በጃፓን ሴት ሠራተኞች መነጽር እንዳያደርጉ መከልከላቸው ጥያቄ አስነሳ

መነጽር ያደረገች ጃፓናዊት Image copyright Getty Images

አንዳንድ የጃፓን ተቋሞች ሴት ሠራተኞች ቢሮ ውስጥ መነጽር እንዳያደርጉ መከልከላቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ኒፖን ቲቪ እና ቢዝነስ ኢንሳይደር የተባሉ የጃፓን መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት፤ አንዳንድ ተቋሞች ልዩ ልዩ ምክንያት በማቅረብ ሴት ሠራተኞች መነጽር እንዲያወልቁ ያስገድዳሉ።

ይህም የጃፓን ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኗል። የአውሮፕላን ማረፊያ እና የውበት ሳሎን ሠራተኞች መነጽር ሳያደርጉ መሥራት ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ከገለጹት መካከል ናቸው።

በኮዮቶ ዩኒቨርስቲ የሶሾሎጂ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኩሚኮ ኔሞቶ፤ ሴቶች ሥራ ቦታ መነጽር እንዳያደርጉ መከልከል "ያረጀ ያፈጀ የጃፓን አሠራር ነው" ብለው ሕጉ አግላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ጃፓን ከቀበሌ መታወቂያ ያነሰች ሞባይል ሠራች

ዚምባብዌ 211 ሀኪሞችን ከሥራ አገደች

ተቃዋሚዎች የከንቲባዋን ጸጉር አስገድደው ላጩ

"ተቋሞች ሴቶችን የሚመዝኑት በሥራቸው ሳይሆን በገጽታቸው ነው" በማለትም ተናግረዋል።

ተዋናይትና ጸሀፊ ዩሚ ኢሺካዋ፤ በመሥሪያ ቤቶች ሴቶች "እንዲህ ይልበሱ" የሚል ድንጋጌ መኖሩን በመቃወም ፊርማ እያሰባሰበች ነው። ዩሚ የቀብር ሥነ ሥርዓት ስታስተባብር ታኮ ጫማ እንድታደርግ መገደዷን እንደ ምሳሌ ትጠቅሳለች።

ብዙዎች ዩሚ የጀመረችውን እንቅስቃሴ እየደገፉ ነው።

በተለይም የጃፓን አመራሮች፤ ተቋሞች ለሠራተኞቻቸው የአለባበስ ደንብ እንዲያወጡና እንዲያስፈጽሙ ማድረጋቸው ተቃውሞውን አባብሶታል።

ፕሮፌሰር ኩሚኖ እንደሚሉት፤ ሴት ሠራተኞች ታኮ ጫማ እንዲያደርጉ የሚያስገድደውን ፖሊሲ በርካቶች እየተቃወሙ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች