ያለታካሚዎች ፈቃድ ቀዶ ህክምና ያደረገው የማህጸን ሀኪም ተከሰሰ

ሀኪሙ ታካሚዎቹ የማያስፈልጋቸውን ቀዶ ህክምና ያለ ፈቃዳቸው አድርጓል ተብሏል Image copyright Western Tidewater Regional Jail
አጭር የምስል መግለጫ ሀኪሙ ታካሚዎቹ የማያስፈልጋቸውን ቀዶ ህክምና ያለ ፈቃዳቸው አድርጓል ተብሏል

ታካሚዎቹ የማያስፈልጋቸውን ቀዶ ህክምና ያለ ፈቃዳቸው አድርጓል የተባለ የማህጸን ሀኪም ቨርጂንያ ውስጥ ተከሰሰ።

ዶ/ር ጃቪድ ፐርዌዝ የተባለው ሀኪም፤ ህመም የሌለባቸው ሴቶችን 'ታማችኋል' በማለት ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ የአሜሪካው የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ አሳውቋል።

ሀኪሙ ባለፈው ጥቅምት በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ከ126 በላይ ሴቶች ጉዳት አድርሶብናል ብለዋል። የ69 ዓመቱ ሀኪም ሀሰተኛ መረጃ በመስጠትና በማጭበርበር ክስ ተመስርቶበታል።

'ሀሰተኛ' የተባለችው ሀኪም ታሰረች

የአትሌቲክስ ቡድን ሀኪም 177 አትሌቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል ተባለ

የጡት ካንሰር የያዛት የጡት ካንሰር ሀኪም

ኤፍቢአይ እንዳለው፤ ቨርጂንያ ውስጥ ሁለት ቢሮ ያለውና በሌሎች ሁለት ሆስፒታሎች የሚሠራው ሀኪሙ፤ ከታካሚዎች እውቅናና ፈቃድ ውጪ ቀዶ ህክምና ያደርግ ነበር።

እንደ ጎርጎሮሳውያ አቆጣጠር ከ2014 እስከ 2018 ድረስ፤ በመንግሥት ድጋፍ ህክምና ካደረጉ ሴቶች በ40 በመቶ ያህሉ ያለ ፈቃዳቸው ቀዶ ጥገና አድርጓል።

ከ510 ታካሚዎቹ፣ 42 በመቶው ቢያንስ ሁለት ጊዜ ቀዶ ህክምና ተደርጎባቸዋል።

ኤፍቢአይ ስለ ሀኪሙ መረጃ ያገኘው 2018 ላይ ነበር። ከሀኪሙ ጋር በአንድ ሆስፒታል የሚሠራ ግለሰብ ጉዳዩን ከታካሚዎች ከሰማ በኋላ ለኤፍቢአይ ጠቁሟል።

አንዲት ሴት ሀኪሙ በማህጸኗ ባደረገው ቀዶ ህክምና ሳቢያ መጸነስ እንደማትችል መግለጿን ኤፍቢአይ አስታውቋል። የኤፍቢአይ መርማሪ ዴዝሬ ማክስዌል እንዳሉት፤ ሀኪሙ ታካሚዎች ካንሰር እንደያዛቸው በማሳመን ቀዶ ህክምና ያደርግም ነበር።

የሀኪሙ ጠበቃ ሊውረንስ ዉድዋርድ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ዶ/ር ጃቪድ ፐርዌዝ ፓኪስታን ውስጥ ህክምና አጥንቶ በአሜሪካ፣ ቨርጂንያ የሥራ ፈቃድ አግኝቷል።

ከዚህ ቀደምም አላስፈላጊ ቀዶ ህክምናዎች በማድረግ ቨርጂንያ ውስጥ ምርመራ ሲደረግበት ነበር። 1996 ላይ ግብር በማጭበርበር ለሁለት ዓመት ከሥራ ታግዶም ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች