ኢሕአዴግ እዋሀዳለሁ ማለቱን የፖለቲካ ተንታኞች እንዴት ያዩታል?

ከግራ አደም ካሴ (ዶ/ር) እና አቶ ገብሩ አስራት

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ስብሰባውን እንደሚያካሂድ ተሰምቷል።

ኮሚቴው ዛሬ በሚያካሂደው ስብሰባ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መክሮ የወደፊት አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል። የውህደት ጉዳይ አጀንዳ እንደሚሆንም ሲወራ ሰንብቷል።

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት የሚያደርገው ጉዞ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ቢነሳም እውን ሆኖ አልታየም። የብሔር ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ እውን ይዋሀዳል? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ሲሆን፤ በቅርቡ ግንባሩ ከሕወሓት ውጪ ሊዋሀድ ይችል ይሆናል የሚል ጭምጭምታም ተነስቷል። በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር) እና የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አስራትን አነጋግረናል።

"የኢሕአዴግ መዋሃድ ጫፍ የደረሰ ይመስላል" አደም ካሴ (ዶ/ር)

የኢሕአዴግ መዋሃድ ጫፍ የደረሰ ይመስላል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር)፤ የኢሕአዴግ አባል የሆኑት ሦስቱ ፓርቲዎች አጽድቀውታል ተብሎ መወራቱ የሚያሳየው ውህደቱ የቀጠለ መሆኑን ነው ይላሉ።

እንደ ፖለቲካ ተንታኙ፤ ውህደቱን ሕወሓት ሲቃወመው ቢቆይም የሚቀር አይመስልም። ዶ/ር አደም፤ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን አሁንም የማናውቅ መሆኑን በማንሳት፤ አዲሱን ውህድ ፓርቲ ጠለቅ ብሎ ለማየት ፈታኝ መሆኑን ያነሳሉ።

ኢሕአዴግ ውህደቱን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ያለው እንደ ፓርቲ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በግልጽ ማወቅ አለብን ማለት አንችልም የሚሉት ዶ/ር አደም፤ የጋራ የሆነ ፕሮግራሙ ምን እንደሚመስል፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎቹ ምን እንደተስማሙ አለማወቃችንን በመጥቀስ ስለ አዲሱ ውህድ ፓርቲ የሚኖረን ምስል ጎዶሎ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

በተለይ ለኦዲፒም ሆነ ለአዴፓ መሠረታዊ የሚባሉና በግልጽ የሚታወቁ ጉዳዮች ላይ (እንደ አዲስ አበባ ያሉ) የወሰዷቸውን ውሳኔዎችን አልሰማንም ይላሉ።

የ31 ዓመቱ ኢሕአዴግ ማን ነው?

ኢህአዴግ እዋሃዳለሁ ሲል የምሩን ነው?

እንዲህ አይነት ሁለቱን ፓርቲዎች የሚያፋጥጡ ነገሮች ዘግይተው ሲሰሙ፤ በታችኛው አባላት ዘንድ ግርታና መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ውህደቱ ቢሳካ እና ኢሕአዴግ ከሕወሓት ውጪ ቢዋሀድ፤ አዲሱ ፓርቲ ከቁጥር እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች አንጻር የሶማሊያና ሌሎች አጋር ተብለው የቆዮ ፓርቲዎች ስለሚቀላቀሉት ሊያካክሰው ይችላል ይላሉ።

ዶ/ር አደም፤ ከባድ ሊሆን የሚችለው፤ ሕወሓት በውህደቱ ውስጥ ካልተካተተ ከእርሱ ጋር የሚሠሩ ሌሎች ፓርቲዎችን መፈለግ ስለሚኖርበት ነው በማለት፤ ሕወሓት በሃሳብ ወይንም በርዕዮተ ዓለም የሚመስሉትን የሚፈልግ ከሆነ፤ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጎልተው የሚታዮትና በብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ አቋማቸው ከእርሱ ጋር የሚመስሉትን ኦነግ፣ አብንና ምናልባትም ኦፌኮ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

እነዚህ ፓርቲዎች የብሔር ፖለቲካን መሰረት አድርገው የተደራጁ መሆናቸውና ጠንካራ ተገዳዳሪ መሆን ከሚችሉ ክልሎች መገኘታቸውን በመጥቀስ፤ ከእነዚህ አካላት ጋር ለመሥራት ፍላጎት ሊኖር እንደሚችል ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ።

ሆኖም ግን በኦሮሚያም በአማራ ክልልም ከሕወሓት ጋር በሃሳብ የሚጣጣሙ ፓርቲዎች ቢኖሩም፤ ሁለቱም ክልሎች ላይ ያሉት ገዢ ፓርቲዎች ከክልላቸው ተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የመሰባሰብ አዝማሚያ ማሳየታቸው፤ ሕወሓት ግንባር የሚሆነው ፓርቲን እያሳነሰበት እንደሚሄድ ዶ/ር አደም ይጠቅሳሉ።

ሕወሓት በሚቀጥሉት አምስት አስር ዓመታት በክልሉ ውስጥ ጠንክሮ ሊሄድ እንደሚችል የሚገልጹት ዶ/ር አደም፤ በሌላ ክልል ካሉ ፓርቲዎች ጋር በግንባር ለመሥራት ያለው ሁኔታ እንደሚታሰበው ቀላል አይሆንለትም ሲሉ ይገልጻሉ።

"ሕወሓት ብቻውን የመሆን እድሉ ሰፊ ነው" በማለትም፤ ከኢሕአዴግ ጋር ድርድር አድርጎ ለመቀጠል ወይም ከሌሎች ጋር በጋራ ለመሥራት ያለው እድል ፈታኝ ዳገት መሆኑን ያነሳሉ።

ሕወሓት በአገር ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመቀጠል ትልልቅ ፓርቲዎች ውስጥ መግባት እንደሚጠበቅበት በማስታወስ፤ ያንን ከየትኛው ወገን፣ ግንባር፣ ጥምረት ጋር ሆኖ እንደሚያደርገው በሂደት ይታያል ይላሉ።

"ሕወሓት በመግለጫ እንገነጠላለን ብሎ አያውቅም" የሚሉት ዶ/ር አደም፤ ካለው ሥርዓት አንጻር በክልል ደረጃ ያለውን ሥልጣን መጠየቁ መጥፎ አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

በዚህ መካከል ግጭትና አለመግባባት ቢነሳ፤ አሁን ባለው የፌደራል ሥርዓት ውስጥ ግጭቶችን መፍቻ መንገድ የለም የሚሉት ዶ/ር አደም፤ ሁሉም በየክልሉ 'ይኼ የኔ ነው፤ ይኼ የኔ ነው' በሚልበት በአሁኑ ወቅት ግጭቶች እንደሚጠበቁ በማንሳት፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ቀድሞው ግጭቶቹን በፓርቲው በኩል የሚፈታ ሥርዓት አለመኖሩን በመጥቀስ ያላቸውን ስጋት ያስቀምጣሉ።

ከፓርቲው ውጪ ግጭቶችን መፍታት የሚያስችል የሕግ ሥርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። ዛሬ ሕወሓት አለኝ የሚለውን ቅሬታ ነገ ሌላ ክልል ሊያነሳው ስለሚችል፤ ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት ግጭቶችን መፍቻ መንገድ ማበጀት እንደሚገባም ይመክራሉ።

አሁን ያለችው ኢትዮጵያ፤ ሁሉ ነገሯ በብሔር የተዋቀረ መሆኑን በማንሳት፤ "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖረውን የኢሕአዴግ የውህደት አጀንዳ ለማስፈፀም ላይ ታች ሲሉ የከረሙት በብሔር የተዋቀረውን ክልል መቀየር ባይችሉ እንኳን፤ የፓርቲ ሥርዓቱን አንድ በማድረግ ማለዘብ አስፈላጊ መሆኑን በማመናቸው ነው" ይላሉ።

ኢህአዴግ ከአባል ፓርቲዎቹ መግለጫ በኋላ ወዴት ያመራል?

"ለውጡን ለማደናቀፍ ከተቻለም ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ"

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ከበርካታ ወገኖች ቅሬታ የሚቀርብበት ቢሆንም፤ በጥሩ መልኩ ከሄደ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደገለፁት ትንንሽ ፓርቲዎች ተውጠው፣ በሃሳብ ዙሪያ የሚደራጁ ትልልቅ ፓርቲዎች መፈጠራቸው አይቀርም ሲሉ ያላቸውን ግምት ያስቀምጣሉ።

"በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ብሔርተኝነት ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ ትልቁ ፈተና ነው" የሚሉት ዶ/ር አደም፤ በቀጣይ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ፤ በክልላቸው ድጋፍ የማግኘት እድላቸው አጠራጣሪ በመሆኑ፤ ኢሕአዴግ ሲዋሃድ ከሌሎች አካባቢዎች በሚያገኙት ድምጽ እድላቸው እንደሚሰፋም ይናገራሉ።

ዶ/ር አደም፤ "ውህደቱ ከዐብይ የሚያልፍ፣ በሀሳብ ላይ የተመሰረተ መሆን አለመሆኑ ላይ ጥያቄ አለን" በማለት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ምክንያት በሥልጣን ባይቀጥሉ ውህደቱ ይቀጥላል ወይ? የሚለውን ለማየት፤ የአዲሱን ውህድ ፓርቲ ፕሮግራም ማየት አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።

"ፓርቲ ሊበተን ይችላል፤ ይሄ የአገርን እጣ ፈንታ መወሰን ግን የለበትም" አቶ ገብሩ አስራት

የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አስራት፤ ስለ ውህደት ሲነሳ፤ የፓርቲዎች ሙሉ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ከሆነ በገዢ ፓርቲው ዘንድ ቀውስ እንዳለ ያመለክታል ይላሉ።

በእርግጥ በየትኛውም አገር የፓርቲ ግንባር ሊፈርስ፣ አዲስ ቅንጅት ሊፈጠር እንደሚችልም ቢጠቅሱም፤ ይህ ሂደት ወደ ኢትዮጵያ አውድ ሲመጣ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንዲህ ያብራራሉ።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ገዢ ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ፣ ሕዝቡንም ለመቆጣጠር የሚሞክር ስለሆነ አንድ ፓርቲ ሲላላና ሲዳከም የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። ከአራቱ መስራች ድርጅቶች አንዱ ሕወሓት ከወጣ፣ [ውህደቱ] የተቀሩት ተወያይተው የተስማሙበት ካልሆነም ችግሩ ለሕዘብ የሚተርፍ ይሆናል።"

በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ኢሕአዴግን ጨምሮ ፓርቲዎች የሚፎካከሩ ሳይሆኑ በጥቅም የተሳሰሩ እንዲሁም አንዱ ሌላውን እየጠለፈ የሚሄድ መሆኑን በማጣቀስ፤ "እስካሁንም ገዢ ፓርቲው አለመስማማቱ፣ አንድ አለመሆኑ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው" ይላሉ።

ኦቶ ገብሩ በመርህ ደረጃ ውህደትን እንደማይቃሙና እንዲያውም ኢሕአዴግ ለውህደት ዘግይቷል ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ። ሆኖም ግን በችኮላ፣ ለፓለቲካ ጨዋታ ሲባልና ስምምነት ሳይፈጠር መዋሀድ ዘላቂነት ይኖረዋል? ሲሉ ይጠይቃሉ።

ኢሕአዴግ መዋሀድ ካለበት፤ የጋራ ፕሮግራም እና የጋራ ሕገ ደንብ መኖርን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ። ሕወሓት በውህደቱ አልሳተፍም ካለም መብቱ እንደሆነና ችግር እንደማይፈጠርም ያክላሉ። ሆኖም ግን ጉዳዩ ችግር ሊያስከትል የሚችልባቸውን ሁለት አካሄዶች እንዲህ ያስቀምጣሉ።

"አንደኛ፤ ቀሪዎቹ ሦስት ድርጅቶች እኔ ያልኩትን ብቻ፣ የኔን ርዕዮተ ዓለም ብቻ ተቀብለው ካልሆነ በስተቀር አልዋሀድም ከተባለ ስህተት ነው። ሁለተኛ፤ እኔ በዚህ ውህደት ከሌለሁ ትግራይም ትገነጠላለች የሚለው አካሄድም ስህተት ይመስለኛል።"

አቶ ገብሩ፤ የፓርቲውን አለመስማማትና የሥልጣን ሽኩቻ ወደ ሕዝብ ወስዶ፤ እኔ እዚህ ሥልጣን መሀል ካልቆምኩ፤ ሕዝብም ይገነጠላል የሚለው አስተያየት የተሳሳተ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከምጣኔ ሀብት፣ ከደህንነት እንዲሁም ከዲፕሎማሲ አንጻርም ለትግራይ ሕዝብም ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር እንዲሁም ሕዝቡ ብዙ ታግሎ ያገኛቸውን ነገሮች የሚያሳጣ እንደሆነም ያክላሉ።

"ሕወሓት ርዕዮተ ዓለሙን የማራመድ፣ ከመሰሉት ድርጅቶች ጋር የመጣመርም መብት አለው። ፓርቲ ሊበተን ይችላል፤ ይሄ ግን የአገርን እጣ ፈንታ መወሰን የለበትም። አገር ሊበተን ይችላል ማለትም አደገኛ ነው" ሲሉም አቋማቸውን ይገልጻሉ።

ሕወሓት እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀጥል ይችላል ወይ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ፤ ውይይትና ድርድር የማይሆን ሲሆን ከፓርቲ ወጥቶ አቋምን ማራመድ በፖለቲካ ያለ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ሕወሓት እጅግ የተዳከመበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለ በመግለጽ "የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም ይዞ ሕዝብን ያሰባስበል የሚል አመለካከት የለኝም" ይላሉ።

መሀል ቦታ የነበረው ድርጅት ለምን በአጭር ጊዜ ተበታተነ? የሚለው መታሰብ አለበት የሚሉት አቶ ገብሩ፤ ችግሩ ቆም ተብሎ ከታየ፤ መልሶ ፓርቲ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢህአዴግን ወዴት ይመራው ይሆን?

ህወሓት፡ ሃገራዊ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ትግራይ የራሷን ምርጫ ታካሂዳለች

ከሳምንት በፊት የሕወሓት ልሳን በሆነው 'ወይን' መጽሔት ላይ አገራዊ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ በማካሄድ 'ዲ ፋክቶ ስቴት' ይሆናል መባሉ ይታወሳል።

አቶ ገብሩ "የተባለው እውን የሚሆን አይመስለኝም "ይላሉ። አሁን ላይ የትግራይ ተወላጆች ከተለያየ ቦታ እየተፈናቀሉ መሆናቸውን፣ የሕወሓት አጋሮች በትግራይ ሕዝብና በሕወሓት ላይ እየዛቱ መሆኑንም ጠቅሰው "በሁሉም በኩል ጽንፈኛ አካሄድ አለ" ይላሉ።

"ሕወሓት ብቻ ሳይሆን አዴፓ፣ ኦዲፒም ጽንፈኛ ፖለቲካ እያራመዱ ነው። የራሳችን መንግሥት እንመሰርታለን የሚለው ጽንፍ ጊዜያዊ ሁኔታው የፈጠረው ነው። ነገር ግን ጊዜያዊ ሁኔታ የፈጠረውን ችግር እንደ ዘላቂ ስትራቴጂ መውሰድ ችግር አለበት" ሲሉም ያብራራሉ።

አንድ ፓርቲ ስለተሸነፈ፣ የፓርቲ አመራር ከሥልጣን ስለተወገደ የትግራይ ሕዝብ እድል በዛ መወሰን የለበትም የሚሉት አቶ ገብሩ፤ "መሰረቱ ሕዝብ ለሕዝብ አይጣላም፣ ሕዝብ ለሕዝብ አይዋጋም፣ ሕዝብ ለሕዝብ አይራራቅም" ሲሉም ያክላሉ።