ኢትዮጵያ ወይስ ናይጄሪያ? የትዊተር አለቃ ለስድስት ወራት ሊኖርባት ያጫት ሃገር

ኢትዮጵያ ወይስ ናይጄሪያ? የትዊተር አለቃ የፈጠረው ክርክር Image copyright Teresa Kroeger

ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር-አምባ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆነው ጃክ ዶርሲይ ከሰሞኑ ወደ አህጉረ አፍሪካ ዓይኑን ጥሏል።

የትዊተር ተባባሪ ፈብራኪው ጃክ፤ በሚቀጥለው ዓመት ለስድስት ወራት ያክል ወይ ኢትዮጵያ አሊያም ናይጄሪያ መኖር እፈልጋለሁ ማለቱን ተከትሎ የማሕበራዊ ድር አምባ ተጠቃሚዎች ግምታቸውን ማስፈር ጀምረዋል።

አለቃ ጃክ ለስድስት ወራት ከሁለት ሃገራት በአንዷ መቆየት የሻተው የትዊተርን በአፍሪካ ተደራሽነት ለማስፋት ነው።

ናይጄሪያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ በርካታ ሕዝብ ያላት ሃገር ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛ ላይ ትገኛለች። በናይጄሪያ የብሪታኒያ አምባሳደር የሆኑት ካትሪዮና ሌይንግ ጃክ ናይጄሪያ ወይ ኢትዮጵያ ቆይታ ለማድረግ መወሰኑ ብዙም አያስገርምም ይላሉ።

የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራትን እየተዘዋወረ በመጎብኘት ላይ የሚገኘው ጃክ የቀድሞ የናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር ጠርተው እራት በጋበዙት ወቅት ነው ይህንን ዜና ይፋ ያደረገው።

ዜናውን ተከትሎ በተለይ ኢትዮጵያውያን እና ናይጄሪያውን የማሕበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚዎች ክርክር ገጥመዋል።

ዛሬ [ማክሰኞ] ጋና ከተማ አክራ የሚገኘው ጃክ የጋናውያን እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካውያን ተወዳጅ ምግብ የሆነውን ጆሎፍ ሊመገብ ሲሰናዳ የሚያሳይ ፎቶ በትዊተር ገፁ ለጥፏል።

ለአንድ ወራት ያክል በአህጉረ አፍሪካ ዝውውር የሚያደርገው ጃክ ዶርሲ ከጋና በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ያቀናል።

የ42 ዓመቱ አሜሪካዊ የኮምፒውተር ጠቢብ እና ሥራ ፈጣሪ 4.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ እንዳለው ይገመታል።