ሦስቱ ሃገራት በዋሽንግተን ምን ተስማሙ?

@realDonaldTrump Image copyright @realDonaldTrump

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ አሞላል ሂደትን በተመለከተ ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይቶች ውጤት አልባ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

በዚህም ከግደቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለው አለመጋባባት እየጎላ መጥቷል።

ትናንት የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የልዑክ ቡድናቸውን ይዘው አሜሪካ ከደረሱ በኋላ በጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት አድርገው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

የጋራ መግለጫው ምን ይላል?

በውይይቱ ላይ ከሶስቱ ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባሻገር የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ተሳታፊ ነበሩ።

የሶስቱ ሃገራት ሚንስትሮች በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሁሉንም ፍላጎት በሚያረካ መልኩ በትብብር እና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ጽኑ አቋማቸውን ገልጸዋል ይላል ትናንት ምሽት በዋሸንግተን የወጣው መግለጫ።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ በየውሃ ሚንስትሮች ደረጃ የሚደረግ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማካሄድ የተስማሙ ሲሆን፤ የዓለም ባንክ እና አሜሪካ ድጋፍ እንዲሰጡ እና በውይይቶቹ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን መግለጫው ያትታል።

በተጨማሪም ሚንስትሮቹ ጥር 6 2012 ዓ.ም. ድረስ ከስምምነት ለመድረስ እንደሚሰሩ እና ኅዳር 29 እና ጥር 4 ዳግም በዋሽንግተን ለመገናኘት እና ሂደቱን ለመገምገም ቀጠሮ ይዘዋል።

እስከ ጥር 6 2012 ዓ.ም. ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ በ2008 ተፈርሞ የነበረው የጋራ አቋም መግለጫ አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።

ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ አቋሟን ትቀይር ይሆን?

በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ

የ2008ቱ ጋራ አቋም መግለጫ አንቀጽ 10 ምን ይላል?

ስምምነቱ የተፈረመው በሱዳን ካርቱም ሲሆን፤ የመርሆ መግለጫ አንቀጽ 10

ሶስቱ ሃገራት በአተረጓጓመ ወይም አተገባባር ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በመልካም መንፈስ ላይ ተመስረተው በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ። ሶስቱ አካላት አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ቢሳናቸው፤ አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩ ለየ ሃገራትቱ መሪዎች ወይም ለርዕሳነ ብሔሮቻቸው ሊያሳውቁ ይችላሉ ይላል።

የውሃ ሚንስትሩ ሲሌሺ በቀለ (ዶ/ር) የሶስቱ ሃገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች ውይይት እንዲያደርጉ ከመግባባት መደረሱ እንዳስደሰታቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

የዋሽንግተኑ ውይይት፡ ድርድር ወይም ውይይት?

በትናንት ውይይት አሜሪካ እና የዓልም ባንክ ተሳትፎ ማድረግ እና በቀጣይ ውይይቶች ላይም በድጋፍ ሰጪነት እና በታዛቢነት በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አልጠፉም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ወደ ዋሽንግተን የምታቀናው ለውይይት እንጂ ለድርድር እንዳልሆነ ገልጿል።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?

"የተርባይኖች መቀነስ በሚመነጨው ኃይል ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም" የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው የአሜሪካ ግምዣ ቤት ሚንስትር ስቲቭ ማቺን ባደረጉት ግብዣ የሶስቱ ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ወደ ዋሽንግተን ማቅናታቸውን ይጠቁማሉ።

"አሜሪካ ይህን ጥሪ ያቀረበችው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ወዳጅ ሃገር ስለሆነች ነው" ያሉ ሲሆን አሜሪካም የአደራዳሪ ሚና እንደሌላት ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ እና የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የሶስቱ ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በዋሽንግተን የከትሙት ለድርድር እንደሆነ በዘገባዎቻቸው ላይ አመላክተው ነበር።

ኢጂፕት ቱደይ የተባለው በእንግሊዘኛ የሚታተመው ጋዜጣ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ጋዜጣ የሆነው ገልፍ ኒውስ 'ወደ ድርድር የሚወስደው ወይይት' በአሜሪካው ግምዣ ቤት ሚንስትር ቢሮ ይካሄዳል ሲሉ ዘግበው ነበር።

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ መስከረም 23 እና 24 በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የተደረገውን የሦስትዮሽ ምክክር ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል።

የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ፤ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ጥሪ አቅርበው ነበር።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት እንደ አውሮፓውያኑ በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል መግለጿ የሚታወስ ነው።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን የተካሄደው ውይይት ውጤታማ እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጠቅሰው ነበር።

ለምን ወደ አሜሪካ?

በናይል ጉዳይ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉት ዶ/ር ያእቆብ አርሳኖ ግብፅና ኢትዮጵያ በአሜሪካ ለመገናኘታቸው ምክንያት ሊሆን የሚችለውን ያስቀምጣሉ።

እንደ እሳቸው እምነት የአሜሪካ ላወያያችሁ ግብዣ በሶስቱ አገራት በተለይም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል አለመግባባት እንዳይፈጠር ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ለማድረግ ነው።

"ምክንያቱም ግብፆች ብዙ ነገሮችን ጮክ አድርገው ቀውስ እንዳለ አድርገው ስለሚያወሩና ስለሚያስወሩ ወዳጅ አገሮች ይህ ያሳስባቸዋል። የአሜሪካም ላወያያችሁ ማለት ለዚህ ይመስለኛል" ይላሉ።

በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የናይል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ወንደሰን ሚቻጎ ኢትዮጵያ ዛሬም በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የአቋም ለውጥ እንዳላደረገች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ለመምከር ወደ አሜሪካ ማቅናቷ የግድቡን ጉዳይ በሰላምና በትብብር ለመፍታት ካላት ፍላጎት የመነጨ እንጂ ትልቅ የአቋም ለውጥ አድርጋ እንደማይሆን አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።

ለምን ወደ አሜሪካ? ለሚለውም አሜሪካ የኢትዮጵያም የግብፅም ወዳጅ ሃገር መሆኗን ነው አቶ ወንደሰን የሚጠቅሱት። አሜሪካ በዚህ መልኩ መንቀሳቀሷ ጉዳዩ ምን ያህል ቦታ እንደተሰጠው የሚያሳይ እንደሆነ፤ ይህም አዎንታዊ እንደሆነም ያክላሉ።

"ዞሮ ዞሮ ነገሩ መፈታት ያለበት ግድቡ እንዴት ይሞላ እና ግድቡ እንዴት ይስራ የሚሉ ነገሮችን ከቴክኒክ አኳያ በመመለስ ነው።" የሚሉት አቶ ወንደሰን ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ከዚህ ቀደምም በዚህ መልኩ አምስት ጊዜ መደራደራቸውን ያስታውሳሉ።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው የሁልጊዜ አቋማ ላይ ትልቅ ለውጥ ያለ አይመስለኝም በማለት የዋሽንግተኑ ውይይት የኢትዮጵያ አቋምን የሚቀይር እንዳልሆነ እምነታቸውን ይገልፃሉ።

በሌላ በኩል አሜሪካ ወዳጅነቷ ለግብፅ ያመዝናል፤ ስለዚህም ነገሮች እንደ ግብፅ ፍላጎት ይሄዳሉ የሚል ስጋቶች ስለመኖራቸው የተጠየቁት ዶ/ር ያእቆብ ለአሜሪካ ወሳኙ ብሄራዊ ጥቅሟ እንጂ ሌላ ነገር እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ በኩል የህዳሴው ግድብ ግንባር ቀደም ተደራዳሪ የነበሩትና አሁን የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽም በኢትዮጵያ በኩል ምንም የአቋም ለውጥ እንደሌለ ያረጋግጣሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች የቴክኒካል ስብሰባው እንዲቀጥል ተስማምተዋል። የኢትዮጵያ አቋም አሁንም "የድርድር ነገር ገና ነው" የሚል ነው።

"ሁለቱ መሪዎች የቴክኒካል ቲሙ ሥራውን ይቀጥል ልዩነት ካለ እኛ እየተገናኘን እንፈታለን ነው ያሉት" ሲሉም ያክላሉ።

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚሉት ወደ ድርድር ለመሄድ፤ መጀመሪያ አገራቱ አደራዳሪ ያስፈልገናል ወይ? ድርድሩ በምን ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩረው? በሚሉ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው።

ቀጥሎም የአደራዳሪው ኃላፊነት ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ወስነው አደራዳሪውን በጋራ መምረጥ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ድርድር ሊኬድ አይቻልም።

ወደ ድርድር መሄድ ራሱ ቀላል እንዳልሆነና የራሱ አካሄድ እንዳለውም ያስረዳሉ።

ከዲፕሎማሲ አንፃር የአሜሪካን ላወያያችሁ ጥያቄ አለመቀበል ከባድ ስለሚሆን ኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር ነገሮችን እንደምታስኬድ ያመለክታሉ አቶ ፈቅአህመድ።

የግብፅና የአሜሪካ የቀደመ ንግግር

ትናንት ከተካሄደው መርሃ ግብር ቀደም ብሎ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቢሮ አስታውቋል።

በውይይታቸው ወቅት ሳሚህ ሽኩሪ አሜሪካ እና ግብጽ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን ወዳጅነት አውስተዋል። የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ግብጽ ባለፉት አምስት ዓመታት የሶስቱንም ሃገራት ፍላጎት ከሚያረካ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት ስታድርግ መቆየቷን እና በኢትዮጵያ በኩል ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ውጤት አልባ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሳሚ ሽኩሪ እና ጃሬድ ኩሽነር የመካከለኛውን ምስራቅ እና የፍልስጤም ጉዳይን በማንሳት ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድረ-ገጽ አስነብቧል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ