ኢትዮጵያና ግብፅ በአሜሪካ ለውይይት እንጂ ለድርድር አይገናኙም ተባለ

ታላቁ የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Grand Ethiopian Renaissance Dam

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት ግብፅ አሜሪካ ታደራድረን በሚል ያቀረበችውን ሃሳብ ኢትዮጵያ አልቀበልም ማለቷ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድና የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከቀናት በፊት በሩሲያ፣ ሶቺ መገናኘታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሦስተኛ ወገን ቢገባ ምንም ችግር እንደሌለው ገልፀው ነበር።

ዛሬም ኢትዮጵያና ግብፅ በመጭው ህዳር ወር ማብቂያ ላይ ዋሽንግተን ላይ ድርድር አዘል ውይይት እንደሚያደርጉ የግብፅን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጥቀስ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አሜሪካም ሩሲያም የማደራደር ፍላጎት እንዳላቸውና እርግጥም ለኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ባቀረበላቸው ግብዣ መሰረት የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ህዳር ላይ አሜሪካ ላይ ለመገናኘት መስማማታቸውን፤ ነገር ግን ለድርድር ሳይሆን ለውይይት ብቻ እንደሆነ የቢቢሲ ምንጮች ይገልፃሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ረፋዱ ላይ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ የሰጠ ሲሆን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸውም ሶስቱ አገራት ለውይይት ዋሽንግተን እንደሚገናኙ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች የቴክኒካል ስብሰባው እንዲቀጥል ተስማምተዋል። ምንጮቹ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አቋም አሁንም "የድርድር ነገር ገና ነው" የሚል ነው።

"ሁለቱ መሪዎች የቴክኒካል ቲሙ ሥራውን ይቀጥል ልዩነት ካለ እኛ እየተገናኘን እንፈታለን ነው ያሉት" ሲሉም ያክላሉ።

ምንጮቹ እንደሚሉት ወደ ድርድር ለመሄድ ፤ መጀመሪያ አገራቱ አደራዳሪ ያስፈልገናል ወይ? ድርድሩ በምን ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩረው? በሚሉ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው።

ቀጥሎም የአደራዳሪው ኃላፊነት ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ወስነው አደራዳሪውን በጋራ መምረጥ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ድርድር ሊኬድ አይቻልም።

ወደ ድርድር መሄድ ራሱ ቀላል እንዳልሆነና የራሱ አካሄድ እንዳለውም ያስረዳሉ።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ፤ ከዲፕሎማሲ አንፃር የአሜሪካን ላወያያችሁ ጥያቄ አለመቀበል ከባድ ስለሚሆን ኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር ነገሮችን እንደምታስኬድ አመልክተዋል።