"የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች ሕይወቱን ማዳን ይችሉ ነበር" የአቶ ገመቺስ ባለቤት ወ/ሮ መሰረት

ገመቺስ ታደሰ Image copyright FB irraa

'የኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ኃላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ በተደጋጋሚ ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ባለቤታቸው ወ/ሮ መሰረት ሁንዴሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ወ/ሮ መሰረት እንዳሉት፤ አቶ ገመቺስ ከዓመት በፊት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር። ይህን ተከትሎም አቶ ገመቺስ ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል።

ወ/ሮ መሰረት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አቶ ገመቺስ የዝውውር ጥያቄያቸውን ለኢትዮ ቴሌኮም አቅርበው ከተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር እየተጻጻፉ ነበር። አቶ ገመቺስ ከኢትዮ ቴሌኮም ባገኙት ምላሽ ደስተኛ እንዳልነበሩ የተናገሩት ባለቤታቸው፤ "የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች ሕይወቱን ማዳን ይችሉ ነበር" ብለዋል።

"በኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ ግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም" የነቀምቴ ፖሊስ አዛዥ

"ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ዋጋ ያላገኘሁበት ቢኖር ትምህርት ነው"

የአቶ ገመቺስን ግድያ እየመረመረ ያለው ቡድን አንድ ሰው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለቢቢሲ ገልጿል።

አቶ ገመቺስ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ. ም. በነቀምቴ ከተማ ውስጥ ጨለለቁ በተባለ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ መገደላቸው ይታወሳል።

ወ/ሮ መሰረት እንደሚሉት፤ በእለቱ አቶ ገመቺስ ከጓደኞቻቸው ጋር ቤት ውስጥ ሳሉ ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ ስልክ ተደውሎላቸው ነበር። "የደወለለት የሚያምነው ጓደኛው" ነበር የሚሉት ወ/ሮ መሰረት፤ አቶ ገመቺስ ስልክ ለማውራት ከቤት ከወጡ በኋላ የተኩስ ድምጽ እንደሰሙ ይናገራሉ።

"የተኩስ ድምጽ ሰምተን ስንወጣ ገሜን [ገመቺስን] መሬት ላይ ወድቆ አገኘሁት" ሲሉ የተከሰተውን ይገልጻሉ። ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለው ግለሰብ ለአቶ ገመቺስ ደውሎ የነበረው ሰው እንደሆነም ያክላሉ።

አቶ ገመቺስን ወደ ሆስፒታል እንደወሰዷቸው ተናግረው፤ "ሆስፒታል ከደረስን በኋላ በቂ አገልግሎት አልተደረገም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳምጠው ጋረደው፤ አቶ ገመቺስ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ከአንድ ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው እንዳለፈ አስታውሰው፤ "በአጭር ጊዜ ተገቢው ህክምና ተደርጓል" ብለዋል።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ አቶ ገመቺስ ቢያንስ አራት ጊዜ በጥይት መመታታቸውን እና አንድ ጊዜ ደግሞ በስለት መወጋታቸውን ተናግረዋል።

"ግራ እጁ ላይ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመቷል። ትከሻው ላይም በጥይት ተመቶ በብብቱ በስተግራ በኩል ጥይቱ ወጥቷል" ያሉ ሲሆን፤ ታፋቸው አካባቢ ሁለት ቦታ መመታታቸውን እና ጥይቶቹ የገቡበት እና የወጡበት ቦታ ይታይ እንደነበረም በወቅቱ ገልጸዋል።

ዶ/ር ዳምጠው እንደሚሉት ከሆነ፤ የአቶ ገመቺስ ሕይወት በፍጥነት እንዲያልፍ ያደረገው ደረታቸው ላይ በስለት መወጋታቸው ነው።

Image copyright Facebook

ወ/ሮ መሰረት እንደሚሉት፤ አቶ ገመቺስ ሕዳር 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ነቀምቴ ከተማ ውስጥ፣ ምሽት ላይ 'አስክ' በሚባል ትምህርት ቤት መኪናቸውን አቁመው ሲወጡ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር።

"ያኔ ክስተቱን ለፖሊስ ሪፖርት ብናደርግም ያገኘነው መፍትሔ አልነበረም" ብለዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት ከመገደላቸው አስቀድሞ ስጋት እንዳላቸው እንደገለጹም አክለዋል።

ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ጋር በተያያዘ 13 ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

"ሴት ተማሪዎችን ባጠቃላይ ተመርመሩ ማለት መፈረጅ ነው" የሕግ ባለሙያ

ከግድያ ሙከራው በኋላም ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ ማቅረባቸውን እንዲሁም ሌላ ሥራ እያፈላለጉ እንደነበረም ያስረዳሉ።

"ለኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሬሕይወት ታምሩ እዚህ መኖር ስጋት ውስጥ እንደጣለው ተናገሮ ነበር" የሚሉት የአቶ ገመቺስ ባለቤት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ቦታ እንፈልግልሀለን የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

"ቦታ እንፈልግልሀለን ቢሉም ከቃል ባለፈ ሊሳካ አልቻለም" ይላሉ።

የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ፤ አቶ ገመቺስ ዝውውር ጠይቀው እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ በምዕራብ ዞን ይሠሩበት ከነበረው አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው፣ አዲስ አበባ እንዲሠሩ እንደተነገራቸው እና አቶ ገመቺስ ግን እንዳልፈለጉ ተናግረዋል።

"ጥያቄውን ከአንድ ዓመት በፊት አቅርበው ነበር። እሳቸው የጠየቁት ቦታ እስኪገኝ አዲስ አበባ በሌላ ቦታ እንዲሠሩ ሥራ አስኪያጇ ፈቅደው ነበር። ውሳኔውን ግን አልተቀበሉም" ይላሉ።

አቶ ገመቺስ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ለምን ነቀምቴ ውስጥ ቆዩ? ስንል ባለቤታቸውን ጠይቀን፤ "በሁኔታዎች ተገዶ እንጂ ወዶ አልቆየም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሦስቱ ሃገራት በዋሽንግተን ምን ተስማሙ?

የኢትዮጵያዊቷ ህክምና መቋረጥ በደቡብ አፍሪካ አነጋጋሪ ሆነ

የሁለት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ገመቺስ፤ በኢትዮ ቴሌኮም ለአሥር ዓመታት ሠርተዋል። ወ/ሮ መሰርት "መንግሥት ችግሩን አይቶ ቢፈታ ኖሮ የገመቺስ ልጆች አባት አልባ አይሆኑም ነበር" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ