ባለቤቷ በቆዳ ቀለሟ የተሳለቀባት ህንዳዊት ራሷን አጠፋች

የህንዳዊት ሙሽራ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለቤቷ በቆዳ ቀለሟ ምክንያት አዘውትሮ ያንጓጥጣት የነበረ የ21 ዓመቷ ህንዳዊት ራሷን ማጥፋቷን ፖሊስ ገለጸ።

ራጃስታን የተባለው ግዛት ፖሊሶች እንዳሉት፤ የወጣቷ አባት ለልጃቸው ሞት ባለቤቷን ተጠያቂ አድርገዋል። ባለቤቱን በጥቁር የቆዳ ቀለሟ ምክንያት ያንጓጠጠው ግለሰብ ላይ ክስም ተመስርቷል።

አባትየው ለፖሊስ እንደተናገሩት፤ ግለሰቡ በተደጋጋሚ በልጃቸው ጥቁር የቆዳ ቀለም እየተሳለቀ ያሸማቅቃት ነበር።

ፖሊስ ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገረው፤ ግለሰቡ እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋለም።

በርካታ ህንዳውያን ቀላ ያለ የቆዳ ቀለም ከጥቁር "የተሻለ እና የሚበልጥ" እንደሆነ ያምናሉ። ከዚህ ቀደምም ሌሎች ህንዳውያን በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በሚደርስባቸው መገለል ራሳቸውን አጥፍተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2014 አንዲት የ29 ዓመት ሴት ባለቤቷ በቆዳ ቀለሟ መሳለቁን ተከትሎ ራሷን አጥፍታለች። በ2018ም የ14 ዓመት ታዳጊ በክፍል ጓደኞቿ "ጥቁር ስለሆንሽ አስቀያሚ ነሽ" በመባሏ ራሷን አጥፍታለች።

ታዳጊ ሴቶች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ትምህርት ቤት ውስጥ መገለል ይደርስባቸዋል። የእድሜ እኩዮቻቸው መሳለቂያም ያደርጓቸዋል። ቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ቀላ ላሉ ልጆቻቸው ያዳላሉ።

በመገናኛ ብዙሀን ሽፋን የሚሰጣቸው ታዋቂ ተዋናዮችና ሞዴሎች ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ናቸው። ጥቁር ሰዎችን አስቀያሚ አድርገው የሚስሉ ማስታወቂያዎች በሕግ የተከለከሉ ቢሆንም፤ ለቀይ ሰዎች የሚያደላው አመለካከትና ሥርዓት ሙሉ በሙሉ አልተለወጠም።