ኢትዮጵያ፡ የሞት አደጋ የሚያንዣብብባቸው አውራ ጎዳናዎች

በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ አቅራቢያ የተገለበጠ መኪና Image copyright Eric Lafforgue/Art in All of Us

ወ/ሮ ሳሙኔ አሊ በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ የድሬ ሂንጪኒ ነዋሪ ናቸው። በደህናው ቀን የሞላቸው የተረፋቸው "እመቤት" ነበሩ። መኪና ስላላቸው ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

በዚህ መካከል ልጃቸው ከባለቤቱ ጋር በጉዞ ላይ እያለ በደረሰበት የመኪና አደጋ ከነባለቤቱ ሕይወቱ አልፈ።

ወ/ሮ ሳሙኔ የልጃቸውን ልጆች ወስደው ማሳደግ ቢጀምሩም አቅም አጠራቸው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ባለቤታቸውም ከአምቦ ለንግድ ወደ አዲስ አበባ እየሄዱ እያለ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ ነው።

የልጅ ልጅ ታቅፈው ሕይወትን ለመምራት ቢፍጨረጨሩም አልሆነላቸውም። ወ/ሮ ሳሙኔ በአጠቃላይ 15 ቤተሰባቸውን ጎሮሮ ደፍኖ ማደር አቃታቸው።

ያኔ "ልጆቹ እናትና አባታቸውን ስላጡና ጥሪት ስለሌለኝ ለባዕድ አሳልፌ ሰጠሁ" ሲሉ የልጅ ልጆቻቸውን በጉዲፈቻ ወደ አውሮፓ መላካቸውን ይናገራሉ።

የባህር ዳር ነዋሪ የሆኑት የሰባተኛ ክፍሉ ተማሪ እስክንድርና (ስሙ የተቀየረ) እና አባቱ ማለዳ ከቤታቸው የወጡት አብረው ነው። ዘወትር አባትና ልጅ ወደ ጉዳያቸው የሚሄዱት ብስክሌታቸውን በማሽከርከር ጎን ለጎን እየተጨዋወቱ ነው።

ዕረቡ ዕለትም የሆነው እንደዚያው ነው፤ ቤት ያፈራውን ቀማምሰው፤ ልጅ ወደ ትምህርት ቤቱ፤ አባቱም ከእርሱ ጋር እየተጨዋወቱ ወደ ሥራ ገበታቸው ይሄዳሉ።

አዝዋ ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ ግን እርሳቸውን አንድ ግለሰብ ያስቆማቸዋል። ልጁ ትምህርት ቤት እየረፈደበት መሆኑን ተናግሮ ቀድሟቸው ይሄዳል።

በልጅ እግሩ ብስክሌቱን እየጋለበ፣ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲያቀና የደረሰበት የትራፊክ መብራት እንዲያልፍ አረንጓዴ አሳየው።

"ዓላማችን ችግሮችን ፈተን ገንዘብ ማግኘት ነው " የጠብታ አምቡላንስ ባለቤት

ስልክዎ ጥሩ አሽከርካሪ ሊያደርግዎ እንደሚችል ያስባሉ?

እርሱ በመልዕክቱ መሰረት ብስክሌቱን ወደ ፊት ገፋ። በሌላ መስመር ግን ቀዩን መብራት ጥሶ የመጣ ሕዝብ ማመላለሻ ገጨው። በወቅቱ ሾፌሩ መኪናውን አቁሞ አምልጧል ይላል እስክንድር።

አሁን በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ሕክምና የሚደረግለት ተማሪ እስክንድር ጭኑና ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት አጋጥሞታል።

እስክንድር ታሞ በተኛበት ያገኘናቸው ዶ/ር አዲሱ መለሰ፣ በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል የኬዝ ማናጀር ነው። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ወደ 300 ሰው በትራፊክ አደጋ ምክንያት ተጎድተው ወደ ድንገተኛ ክፍል መምጣታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እነዚህ 300 ሰዎች መንገድ ላይ የሞቱትን፣ ከነጉዳታቸው ወደ ቤታቸው የሄዱትንና ወደ ሌላ ጤና ተቋም የተወሰዱትን ሳይጨምር መሆኑን ይናገራሉ።

ይህ የሚያሳየው ይላሉ ዶ/ር አዲሱ፣ በመኪና አደጋ የሚጎዱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና አደጋው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሄዱን ነው።

የድንገተኛ ክፍሉ በሰው ኃይልና ቁሳቁስ አቅርቦት የተሟላ ባለመሆኑ በትራፊክ አደጋ ወደ ክፍላቸው የሚመጡ ሕሙማን የሚደርስባቸው ጉዳት በሚገባው ለማከምና በተገቢው ሰዓት የሕክምና ርዳታ ለመስጠት ፈታኝ እንደሆነባቸው ጨምረው ያስረዳሉ።

እነዚህ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች አደጋው ከደረሰበት ስፍራ ሆስፒታል እስኪደርሱ ድረስ የሚደረግላቸው ሕክምና ርዳታና ድጋፍ አለመኖሩን በማንሳት በዚህም ደረጃ በሀገር ደረጃ ያለው ተሞክሮ አነስተኛ በመሆኑ የአደጋው ተጎጂዎች ጉዳት እንደሚባባስ ይጠቅሳሉ።

አክለውም በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል በአንቡላንስ ርዳታ እያገኙ መምጣት ቢኖርባቸውም ይህ ሲሆን እንደማይመለከቱ የሚገልፁት ዶ/ር አዲሱ፣ ተጎጂዎቹ በርካታ ደም ሊፈሳቸው፣ ምላሳቸው ታጥፎ መተንፈሻ አካላቸውን ሊዘጋው እንደሚችል፣ በመጥቀስም በቀላሉ ለመርዳት የሚቻሉ ጉዳቶች ወደ ሞት ሊያደርሱ ይችላሉ ሲሉ ያለውን ችግር ይገልጻሉ።

በመኪና አደጋ የተጎዱ ግለሰቦች የሕክምና ርዳታ ማግኘት የሚጀምሩት ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ መሆኑን በማስታወስ ይህ በሕይወት የመትረፋቸውን ዕድል እንደሚያጠበው ያስረዳሉ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ደህንነት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ ለቢቢሲ እንዳሉት ከአመት ዓመት የትራፊክ አደጋው እየጨመረ የሄደ ሲሆን፣ በክልሉ ካለው የአደጋ ስጋት የተነሳ ባልና ሚስት ወደ አንድ ጉዳይ በተመሳሳይ ተሽከርካሪ ለመሄድ በመፍራት 'አንዳችን ብንተርፍ በሚል' የተለያየ መኪና እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በ2012 ሩብ አመት ብቻ 618 አደጋዎች መድረሳቸውንኮማንደር ሙሉጌታ አስረድተዋል። በዚህ አደጋ 183 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል። 105 ከባድ፣ 114 ቀላል አካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን በማስታወስም እዚህ ውስት ቁጥራቸው ያልተካተተ ሊኖርአእንደሚችልም ገልጸዋል

አቶ ይበልጣል ታደሰ በአማራ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት የኮሙኑኬሽን ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር ናቸው። በአማራ ክልል ከመስከረም ወዲህ ያለው የትራፊክ አደጋ እየጨመረ መሆኑን ያስረዳሉ ይላሉ።

ከፍተኛ የሆነ የሰው ሞት ያስከተሉ አደጋዎች ከመስከረም ወዲህ መመዝገባቸውን ገልፀው በ2011 አጠቃላይ የአደጋው ብዛት 2591 መሆኑን ያስታውሳሉ።

ከእነዚህ መካከል 1109 ሰዎች ሞተዋል የሚሉት አቶ ይበልጣል የደረሰው የጉዳት መጠን በንብረት ሲሰላ ደግሞ ከ97 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንም ያስረዳሉ።

በኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ የትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አዲሱ ተመስገን አንደሚሉት በ2012 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 1095 የትራፊክ አደጋ መከሰቱን የደረሰ ሲሆን፣ የ433 ሰዎችም ሕይወት አልፏል።

በዚህ ዓመት በደረሰው የትራፊክ አደጋ የወደመው ንብረትን በገንዘብ አስልተው ሲናገሩም 63.7 ሚሊየን ይገመታል ይላሉ።

Image copyright Eric Lafforgue/Art in All of Us

የትግራይ ክልል ትራፊክ ፖሊስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ብርሃነ መስቀል በበኩላቸው በክልላቸው በ2011 ብቻ 1512 አደጋዎች ማጋጠማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚህ አደጋ 386 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 79 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ብለዋል።

ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ እንደሚሉት ከሆነ በክልላቸው አጠቃላይ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረው፣ የትራፊክ አደጋ ሲሰላ ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር በንጽጽር እየተሰላ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ የትራፊክ ማናጅመንቱ ካለው የትራፊክ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ጠቅሰዋል።

አቶ አዲሱ ተመስገን የኦሮሚያ ክልል ብዙ የትራፊክ ፍሰት ያለበት እንደመሆኑ መጠን የትራፊኩ አደጋ በዛው ልክ እንደሚበዛ ያብራራሉ።

በክልሉ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ብዙ ጊዜ ከአሽከርካሪዎች ስነምግባር ጉድለት ጋር የተያያዘ መሆኑን ቢሯቸው በጥናት ማረጋገጡን የሚናገሩት አቶ አዲሱ፣ ሌሎች ምክንያት ናቸው ያሉትን ሲጠቅሱም ለቁጥጥር የሚሰማሩት ፖሊሶች በትክክል አለመቆጣጠራቸውን፣ በፍጥነት ማሽከርከር፣ ከመጠን በላይ መጫን እና ሱስ አስያዥ ነገሮችን እየተጠቀሙ ማሽከርከር እና ተገቢውን እርፍት ሳይወስዱ ማሽከርከር ናቸው ይላሉ።

ኮማንደር ሙሉጌታ በበኩላቸው በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ መኪኖች እየገቡ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት የቁጥጥር ስርዓቱ በቴክኖሎጂ አለመደገፉን በማንሳትም የያለውን ክፍተት ያሳያሉ።

በእግሩ እየሄደ ህግ የሚያስከብር የትራፊክ ፖሊሱ አባል መኖሩ፣ በየትልልቅ ከተሞች ላይ የትራፊክ መብራት የተሟላ አለመኖር፣ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ካሜራ፣ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር አለመኖራቸውን በማንሳትም የትራፊክ ማናጅመንቱ ጉዳይ በሚጠበቀው ደረጃ አይደለም ሲሉ የችግሩን ስፋት ያሳያሉ።

ትልልቅ መንገዶች ሲገነቡ የእግረኛ መንገድ በሚፈለገው ደረጃ አለመገንባት፣ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ የመንገድ ስርዓት አለመኖር፣ የብስክሌት ማሽከርከሪያ መስመር አለመከለልንም ለትራፊክ አደጋ መበራከት ምከንያት ከሆኑት መካከል ይጠቅሳሉ።

Image copyright Eric Lafforgue/Art in All of Us

ወደ ሀገሪቱ የሚገባው የተሽከርካሪ ብዛት ካለን የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን በየሚናገሩት ኮማንደር ሙሉጌታ፣ የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑን ይስማሙበታል።

ለዚህ ሁሉ አደጋ የትራፊክ ማኔጅመንቱ ያለውን የትራፊክ ስርዓት ለመምራት በሚችል መልኩ የተዘረጋ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ዋና ዋና የትራፊክ አደጋዎች አሽከርካሪም እግረኛም የሚፈጽሙት ስህተት መሆኑን አንስተው፣ የማሽከርከር ስራ ያለውን ከባድ ኃላፊነት ያለመገንዘብ ለአደጋ ምክንያት መሆኑን ያስታውሳሉ።

የመንገድ ችግር፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ከሚደርሱ የመኪና አደጋዎች ጥቂቱን እንደሚይዙ በመጥቀስ አብዩን ድርሻ የሚይዘው የእግረኛና የአሽከርካሪ ስህተት መሆኑን አጽንኦት ይሰጡታል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ