"በአዲስ አበባና በባህር ዳር የተፈጸመው የሰኔ 15ቱ ግድያ ዕቅድ የጀመረው ከሚያዚያ ወር አንስቶ ነበር" ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሰኔ 15ቱ የከፍተኛ ባለስልጣናት እና የጦር መኮንኖች ግድያ ጋር በተያያዘ አጠናቅቄዋለሁ ያለውን መረጃ ይፋ አደረገ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ዛሬ [ረቡዕ] ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ የተለያዩ የቴክኒክ፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ግድያውን አቀነባብረውታል የተባሉት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ እና ሌሎች አጋሮቻቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩ ኮምፒውተሮችን፣ ፍላሽ ዲስኮችንና አምስት ተሽከርካሪዎችን ፈትሾ የተለያዩ የውጪ ሀገራት ገንዘብና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን መያዙን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ ይህንን መፈንቅለ መንግሥት ለማከናወን ዝግጅት የተጀመረው በሚያዚያ ወር መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሀኑ፣ ወንጀሉ በጄነራል አሳምነውና ለክልሉ ተቆርቋሪ ነን በሚሉ አክቲቪስቶች የተጠነሰሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንንም ለማሳካት ኢመደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችንና እንዲሁም ሽፍቶችን በማደራጀት ተከናውኗል ሲሉ ጨምረው አስረድተዋል።

በተለይ የክልሉና የፌደራል መንግሥት የተቃረኑ በማስመሰልና ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ በፓርቲው የተበደሉ በማስመሰል ሕብረተሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል ያሉትጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ይህንንም ሲሰሩ የክልሉ ስልጣን ያልሆኑ ሥራዎችንም ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንዲሁም ከአማራ ክልል 110 የሚሆኑ ሰዎችን በመሰብሰብ ለሰባት ሳምንታት የስለላ ስልጠና በመስጠት አሰማርተዋል ብለዋል።

ስልጠናው ስውር ጦርነት፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነት ላይ የሚያተኩር ነበር ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ለግለሰቦቹ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠናዎችም መሰጠቱን ተናግረዋል።

ስልጠናውን የወሰዱ ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ አሶሳ፣ አዋሳና አፋር የተሰባሰቡ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከልም ከመከላከያ ሠራዊት በሥነ ምግባር ጉድለት ጭምር የተባረሩት እንደሚገኙበት አስረድተው የልዩ ኃይሉ አባል በማድረግ ለተግባሩ ዝግጁ እንዲሆኑ ተሰርቷል ብለዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ በዋናነት የክልሉን ስልጣን ለመቆጣጠር የታቀደ መሆኑን የገለፁት አቶ ብርሃኑ፤ ከተሳካ በኋላ በዞንና በወረዳዎች ላይ ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ የተባሉ ባለሰልጣናት ላይ ተጨማሪ ርምጃ ለመውሰድ የታጠቀ ኃይል ተዘጋጅቶ እንደነበርም ተናግረዋል።

የጄነራሎቹን ግድያ በተመለከተ በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ "እርምጃ ከተወሰደባቸው በኋላ የመከላከያ ሠራዊቱ በየብሔሩ ይበታተናል፣ መፈንቅለ መንግሥቱንም ለማሳካት ቀላል ይሆናል በዚህም የፌደራል ስልጣንን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል" በሚል የተፈፀመ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በቅድሚያ ጄነራል ሰዓረ ሲመቱ በቦታው የእርሳቸውን ግድያ ተከትሎ ጄነራል ብርጀሃኑ ጁላ ሊገኙ ስለሚችሉ እርሳቸውም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ተነግሮ እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።

ጄነራል ብርሃኑ በስፍራው ባለመገኘታቸው የግድያው ሰለባ ሳይሆኑ ቀርተዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ይህንንም ለማድረግ ተመልምሎ ጎንደር ውስጥ የሰለጠነ ወታደር የባህር ዳሩ ድርጊት ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ ለጄነራል ሰዓረ ጥበቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ ደውሎ እንደነገረው ገልፀው ወታደሩም ጄነራል ሰዓረንና ጄነራል ገዛዒን እንደገደላቸው አብራርተዋል።

ለመፈንቅለ መንግሥቱ ማስፈፀሚያ ከመንግሥት በጀትና ከባለሃብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ ግልና የቡድን መሳሪያዎች ተገዝተዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በአጠቃላይ ባህር ዳር ላይ 3 ሻምበሎችን ከክልሉ ልዩ ኃይል ውጪ በማደራጀት በርዕሰ መስተዳድሩ፣ በአዴፓና በፓሊስ ጽህፈት ቤቶች፣ በክልሉ እንግዳ ማረፊያ፣ እንዲሁም በፖሊስ ኃላፊዎች ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙን አብራርተዋል።

በዚህም 15 ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች ደግሞ የመቁደሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በሰኔ 15 ወንጀል በባህር ዳር 200 በአዲስ አበባ ደግሞ 147 ሰዎች ተጠርጥረው ተይዘዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፣ 70 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶ እየተፈለጉ ሲሆን 31 ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው በማለት ቀሪዎቹ 39 ግለሰቦች ግን አለመያዛቸውን ገልፀዋል።

በባህር ዳር ደግሞ 47 ተጠርጣሪዎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ተደርጎ በአጠቃላይ 55 ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት መሆኑ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከተያዙት መካከል 5 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ወደ መሳሪያ ማዘዋወር የተቀየረ ሲሆን 61 ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ተወስኗል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ ነገር ግን 13 የሚሆኑት ቅድመ ምርመራ ክስ ስለተዘጋጀ በዚህ ሳምንት ይከሰሳሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።

ባህር ዳር ላይ 15 ተከሳሾች ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የተከሰሱ ሲሆን እነዚህም የሟቾች አጃቢዎችና የሥራ ኃላፊዎች ናቸው ተብሏል።

ምርመራውን ለማካሄድ የፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ የኢንፎርሜሽን ደህንነት፣ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት፣ የመከላከያ ሠራዊት ባለሙያዎች፣ የአማራ ክልል ፖሊስና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ መሳተፋቸው ተገልጿል።