"ቦይንግ እኔ በሌለሁበት አባቴን ቀበረው" በአደጋው አባቷን ያጣችው ዚፓራ

ዚፖራ ኩሪያ
አጭር የምስል መግለጫ ዚፖራ ኩሪያ

በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ሳቢያ ሕይወታቸውን ካጡት አንዱ የዚፖራ ኩሪያ አባት ናቸው።

ባለፈው ሐሙስ በአደጋው የሞቱና አስክሬናቸውን ለመለየት ያልተቻለ ተሳፋሪዎች በተመሳሳይ ሬሳ ሳጥን፣ በመደዳ ተቀብረዋል።

ዚፓራ ይህ ሲከናወን በሥፍራው አልተገኘችም ነበር። በዕለቱ የቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦታው እንደተገኙ ቢነገርም፤ ዚፓራና ቤተሰቦቿ ስለ ክንውኑ የሰሙት ዘግይተው ስለነበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አልተኙም።

በአደጋው ከሞቱ ተሳፋሪዎች የሦስቱ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ስለ ሥነ ሥርዓቱ የተነገራቸው ከቀናት በፊት ነበር። ስለዚህም በዕለቱ መገኘት የቻሉት ከ157 የሟቾች ቤተሰቦች ሁለቱ ብቻ ናቸው።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የሞቱ ሰዎች አጽም ለቤተሰቦቻቸው እየተሰጠ ነው

ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ቦይንግን ሊከሱ ነው

"ቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአባቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ሳስበው ያንዘፈዝፈኛል" ስትል ዚፓራ ሀዘኗን ትገልጻለች።

እስካለፈው ሳምንት ድረስ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ሥፍራ የሰዎች አስክሬን እንዲሁም የአውሮፕላኑ ስብርባሪም ይገኝ ነበር።

በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ባለፈው ወር አካባቢውን ሲጎበኙ፤ የሰዎች ቅሪተ አካል እና ቁሳቁሶችም ማየታቸው እንዳስደነገጣቸው ተናገረው ነበር።

Image copyright Zipporah Kuria
አጭር የምስል መግለጫ በአደጋው የሞቱና አስክሬናቸውን ለመለየት ያልተቻለ ተሳፋሪዎች በተመሳሳይ ሬሳ ሳጥን፣ በመደዳ ተቀብረዋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሱ ይታወሳል። የሰዎች አስክሬን እና የአውሮፕላኑ የመረጃ ቋትም ተሰብስቦ ነበር።

አደጋው የደረሰው በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ እክል ምክንያት ሲሆን፤ ከዓመት በፊት ኢንዶኔዥያ ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ 737 ማክስ አውሮፕላን ተከስክሷል።

ማክስ 737 ላለፉት ዘጠኝ ወራት ከበረራ ታግዷል።

"ለአውሮፕላኑ መከስከስ ፓይለቶች ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም" አቶ ተወልደ ገብረማርያም

ቦይንግ የአደጋውን የምርመራ ውጤት ተቀበለ

የቢቢሲ ባልደረቦች አደጋው የደረሰበትን ሥፍራ በጎበኙበት ወቅት የአውሮፕላኑ የተለያዩ ክፍሎች ወዳድቀው አግኝተዋል። አካባቢው እየተጠበቀ ስላልነበረ እንስሳት በተከለለው ሥፍራ ገብተው ነበር።

በአካባቢው ዝናብ ሲበረታ ችግሩ መባባሱን ያስተዋሉ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች አንዳች እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ነበር።

አጭር የምስል መግለጫ ሳምያ ሮዝ

ልጇ ሳምያ ሮዝን በአደጋው ያጣችው ናዲያ ሚሊሮን፤ "በአካባቢው በግልጽ የሚታየውን የሰዎች አጥንት ነዋሪዎች ይሸፍኑት ነበር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎችን ቅሪተ አካል እንዲሸፍን እንፈልጋለን" ብላለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሩ መኖሩን አምኖ፤ በኢንሹራንስ ምክንያት እርምጃ መውሰድ አለመቻሉን ለሟቾች ቤተሰቦች አስታውቆ ነበር። ሆኖም ከቤተሰቦች ጫና ሲበረታበት እና የቢቢሲን ምርመራ ተከትሎ ችግሩ ተቀርፏል።

ከዚህ ቀደም ለፎረንሲክ ምርመራ የተነሱ የአጽም ቅሪቶች ተሰባስበው በሬሳ ሳጥን ተከተዋል። አካባቢው የቀብር ሥፍራም ተደርጓል።

የቦይንግ ኃላፊ የሟቾችን ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ ጠየቁ

«ሙሉ ቤተሰቤን በኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ አጥቻለሁ»

የሟቾች ቤተሰቦች፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሊያሳውቃቸው ይገባ እንደነበር ገልጸዋል።

ቦይንግ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ሆኖም "በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በላየን ኤር አደጋ ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሰዎች መጽናናቱን እንመኛለን፤ ድጋፍ በማድረግም እንቀጥላለን" የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ዚፓራ ኩሪያ ባለፈው ወር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛ የአባቷን አስክሬን ለመውሰድ ጥረት ብታደርግም የደረሰችው ዘግይታ ነበር። "ቦታው ላይ በጊዜው አለመገኘቴ ልብ ይሰብራል" ስትልም የተሰማትን ሃዘን ገልጻለች።

የአባቷ ሥርዓተ ቀብር የሚካሄድበትን ቀን ብታውቅ እንደማትቀር ገልጻም፤ "አባቴን እንዳልሰናበተው አደረጉኝ" ብላለች።