ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከደረሰው ግጭት ጋር በተያያዘ 13 ተማሪዎች መታሠራቸው ተነገረ

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, Woldiya University Facebook

ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከደረሰው እና የሁለት ተማሪዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ግጭት ጋር በተያያዘ 13 ተማሪዎች መታሠራቸው ተነገረ።

የሰሜን ወሎ ዞን ፀጥታ እና ሰላም ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ ሌሎች ተጨማሪ ተማሪዎች በግጭቱ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተጠርጥረው እየተፈለጉ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቅዳሜ ምሽት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና መምህር የብሄር መልክ በያዘው ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውን አረጋግጠውልን ነበር።

ትናንት የአማራ መገናኛ ብዙሃን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንኤ መኮንን በመጥቀስ ቅዳሜ ምሽት ግጭት የተከሰተው፤ ተማሪዎች በጋራ እግር ኳስ በቴሌቪዝን ተመልክተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት መሆኑን እና በዚህም ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን እና ስምንት ተማሪዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ዘግቦ ነበር። የሰሜን ወሎ ዞን ፀጥታ እና ሰላም ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ የአገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ መግባታቸውን እና ይሄም እርምጃ መረጋጋትን ማምጣቱን ለቢቢሲ ተናገግረዋል።

ኮሎኔል ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ዩኒቨርሲቲው "የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በፀጥታው ሁኔታ ስጋት ገብቷቸው ወደየቀያቸው ለመመለስ የፈለጉ ተማሪዎች እንደበሩ አልካዱም።

ነገር ግን ከአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የዞኑ አመራሮች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ከወልዲያ ከተማ ከንቲባ ጋር ውይይት በማድረግ ደህንነት ተሰምቷቸው ትምህርታቸውን አንዲቀጥሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ቢቢሲ ያነጋገረው ከሌላ ስፍራ ወደ ዩኒቨርሲቲው ያቀና ተማሪ ከሃገር ሽማግሌዎች አና የአካባቢው ነዋሪዎች አለንላችሁ እያሉን ቢሆንም ጥቃት አድራሾቹ ሲጋለጡ አላየንም ይላል።አሁንም ቢሆን ስጋት እንዳልተለየው የሚገልፀው ይሄው ተማሪ ወደትውልድ ቀዬው የመመለስ ፍላጎቱን እንዳልቀየረ ይናገራል።

የምስሉ መግለጫ,

ግጭቱን ተከትሎ የደህንነት ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት ሲሞክሩ መከልከላቸውን ተናግረዋል። [ፎቶ፡ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እሁድ ጠዋት]

እሁድ ዕለት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ተማሪ ለቢቢሲ "ትናንት [ቅዳሜ ምሽት] የተፈጸመውን አይተን እንዴት ነው ዶርም ውስጥ የምንተኛው?" ሲል ተናግሯል። ጨምሮም "ትናንት የተፈጸመው ዳግም ላለመከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም" በማለት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንዳይወጡ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቁሟል።

ትላንት [እሁድ] የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኘተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ በተማሪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት የብሔር ለማስመሰል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ ሲሉ ተደምጠው ነበር።

"በግጭቱ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩን አረጋግተነዋል። በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል። አልፎም አማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን ለይተን እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀስን ነው።" ብለው ነበር።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትናንት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን ክስተት ማውገዙም አይዘነጋም።

የክልሉ ምክት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲስ ትናንት ከሰዓት በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ፤ "አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ እና አስተሳሰቦቻቸውን በኃይል ህዝብ ላይ ለመጫን ጥረት እያደረጉ ነው" ብለዋል። አክለውም ለክስተቱ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ለፍርድ እንዲቀርቡ ከፌደራል እና ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር አብረው እንደሚሰሩ አሳውቀዋል።