የ31 ዓመቱ ኢሕአዴግ ማን ነው?

የኢሕአዴግ አርማ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እንደ ጥምር ግንባር የተመሰረተው ከ31 ዓመታት በፊት ግንቦት 1981 ዓ. ም. በትግራይ ክልል በተምቤን ዓዲ ገዛእቲ በሚባል አካባቢ ነበር።

ወደ ስድስት ሚለየን ገደማ አባላት እንዳሉት የሚነገርለት ገዢው ፓርቲ፤ ከግራ ዘመም ፓለቲካዊ መርህ በሚመነጨው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲመራ ቆይቷል።

ዋና መስራቹ ፓርቲ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የደርግ ሥርዓትን በመቃወም የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ. ም. ወደ ትጥቅ ትግል ከገባ ዘንድሮ 44ኛ ዓመቱን ይዟል።

የቀድሞው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የአሁኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የቀድሞው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የአሁኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደሕዴን) ብሄራዊ ድርጅቶች ግንባሩን ተቀላቅለዋል።

ደርግ ከሥልጣን ከተወገደበት ጊዜ አንስቶ የፓርቲው የረዥም ጊዜ ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከሰባት ዓመት በፊት ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገሪቷንም በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል። ከሰባት ዓመት በፊት አቶ መለስ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ምክትላቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበር ሥልጣኑን የተረከቡት።

በዋነኛነት በኦሮሚያ ተነስቶ በመላው አገሪቱ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን በመልቀቃቸው መንበሩን ዐብይ አሕመድ ተረክበዋል።

ሥልጣን ለዓመታት አውራ ፓርቲ ከነበረው ሕወሓት ወደ ኦዴፓ መሸጋገሩ በወቅቱ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ኢህአዴግ እዋሃዳለሁ ሲል የምሩን ነው?

"ለውጡን ለማደናቀፍ ከተቻለም ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ"

የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ፤ በየሁለት ዓመቱ ከእያንዳንዱ አባል ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴው መካከል በሚመረጡ 36 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ይመራል።

ሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን)፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) የአሁኑ ሶማሊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶዴፓ) እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) አምስቱ የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች ናቸው።

ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኃላ ከግንቦት 24-28 ቀን 1983 ዓ. ም. በተካሄደው የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጉባኤ የሸግግር መንግሥት ተመስርቶ፤ በሽግግር ወቅቱ እንደ ሕገ መንግሥት የሚያገለግል ቻርተር ጸድቋል።

በቻርተሩ መሠረት 86 አባላት ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ተመስርቷል። የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 11/1984 ዓ. ም. በሽግግር ወቅቱ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ በየካቲት ወር 1984 ዓ. ም. የአከባቢና ክልላዊ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ምርጫ ተደርጓል።

የመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 1987 ዓ. ም. የተካሄደ ሲሆን፤ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በጉልህ ከሚታወሱት ዋነኛው የ1997 ዓ. ም. ምርጫ ነው። ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ እንዳገኘ በመግለጽ ከአንዱ የሥልጣን ዘመን ወደ ሌላው የሚሸጋገረው ኢሕአዴግ፤ በተለይ ከቅንጅት ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ ፉክክር የገጠመው በዚሁ ምርጫ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ግን ኢሕአዴግ ከ90 በላይ ድምፅ ማግኘቱን ዳግመኛ በመግለጽ በመንበሩ ቆይቷል።

ቀደም ሲል የመወሀድ አጀንዳ ተደጋግሞ በግንባሩ ጉባኤዎች ሲነሳ ቆይቷል።

ዶ/ር ዐብይ በግላቸው ለውጥ ያመጣሉ?

ኢህአዴግን ያጣበቀው ሙጫ እየለቀቀ ይሆን?

ይሁን እንጂ ከዐብይ አሕመድ ወደ ሊቀ መንበርነት መምጣት ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአባል ድርጅቶች መካከል ቅራኔና መከፋፈል ሲፈጠር ይሰተዋላል።

ፓርቲው ከተመሰረተ ግዜ ጀምሮ ሲመራበት የቆየውና የአገሪቱ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ምንጭ እንደሆነ የሚነገርለት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ሊቀ መንበሩ ይህ ርዕዮተ ዓለም በ 'መደመር' ሃሳብ እንደሚቀየር አሳውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሕአዴግ ተዋህዶ 'የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ'ን የመመስረት እቅድ እንዳለው መነገሩን ተከትሎ፤ ሕወሓት ከሕግም፣ ከተቀባይነትም አንጻር ሕገ ወጥ አካሄድ ሲል መንቀፉን ይታወሳል። በየዕለቱም በፓርቲውና በግንባሩ መካከል የታየው ልዩነት እየሰፋ መሄዱ ይስተዋላል።

ሆኖም ከህወሓት ውጪ ያሉት ሦስቱ እህት ፓርቲዎች የውህደቱ አካል እንደሚሆኑ እየተነገረ ነው።

የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ምዕራፍ ስድስት፣ አንቀጽ 91 ላይ እንደተቀመጠው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ለመፍጠር በፓርቲዎቹ የመተዳደርያ ደንብ መሰረት ውህደቱ በእያንዳንዱ የፓርቲው ጉባኤ መረጋገጥ እንዳለበት ይደነግጋል።

"ምን ተይዞ ምርጫ?" እና "ምንም ይሁን ምን ምርጫው ይካሄድ" ተቃዋሚዎች

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት የሚያደርገው ጉዞ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ቢነሳም እውን ሆኖ አልታየም። የብሔር ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ እውን ይዋሀዳል? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ሲሆን፤ በቅርቡ ግንባሩ ከሕወሓት ውጪ ሊዋሀድ ይችል ይሆናል የሚል ጭምጭምታ አስነስቷል።

በተለይ በ1993 ዓ. ም በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ግንባሩም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮበት ነበር። አሁንም በግንባሩ ውስጥ የሚታየው መከፈፋልና አለመግባበት ወዴት ሊያመራው ይችላል? የሚል ጥያቄ እየፈጠረ ይገኛል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ