በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ የአረብ አብዮት ሊቀሰቀስ ይሆን?

ኢራቃውያን የተቃውሞ ሠልፈኞች የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ አድርገው ሲያሳዩ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

በመካከለኛው ምስራቅ፣ ኢራቅን ጨምሮ፣ መንግሥትን የሚቃወሙ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

የመካከለኛው ምስራቅ ወደ አዲስ የአረብ አብዮት እየተሸጋገረ ይመስላል።

በኢራቅ የተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሞተዋል፣ በሊባኖስ የተቃውሞ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ሰዎች ሀገሪቷን ቀጥ አድርገዋት ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ አል ሃሪሪ እንዲወርዱ ሲጠይቁ ተደምጠዋል።

ባለፉት ሳምንታት ደግሞ የግብፅ ደህንነት ኃይል በፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙ ሰልፈኞችን በትኗል።

ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና ግብፅ በርካታ ልዩነት ቢኖራቸውም የተቃዋሚዎች የቁጣ ምክንያት ተመሰሳይ ነው። ይህ ቁጣ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ አረብ ሀገራት ያሉ ሚሊየኖች፣ በተለይ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ከፍ ያለ የቁጣ ስሜት ነው።

በዚህ ቀጠና ባሉ ሀገራት ካሉ ህዝቦች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች እንደሆነ ይገመታል።

ወጣቶች ለአንድ ሀገር ወሳኝ ኃይሎች ናቸው። ይህ ግን የሚሆነው ምጣኔ ኃብቱ፣ የትምህርት ስርዓቱ እና የሀገሪቱ የተለያዩ ተቋማት የወጣቶቹን ፍላጎት ለማስጠበቅ በአግባቡ ሲሰሩ ነው።

በእነዚህ የአረብ ሀገራት ግን ይህ እየሆነ አይመስልም።

በሊባኖስ፣ ኢራቅ እና በቀጠናው ባሉ ሌሎች ሀገራት ወጣቱ ስራ አጥ በመሆኑ ስር የሰደደውን ሙስና ሲመለከት በቀላሉ ይቆጣል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሙስና

በእነዚህ ሀገራት ከተነሱ ቁጣዎች ሁለቱ ሙስናና ስራአጥነት የቀሰቀሳቸው ናቸው።

እንደ ዓለም ዓቀፉ ሙስናን አመላካች ተቋም ከሆነ በዓለማችን ሙሰኛ ሀገራት መካከል በቀዳሚነት የምትገኘው ኢራቅ ናት። ሊባኖስ ከኢራቅ የምትሻለው በትንሹ ነው።

የቢቢሲ መካከለኛው ምስራቅ ኤዲተር ሙስና የተጠቂዎቹን ተስፋና ምኞችት እምሽክ አድርጎ የሚበላ ካንሰር ነው ይላል።

እሱ እንደሚያስቀምጠው በሙስና በተዘፈቀ ስርዓት ውስጥ ያሉ እና የሚከስሩ ግለሰቦች፣ ተምረው ስራ ሲያጡና ወደ ኪሳቸውም ወደ አፋቸውም የሚያደርሱት ቁራሽና ሰባራ ሳንቲም ሲያጡ በጣም በፍጥነት ይቆጣሉ።

በተለይ ደግሞ የመንግሥት መዋቅሩ፣ የሕግ አስከባሪና የጸጥታ አካላት በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ሲገኙ የስርዓቱ መውደቅ ማሳያዎች ናቸው።

በሊባኖስም ሆነ በኢራቅ ሰልፈኞች መንግሥት ስልጣኑን እንዲለቅ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የመንግሥት መዋቅሩ እንዲለወጥና በሌላ እንዲተካ ይፈልጋሉ።

ሠልፈኞች ላይ መተኮስ

በኢራቅ ሰልፈኞቹ ስራ አጥነትና ሙስናን እያነሱ መንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የጸጥታ አካላት ጥይት በመተኮስ በትነዋቸዋል።

በኢራቅ በአሁኑ ሰዓት ያለው ሰልፍ መሪ አልባ ይመስላል።

ነገር ግን መንግሥት ሰልፉ በተጠናከረ ቁጥር የራሱን መሪ ይወልዳል የሚል ስጋት አለው።

ሠልፈኞቹ በባግዳድ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለስልጣናት፣ ኢምባሲዎች የሚኖሩበትንና ትልልቅ የመንግሥት ቢሮዎች የሚገኙበትን አካባቢ ለተቃውሟቸው ማዕከል አድርገዋል።

በባግዳድ የተጀመረውን ሰልፍን ተከትሎ ወዲያውኑ ማታ ቅዱስ ከተማችን ወደ ሚሏት ካራባላ ተዛምቷል።

የተቃውሞ ሰልፉ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከጸጥታ አካላት በሚተኮሱ ጥይቶች የሚሞቱና የሚቆስሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይነገርም የሞቱ እንዳሉ ግን ማወቅ ተችሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከኢራቅ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ወታደሮች የኢራቅን ሰንደቅ ዓላማ ትከሻቸው ላይ ለብሰው ታይተዋል። ይህም በወታደሩ ዘንድ ሰልፈኞቹን የመደገፍ አዝማሚያ መኖሩን ያሳያል ይላል የቢቢሲ የመካከለኛው መስራቅ ከፍተኛ አዘጋጅ።

ያልተጠናቀቀ የቤት ሥራ

በሊባኖስ የተቃውሞ ሰልፉ የተጀመረው በወርሃ ጥቅምት አጋማሽ ላይ መንግሥት ትምቧሆ፣ የዋትስ አፕ ጥሪዎችና ነዳጅ ላይ ታክስ ለመጨመር ማሰቡን ሲናገር ነበር።

መጀመሪያ ሰልፉ በሰላም እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ግጭቶች መከሰት ጀመሩ።

እኤአ በ2011 የተጀመረው የአረብ አብዮት ያላለቀ የቤት ሥራ ይሆን? ሲል የሚጠይቀው የቢቢሲ የመካከለኛው መስራቅ ከፍተኛ አዘጋጅ፣ በ2011 የተካሄደው የአረብ አብዮት የሚፈለገውን ነፃነት አላመጣም ይላል። ዜጎች አንደሚፈልጉት ከጨቋኝ መንግሥታቶቻቸው አልተላቀቁም ሲልም ሀሳቡን ያጠናክራል።

ይሁን እንጂ በእነዚህ ሀገራት አሁንም የአብዮቱ ትኩሳት ይሰማል። ሶሪያ፣ የመን እንዲሁም ሊቢያ በጦርነት ይታመሳሉ። ግብጽ ውስጥ ጠንካራ የደህንነት ቁጥጥር ይታያል።

አሁንም ግን የ2011 አብዮት የቀሰቀሰው ብሶት በአንዳንድ ሀገራት እንደውም በባሰ ሁኔታ ባለበት አለ።

በሙስና የተበላሸ የመንግሥት አስተዳደር ከፍተኛ ስራ አጥ ባለባቸው ሀገራት ለሚገኙ ወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር አቅሙ በመዳከሙ ወጣቶቹን እንደ እሳት ከሚንቀለቀለው ቁጣቸው እና ከሚያሰሙት ተቃውሞ ሊያቆማቸው አልተቻለውም።