ሞራሌስ የሜክሲኮን የፖለቲካ 'ጥገኝነት ልስጥዎ' ጥያቄ ተቀበሉ

ኤቮ ሞራሌስ Image copyright Reuters

ኤቮ ሞራሌስ ከቦሊቪያ ፕሬዘዳንትነት በፈቃዳቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ሜክሲኮ ያቀረበችላቸውን የፖለቲካ ጥገኝነት ልስጥዎ ጥሪ ተቀብለዋል። ሥልጣናቸውን በለቀቁ ማግሥት ሜክሲኮ ጥገኝነት ከፈለጉ እንደምትሰጣቸው መናገሯ ይታወሳል።

ቦሊቪያን ጥሎ መሄድ እንደሚያሳዝናቸው በትዊተር ገጻቸው የተናገሩት የቀድሞው ፕሬዘዳንት፤ 'በተሻለ ኃይል' ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

የሜክሲኮ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርሴሎ ኤብራርድ፤ ኤቮ ሞራሌስ የሜክሲኮ መንግሥት በሆነ አውሮፕላን መሳፈራቸውን አረጋግጠዋል።

ተቃዋሚዎች የከንቲባዋን ጸጉር አስገድደው ላጩ

አንድም ሴት የፓርላማ አባል የሌላት ሃገር

የቦሊቪያ መከላከያ ኃላፊ የአገሪቱ ወታደሮች ከሞራሌስ ደጋፊዎች ጋር የተጋጩትን ፖሊሶች እንዲደግፏቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በቦሊቪያ በተነሳው ግጭት ሳቢያ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አዲስ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እስከሚካሄድ የምክር ቤቱ ምክትል ኃላፊት አገሪቱን እንደሚያስተዳድሩ ታውቋል።

ሞራሌስ ሥልጣን የጨበጡት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2006 ነበር። ድህነትን በመዋጋትና የቦሊቪያን ምጣኔ ኃብት በማሻሻል ቢመሰገኑም፤ ሕገ መንግሥቱን በመጻረር የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘማቸው አስኮንኗቸዋል።

የሞራሌስ ደጋፊዎች መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሟል ሲሉ፤ ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ አምባገነን መሪ ከሥልጣን ወርደዋል ብለዋል።

ሞራሌስ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የፖርቲያቸው አባላትም ፓርቲውን ጥለው እየወጡ ነው።

አንድም ሴት የፓርላማ አባል የሌላት ሃገር

ኬሚካል ኢንጂነሩ ሊስትሮ በባህር ዳር

ምርጫ አካሂዶ በተለያየ ጽንፍ ላይ የሚገኙ ቦሊቪያውያንን ወደ አንድ መድረክ ማምጣት፤ በቀጣይ ሊነሱ ከሚችሉ ግጭቶች አገሪቱን ይታደጋታል።

የሜክሲኮ ግራ ዘመም መንግሥት ውስጥ ሞራሌስ ደጋፊዎች አሏቸው። ሞራሌስ ከሥልጣናቸው በተነሱበት ሂደት ውስጥ የአገሪቱ መከላከያ እጅ መኖሩ መፈንቅለ መንግሥት ያስብለዋል ሲሉ ሜክሲኮ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርሴሎ ኤብራርድ ተናግረዋል።

ሞራሌስ ባለፈው ወር የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈዋል መባሉን ተከትሎ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጫና ሲደረግባቸው ነበር።

ምርጫውን የታዘበው 'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ አሜሪካን ስቴትስ' ባደረገው ምርመራ ምርጫው መጭበርበሩን እንደደረሰበትና ውጤቱ መቀልበስ እንደሚገባው መማሳወቁን ተከትሎ ነገሮች ተባብሰዋል።

ሞራሌስ ሌላ ምርጫ ለማካሄድ ቢስማሙም በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ካርሊስ ሜሳ፤ ሞራሌስ ራሳቸውን ማግለል አለባቸው የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

የመከላከከያ ሠራዊቱ ኃላፊ ጄነራል ዊልያምስ ካሊማን፤ ሞራሌስ ከሥልጣን እንዲወርዱ ሲያሳስቡ ሁኔታው የበለጠ ተባብሷል። ሞራሌስ ከሥልጣናቸው የወረዱት በመፈንቅለ መንግሥት እንደሆነም ተናግረዋል።

የሞራሌስ ከሥልጣን መልቀቅ ተቃዋሚዎቻቸውን ያስፈነጠዘ ዜና ሲሆን፤ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሞራሌስ ከሥልጣን መልቀቃቸውን የዴሞክራሲ መስፈን ተምሳሌት ሲያደርጉት፤ የሩስያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ደግሞ ተቃዋሚዎች አገሪቱን እየናጧት ነው ብለዋል።

የኩባው ፕሬዘዳንት ሚጌል ዲያዝ ካነል፤ "ጸረ ዴሞክራሲያዊ እና በቅኝ ዘመሞች የተሸረበ መፈንቅለ መንግሥት ነው" ብለዋል። ሶሻሊስቶቹ ኒካራግዋና ቬንዝዌላም ሞራሌስን ደግፈዋል።

ስፔን በበኩሏ የአገሪቱ መከላከያ እጁን ማስገባቱ አስጊ ነው ብላለች።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ