እሮብ ዕለት ድሬዳዋ ሰላም ርቋት መዋሏ ተሰማ

ቀፊራ

እሮብ ዕለት በድሬዳዋ ከተማ በተነሳ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰማ።

የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ተወካይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሚካኤል እንዳለ ለቢቢሲ እንደገለፁት በድሬደዋ በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትባቸው ቀበሌ 6፣ ቀፊራ ደቻቱና መጋላ ፣ በቀበሌ 05 ገንዳ አዳ፣ እንዲሁም ቀበሌ 09 ገንደ ጋራ የሚባሉ ቦታዎች ናቸው።

በድሬዳዋ ከጥቅምት 30 ጀምሮ ግጭት እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው ትናንትናና ዛሬም ግጭት ተቀስቅሶ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በስጋት የሚናጡት ዩኒቨርስቲዎች

ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ጋር በተያያዘ 13 ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የኢትዮጵያዊያንን ትዳር አከርካሪ እየሰበረ ያለው ምን ይሆን?

ዛሬ በተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛም መካከለኛም ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ሚካኤል ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሆስፒታል ሕክምና አግኝተው እየተመለሱ ነው ብለዋል።

ከፖሊስም ከሆስፒታልም የሞት አደጋ መድረሱን ለጊዜው መረጃ እንዳልደረሳቸው የተናገሩት ኃላፊው ግጭቱን ለማብረድ የፀጥታ መዋቅሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሚካኤል የግጭቱ ባህሪ ተለዋዋጭ እንደሆነና አንድ ቦታ በቁጥጥር ስር ሲውል ሌላ ቦታ አንደሚቀሰቀስና ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ያስረዳሉ።

ግጭቱ የብሔርና የሀይማኖት መልክ እንዲይዝ ሙከራዎች እንዳሉ የገለፁት ኃላፊው ጥፋተኞችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

አሁንም ቢሆን የተፈጠረው ግጭት ከጸጥታ መዋቅሩ በላይ አይደለም በማለት ከከተማው አስተዳደር የጸጥታ ኃይል በተጨማሪ ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ እንደተሰማራ ተናግረዋል።

ግጭቱንም ለመቆጣጠር ሁሉም በጋራ እየሰሩ መሆኑን በማስረዳት ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ ከሚገኙ ሐሰተኛ መልእክቶች ራሱን እንዲጠብቅ ተማጽነዋል።

የዛሬውን ግጭት መንስዔው ምንድነው የሚለውን ለማጣራት እየሰሩ መሆኑን በመግለጽ ዝርዝር ነገሮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በግጭቱ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለመናገር መረጃዎችን ማጠናቀር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ጥቅምት 30 በነበረው ግጭት ግን ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

ጥቅምት 30 የተፈጠረው ግጭት መንስኤ የሁለት ሰዎች አለመግባባት መሆኑን በመግለጽ ይህም ሠፈር ለይቶ ድንጋይ ወደ መወራወር ማደጉን ገልጸዋል።

አቶ ሚካኤል ዛሬ ማምሻውን ባደረሱን መረጃ በዛሬው ግጭት አንድ ግለሰብ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ለተጨማሪ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ከመላኩ ውጭ እስካሁን በግጭቱ ሕይወት አልጠፋም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ