እረፍት መውሰድ ያበዙት የፊሊፒንሱ መሪ ዱቴርቴ ጤናቸው ሳይቃወስ አልቀረም ተባለ

እረፍት ያበዙት ዱቴርቴ ጤናቸው ሳይቃወስ አልቀረም Image copyright EPA

የፊሊፒንሱ ፕሬዝደንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ ጠንካራ ሰብዕና እንዳላቸው ብዙዎች ያምናሉ።

'ቀጭው' የተሰኘ ቅጥያ የተሰጣቸውም እንዲሁ አይደለም። ወንጀለኞችን ከአገራቸው ፊሊፒንስ ለመጠራረግ ወደ ኋላ አለማለታቸው ታይቶ እንጂ።

ነገር ግን ወደ ሥልጣን ከመጡበት 2008 ጀምሮ እኒህ ሰው ጤና ይጎላቸዋል የሚሉ ወሬዎች ከዚህም ከዚያም ይሰሙ ነበር።

ከሰሞኑ ደግሞ ቃል-አቀባያቸው ፕሬዝደንት ዱቴርቴ የሦስት ቀናት እረፍት ወስደዋል ማለታቸውን ተከትሎ ከተማው ማጉረምረም ጀምሮ ነበር። ኋላ ላይ ግን ቃል-አቀባዩ እረፍት ሳይሆን ከመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ሊሠሩ አስበው ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

አሁን ፊሊፒኖዎችን አንድ ጥያቄ ሰቅዞ ይዟቸዋል። እውን የ74 ዓመቱ ዱቴርቴ ጤናቸው የተሟላ ነው? የሚል። እንዲህ እየሆኑማ ሊመሩን አይችሉም የሚሉም አልጠፉም።

ዱቴርቴ ጤና ናቸው ወይ? ሲል ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው ቃል-አቀባይ ሳልቫዶር ፓኔሎ «ኧረ እንደውም። እንዲሁ ራቅ ብለው መሥራት ስለፈለጉ እንጂ. . .» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ችግሩ ዱቴርቴ እረፍት ሲወስዱ የመጀመሪያቸው አለመሆኑ ነው። ብዙ ጊዜ በክብር የተጠሩበትን ዝግጅት ሲቀጡ ሰውዬው ምን ነካቸው? የሚል ጥያቄ መሰንዘሩ አልቀረም።

ባለፈው ዓመት ዶክተሮች ዱቴርቴን መርምረው አንድ ባዕድ ነገር አግኝተንባቸዋል ብለው ነበር። ካንሰር ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢሰጋም ዶክተሮች 'ጉዳት የሌለው ዕጢ' ነው የሚል መደምደሚያ ሰጥተዋል።

ጥቅምት ላይ ሩስያ ሄደው ከአገራቸው ዜጎች ጋር ውይይት ያካሄዱት ፕሬዝደንት ዱቴርቴ የአንድ ዓይናቸው ሽፋሽፍት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ በሽታ እንዳለባቸው አሳውቀው ነበር።

ከሳምንታት በኋላ ደግሞ ማኒላ የሚገኘው ቤተ-መንግሥታቸው ውስጥ በሞተር ብስክሌት ሲንሸራሸሩ ወድቀው ጀርባቸው መጎዳቱ ተነገረ።

በፊሊፒንስ ሕገ-መንግሥት መሠረት ሥልጣን ላይ የሚገኝ ፕሬዝደንት በጤና ምክንያት መምራት ከተሳነው ምክትል ፕሬዝደንቱ ሥልጣን ይይዛል። ምክትላቸው ደግሞ ሌኒ ሮቤርዶ። ሴትዬዋ የሊበራል ፓርቲ አባልና የዱቴርቴ አገዛዝ ቀንደኛ ነቃፊ ናቸው።

አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ከበድ ያለ እርምጃ በመውሰድ የሚታወቁት ዱቴርቴ በጭካኔያቸው ቢተቹም ወንጀል በአገሪቱ በመቀነሱ የሚያወድሷቸው አሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ