የማርቲን ሉተር ኪንግ ስም ከመንገድ ላይ እንዲነሳ ተደረገ

የሉተር ኪንግ ስም ከመንገድ ላይ እንዲነሳ ተደረገ Image copyright Getty Images

የካንሳስ ከተማ ነዋሪዎች በጥቁር መብት ተሟጋቹ ስም እንዲጠራ ከተደረገው መንገድ ላይ ስያሜው እንዲነሳ አድርገዋል።

መንገዱ በማርቲን ሉተር ኪንግ ስም የተሰየመው ከወራት በፊት ቢሆንም የከተማዋ ነዋሪዎች ባደረጉት ምርጫ ስሙ እንዲነሳ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

'ዘ ፓሴዎ' በመባል ይታወቅ የነበረው የ16 ኪሎ ሜትር መንገድ በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን የሚኖሩበት ሥፍራ ላይ የተዘረጋ ነው።

በዓለም ዙሪያ በማርቲን ሉተር ኪንግ ስም የሚጠሩ 1000 ያህል መንገዶች እንዳሉ ይታመናል። የዘጠኝ መቶ ሃምሳ አምስቱ መንገዶች መዳረሻ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ነው።

ካንሳስ ከአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞች በዶ/ር ኪንግ የሚጠራ መንገድ የሌለባት ብቸኛዋ ከተማ ልትሆን ነው።

Image copyright Getty Images

ምንም እንኳ በከተማዋ ብዛት ያላቸው ጥቁር አሜሪካውያን ቢኖሩም መንገዱ ቅድሚያውንም ዘ ፓሴዎ ከተሰኘው ስም ወደ ማርቲን ሉተር ኪንግ የተቀረበት ሂደት ፍትሃዊ ነው ብለው አያምኑም። አልፎም ማርቲን ሉተር ኪንግን በዚህ መንገድ አይደለም መዘከር ያለብን ያሉ በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን እንዳሉ ተሰምቷል።

የካንሳስ ነዋሪዎች የማርቲን ሉተር ኪንግ ስም የተለጠፈበት የመንገድ ምልክት ይወርድልን ብለው ይመርጣሉ ተብሎ ባይታሰብም 70 በመቶ ያህል ድምፅ ሰጭዎች ስያሜው እንዲሳ ሲሉ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የዶ/ር ኪንግ ስም እንዲነሳ መወሰኑ ያንገበገባቸው ጥቁር አሜሪካውያን ግን አልጠፉም። ስያሜው በከተማዋ ለሚኖሩ ጥቁር አሜሪካዊ ታዳጊዎች ምሳሌ ይሆን ነበር ሲሉም ቁጭታቸውን ይገልፃሉ።

ጉዳዩን እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩትም አልጠፉም። አሁን ዶ/ር ኪንግን በመንገድ ስያሜ ሳይሆን በተሻለ ይዘት መዘከር እንችላለን ይላሉ።