በድርቅ የተመታችው ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ የእርዳታ ምግብ አልቀበልም አለች

ሰሜን ኮሪያ በድርቅ ተመታች Image copyright KCNA

የሰሜን ኮሪያ መኸር ስብሰባ ካለፉት ዓመታት እጅጉን የቀነሰ መሆኑና ሃገሪቱ ከባድ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማት አንድ ቡድን ይፋ አደረገ።

መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ጄዎግላም የተሰኘው ድርጅት የሳተላይት ፎቶዎች እንደሚያሳዩት 'ሲሪያል ቦውል' በመባል የሚታወቀው ሰሜን ኮሪያ አካባቢ በድርቅ ተመቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ከ10 ሰሜን ኮሪያውያን አራቱ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፤ የዚህ ዓመት ሰብል ስብሰባም ከባለፉት አምስት ዓመታት ዝቅ ያለ ነው የሚል ዘገባ አውጥቷል።

የምግብ እጥረቱ እንዲባባስ የሆነው ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ያላትን የጦር መሣሪያ አስመልክቶ የተጣለባት ማዕቀብ ነው ተብሏል።

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ 70 በመቶ ያክል ዜጎች የምግብ 'ራሽን' ተጠቃሚዎች ናቸው። በምግብ እጥረቱ ምክንያት በፊት 550 ግራም በነብስ ወከፍ የነበረው የምግብ ዕድላ ከባለፈው ግንቦት ጀምሮ ወደ 300 ግራም ዝቅ ማለቱም ታውቋል።

ዋና ዋና የምግብ አምራች የሆኑት ሰሜን እና ደቡብ ሁዋንጋሄ እና ደቡብ ፒዮንግያንግ ሰብል ቢሰበሰብባቸውም መጠኑ እጅግ ዝቅ ያለ ነው ይላል ጄዎግላም የተሰኘው ድርጅት።

ሰሜን ኮሪያ ያጋጠማትን የምግብ እጥረት ተከትሎ ቻይና ጨምሮ ወዳጅ ሃገራት ድጋፍ እየደረጉለት ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደቡብ ኮሪያ 50 ሺህ ቶን የሩዝ እርዳታ ለሰሜን ኮሪያ ለማቅብ ብትፈልግም ሰሜን ኮሪያ አሻፈረኝ ብላለች።

Image copyright WFP

የድርቁ ዋነኛ ምክንያት ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብ ነው ተብሏል። አልፎም ሊንግሊንግ የተሰኘው ጎርፍ የቀላቀለ ዝናብ የእርሻ ቦታዎችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል።

ባለፈው መስከረም የተባበሩት መንሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት [ፋኦ] የለቀቀው መረጃ ሰሜን ኮሪያ የሩዝ እና በቆሎ ምርቷ ዝቅ ማለቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚጠብቁ አድርጓል ይላል።

ሰሜን ኮሪያ የምግብ እጥረት ደጋግሞ ይጎበኛታል። በ1990ዎቹ ሃገሪቱን በመታ ድርቅ እና የምግብ እጥረት በመቶ ሺዎች እንዳለቁ ይታወሳል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ