ኡጋንዳ የጠፉት ኤርትራውያን ኳስ ተጫዋቾች ስጋት ላይ ነን አሉ

ኤርትራውያኑ ኳስ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/ONE DAY SEYOUM

ኡጋንዳ ውስጥ የጠፉት አራት ኤርትራውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ስጋት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ። ባለፈው ወር በደቡብ ምዕራብ ኡጋንዳ ጂንጋ ከተማ ከሆቴላቸው የጠፉት የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦብናልም ብለዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑን ትተው ኡጋንዳ ውስጥ በመጥፋታቸው ድረ ገጽ ላይ ማስፈራሪያዎች እየደረሷቸው እንደሆነ ተጫዋቾቹ ገልጸዋል። የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ከ20 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ላይ መሰናበቱ ይታወሳል።

ተጫዋቾቹ ታፍነው ወደ ኤርትራ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ስጋት እንደገባቸው ገልጸው፤ ከኡጋንዳ አስወጡን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተጫዋቾቹ አንዱ፤ "ስለኛ ግድ የሚሰጠው አካል ካለ ከዚህ አገር እንዲያወጣን እንለምናለን። በየሳምንቱ ከቤት ቤት እየቀየርን፣ እየተሽሎኮሎክን እየኖርን ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ተጫዋቾቹ ወደ ኤርትራ ከተመለሱ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, FUFA

አሜሪካዊ ጠበቃቸው ኪምበርሊ ሞተሊ እንዳሉት፤ ተጫዋቾቹ ኡጋንዳ ውስጥ እየተፈለጉ እንደሆነ ሰምተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድኦ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ጥገኝነት ቢጠይቁም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙም ጠበቃዋ ተናግረዋል።

ተጫዋቾቹ እንዳሉት፤ ሰዎች ስለሚያውቋቸውና ሊለይዋቸው ስለሚችሉ ከቦታ ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻሉም። ሕይወታቸውን እየገፉ ያሉትም ከበጎ ፍቃደኞች በሚያገኙት እርዳታ ነው።

ኤርትራ በተሳተፈችባቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ኤርትራውያን ተጫዋቾች ሲጠፉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።