የአፕል ተቀጣሪ የደንበኛውን ሚስጥራዊ ፎቶ ወደ ግል ስልኩ መላኩ ተነገረ

የአፕል ሱቅ Image copyright Getty Images

አንድ የአፕል ሠራተኛ ከደንበኛው ስልክ ላይ ሚስጥራዊ ፎቷዋን ወደ ግል ስልኩ መላኩ ተሰማ።

ግሎሪያ ፉየንትስ ስልኳ ስለተበላሸባት ለማስጠገን ወደ አፕል መደብር ሄዳ ነበር። በቦታው ላገኘችው የአፕል ተቀጣሪም ስልኳን ሰጠችው። ሠራተኛው ግሎሪያ ስልክ ላይ ያገኘውን የግል ፎቶዋን ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኩ እንደላከም ተገልጿል።

ግሎሪያ ካሊፎርንያ ወደሚገኘው የአፕል መደብር ከማምራቷ በፊት የግል መረጃዎቿን ከስልኳ ላይ አጥፍታ ነበር። ሆኖም የአፕል ተቀጣሪው በፌስቡክ ገጿ በኩል ፎቶዋን እንዳገኘው ተናግራለች።

አፕል ስልኮች በዝግታ እንዲሰሩ በማድረጉ ይቅርታ ጠየቀ

ሴቶችን ከመንቀሳቀስ የሚያግደው መተግበሪያ ሊመረመር ነው

የአፕልና ሌሎችም ምርቶች ችግር እንዳጋጠማቸው ተገለፀ

አፕል ሠራተኛውን እየመረመረው እንደሆነና፤ ሠራተኛው ከዚህ በኋላ አፕልን እንደማይወክል አሳውቋል።

ግሎሪያ ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገረችው፤ ስልኳን ለጥገና የወሰደችው የገንዘብ ዝውውሯን ጨምሮ በርካታ የግል መረጃዎቿን ካጠፋች በኋላ ነው።

"ስልኬ ላይ የነበሩትን ፎቶዎችን ላጠፋ ነበር፤ የቀጠሮዬ ሰዓት አንደተለወጠ ሲነግሩኝ ግን ፎቶዎቹን ማጥፋቱን ዘንግቼ ወደ መደብሩ ሄድኩ" ስትል የተፈጠረውን አስረድታለች።

ተቀጣሪው ስልኳን ለመጠገን ዘለግ ያለ ጊዜ እንደወሰደበትና ሁለቴ የይለፍ ቃሏን (ፓስኮድ) እንደጠየቃትም አክላለች።

ግሎሪያ ስልኳ ተሠርቶ ቤት ከወሰደችው በኋላ፤ ፎቶዋ ወደማታውቀው ስልክ ቁጥር መላኩን አስተዋለች።

"ለወንድ ጓደኛዬ ያነሳሁትን የግል ፎቶዬን ወደ ስልኩ ልኳል፤ ምስሉ ላይ የምኖርበት አካባቢ ምልክት (ጂኦሎኬሽን) ስላለ ቤቴ የት እንደሚገኝም ያውቃል ማለት ነው፤ ሠራተኛው ያደረገውን ሳውቅ አለቀስኩ፤ እንዴት እንደቀፈፈኝ ለመግለጽም ይከብደኛል።"

ወደ መደብሩ ሄዳ ሠራተኛውን ስታነጋግረው፤ ፎቶው ከሷ ስልክ ወደእሱ እንዴት እንደተላከ የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን ገልጾላታል።

አፕል በበኩሉ ግሎሪያ ጉዳዩን ይፋ በማድረጓ አመስግኖ፤ የደንበኞችን የግል መረጃ የመጠበቅ ሕግን የጣሰው ሠራተኛው ላይ ምርመራ እንደሚያካሂድ የሚጠቁም መግለጫ አውጥቷል።

ግሎሪያ ግለሰቡ ላይ ክስ እንደምትመሰርት ፌስቡክ ገጿ ላይ አስፍራለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ