ትዊተር የትኛውንም የፖለቲካ ይዘት ያለው ማስታወቂያ ሊያግድ ነው

የትዊተር የበላይ ኃላፊ ጃክ ዶርሴይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትዊተር በመላው ዓለም የፖለቲካ ይዘት ያላችው ማስታወቂያዎችን ሊያግድ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ማስታወቂያዎቹ ከሚፈለገው ቦታ መድረስ እና ተደራሽ መሆን ያለባቸው በራሳቸው እንጂ በገንዘብ ተገፍተው መሆን እንደሌለበት አስታውቋ ኩባንያው።

"ለንግድ ተቋማት በበይነ መረብ ማስተዋወቅ አቻ የሌለው የማስታወቂያ ስልት ቢሆንም ፖለቲካ ላይ ሲመጣ ግን የራሱ አደጋዎች አሉት" ሲሉ የተናገሩት የድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ጃክ ዶርሴይ ናቸው።

በቅርቡ ተቀናቃኛቸው ፌስ ቡክ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን እንደማያግድ ገልጾ ነበር ።

ይህ ዜና በ2020 ምርጫ በሚወዳደሩ በአሜሪካውያን ፖለቲከኞች ዘንድ ጎራ ፈጥሯል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዳግም ምርጫ ዘመቻ አስተዳደር የሆኑት ብራድ ፓርስኬል ፣ እገዳው " ትራምፕንና ወግ አጥባቂዎችን ዝም ለማሰኘት በግራ ዘመሞች የተወሰደ ርምጃ" ሲሉ ገልፀውታል።

ነገር ግን የጆ ባይደን የምርጫ ዘመቻ ቃል አቀባይ የሆኑት ቢል ሩሶ " በገንዘብና ለዲሞክራሲያችን ባለን ታማኝነት መካከል ምርጫ ሲደቀን ቢያንስ ለአንድ ጊዜ እንኳ ገንዘብ ማሸነፍ እንደማይችል ማወቅ አበረታች ነው" ብለዋል።

እርምጃውን በተመለከተ የፌስ ቡክ መስራች የሆኑት ማርክ ዙከርበርግ የኩባንያውን ፖሊሲ ደግፎ ተናግሯል።

" በዲሞክራሲ ውስጥ የግል ኩባንያዎች ፖለቲከኞችን ወይንም ዜናን ቅድመ ምርመራ ሊያደርጉ ይገባል ብዬ አላምንም" ሲል ከጋዜጠኞች ጋር በስልክ በነበረው ውይይት ላይ ገልጿል።

የቲውተር እገዳ ከ22 ቀን በኋላ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን ዝርዝሩ ህዳር ወር አጋማሽ ላይ ይወጣል ተብሏል።

በበይነ መረብ የሚቀርቡ የፖለቲካ ማስታወቂያዎች "ሲቪክ ማሕበረሰቡ ለሚያደርገው ውይይት ፈተና" መሆኑን የትዊተር የበላይ ኃላፊ በትዊተራቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

ተጋርጠዋል ካሏቸው አደጋዎች መካከልም "መልዕክቶችን በማሽን በታገዘ ሁኔታ ለተወሰነ ሰዓት አቆይቶ መልቀቅ፣ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በትንንሹ ከፋፍሎ ሳይቀር ተደራሽ ማድረግ፣ በአግባቡ ያልተፈተሸ አሳሳች መረጃ፣ ሐሰተኛ ዜናዎች" ናቸው።

" ታማኝ አይለም" ያሉ ሲሆን " ለኛ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ እያስተላለፉ በስርዓታችን ላይ ሲጫወቱ፣ ሰዎች ማስታወቂያዎቻቸውን እንዲያዩላቸው ሲከፍሉን፣ የሚፈልጉትን ማለት ሲችሉ ጠንክረን እየሰራን ነው ማለት ከባድ ነው" ብለዋል።

ይህ አዲስ ፖሊሲ በስልጣን ላይ ያሉ የምርጫ ተወዳዳሪዎችን እደግፋል የሚል ትችት የቀረበበት ሲሆን ለዚህም መልስ ሲሰጡ "በርካታ ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ያለ ፖለቲካ ማስታወቂያዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ግለሰቦች ይደርሳሉ" ብለዋል።

የመራጮች ምዝገባ ማስታወቂያዎች በዚህ እገዳ የተነሳ አይጎዱም ሲሉ አስታውቀዋል።