሪያ ወጡ

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, UNHCR TWITTER PAGE

ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በሊቢያ መንግሥት ይዞታ ስር ካለው የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ወጡ።

ከስደተኞቹ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን መሆናቸውም ተገልጿል።

በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ ከሚገኘው የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ለመውጣት የተገደዱበትም ዋነኛው ምክንያት በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው እንዲሁም ከሽንት ቤት ውሃ ለመጠጣት በመገደዳቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ስደተኞቹ ለአንድ ዓመት ያህል በቂ ምግብ እንዲሁም ውሃ አለማግኘታቸው ለኃላፊዎቹ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምላሽ ያልተሰጣቸው ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለትም ጥቅምት 18/2012 ዓ.ም የማጎሪያው ጠባቂዎች ከፈለጋችሁ መውጣት ትችላላችሁ ብለው በሩን እንደከፈቱላቸው ቢቢሲ ያናገራቸው ስደተኞች ተናግረዋል።

ቄስ ዮውሃንስ ጎበዛይና ተክለብርሃን ተክሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ለዓመት ያህል እንደቆዩና ስደተኞቹ በምግብ እጦት በርሃብ ሲሰቃዩ እንዲሁም በበሽታ ሲጠቁ እንዳዩ ተናግረዋል።

"ባለፉት ሳምንታት የሚጠጣ ውሃ አልነበረም እናም ከሽንት ቤት ውሃ እየጠጣን ነበር" በማለት ቄስ ዮውሃንስ ተናግረዋል።

የታመሙ ሰዎችንም ከስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ተሸክመው ለሦስት ሰዓታት ያህል በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ትሪፖሊ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ማዕከል ደርሰናል ብለዋል።

በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት ቢሮም ስደተኞቹ ማዕከላቸው መድረሳቸውን አረጋግጧል።

በደቡባዊ ትሪፖሊ የሚገኘው የአቡ ሳሊም የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከል ከስምንት መቶ በላይ ስደተኞች እንዳሉበት ይታመናል።

በሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት እነዚህ የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከላት ለስደተኞቹ በቂ ባለመሆናቸው እንዲዘጉም ጥሪ አቅርቦ ነበር። እነዚህንም ማዕከላት "አሰቃቂ" ሲልም ገልጿቸው ነበር።