ሊቨርፑል ከሲቲ፡ ማን ያሸንፍ ይሆን?

ሊቨርፑል ከሲቲ Image copyright Getty Images

ሊቨርፑሎች የ30 ዓመት የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ጥማቸውን ለማርካት ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፤ ጊዜውም ከእነርሱ ጋር ነው። ሊጉን ዛሬ ከሚከናወነው ጨዋታ በፊት በአምስት ነጥብ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ።

ዛሬ አንፊልድ ላይ የሚደረገው ጨዋታ ለሊቨርፑል እጅግ ወሳኝ ነው። ችግሩ ወዲህ ነው [ለሊቭርፑል ማለት ነው]፤ የሚጫወቱት ከአምናው ዋንጫ ባለቤቶች ጋር ነው። ከማንቸስተር ሲቲ።

ሊቨርፑል እና ሲቲ አንፊልድ ላይ ዛሬ ምሽት 1፡30 ከመገናኘታቸው በፊት ቀያዮቹ ሊጉን በ31 ነጥብ ይመራሉ። ቅዳሜ ዕለት ጨዋታቸውን ያሸነፉት ሌይስተር ሲቲ እና ቼልሲ በእኩል 26 ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ናቸው። ሲቲ ደግሞ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ አራተኛ ነው።

የዩርገን ክሎፕ ልጆች ሲቲን ማሸነፍ ከቻሉ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 9 ይሆናል። ከሌይስተር እና ቼልሲ ደግሞ በ8 ነጥብ ርቀው ይቀመጣሉ።

ሊቨርፑሎች ባለፉት 49 የሊግ ጨዋታዎች የተሸነፉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ዛሬ ማሸነፍ ከቻሉ ደግሞ ታሪክ ይፅፋሉ።

ነገር ግን መንገዱ ለሊርፑል ጨርቅ ነው ማለት አይቻልም። አምና ሊቨርፒሎች ከ20 የሊግ ጨዋታዎች በኋላ ሲቲን በ10 ነጥብ ልዩነት እየመሩ ነበር።

በ2006 የፕሪሚዬር ሊግ ፍሊሚያ ዋንጫውን ሊያነሱ ጫፍ ደርሰው የነበሩት ሊቨርፑሎች በሰማያዊዎቹ ተሸንፈው [አምበሉ ስቲቨርን ጄራርድ ተንሸራቶ ወድቆ ጎል የተቆጠረበት አጋጣሚ] ቼልሲ ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም።

ተንታኞች የዛሬው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው ይላሉ፤ በተለይ ደግሞ ለቀያዮቹ። ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ወደኋላ የሚመልሰው ምንም ኃይል አይገኝም ነው የእግር ኳስ አዋቂዎች ትንታኔ።

የፕሪሚዬር ሊግ ሚዛን ከአርሰናል-ዩናይት-ቼልሲ ወደ ሊቨርፑል-ሲቲ አድልቷል። የሁለቱ ቡድኖች ፉክክርም ሁሌም ተጠባቂ ሆኗል። ይህ ደግሞ ለዚህ ዓመት ብቻ አይደለም፤ ለሚቀጥሉት ዓመታትም ጭምር እንጂ።

ብዙዎች የአሸናፊነቱን ግምት ለሊርፑል ሰጥተዋል። ይህ ደግሞ ሲቲ ባልታሰቡ ጨዋታዎች ነጥብ መጣሉና ወሳኝ ተጫዎቾች መጎዳታቸው ነው፤ በተለይ ደግሞ ግብ ጠባቂው ኤደርሰን። ቢሆንም ሲቲ ለሊቨርፑል ይተኛል ማለት ከባድ ነው። ለዚህ ነው ጨዋታው እጅግ አጓጊ እና ተጠባቂ የሆነው።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ውጤቶችን 'የሚተነብየው' ላውሮ ሊቨርፑል ጨዋታውን 2-0 ያሸንፋል ሲል ግምቱን አስቀምጧል። እርስዎስ?

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ