በቦሊቪያ የሞራሌስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ተጋጭተው ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

በቀድሞው የቦሊቪያ ፕሬዝዳንት ኤቮ ሞራሌስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ Image copyright Reuters

በቀድሞው የቦሊቪያ ፕሬዝዳንት ኤቮ ሞራሌስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

በማዕከላዊ ሳካባ የሚሠሩ ሀኪም እንደተናገሩት ሰዎቹ ሕይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው ነው። የቦሊቪያ አመራሮች ሰዎች ስለመገደላቸው ያሉት ነገር የለም።

ሞራሌስ ባለፈው እሁድ ከሥልጣን ወርደው ወደ ሜክሲኮ መሸሻቸው ይታወሳል።

ሞራሌስን ከሥልጣን ለመውረድ ያበቃቸው ባለፈው ወር የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል መባሉ ቢሆንም፤ እርሳቸው ግን ለቢቢሲ፤ ምንም አይነት ክስ ሊቀርብባቸው እንደማይችል ተናግረዋል።

ሞራሌስን ተክተው ሥልጣን የያዙት እንደራሴዋ ጄነኔ አኔዝ፤ ሞራሌስ ወደ ቦሊቪያ ከተመለሱ ክስ ይመሰረትባቸዋል ብለው ነበር።

ተቃዋሚዎች የከንቲባዋን ጸጉር አስገድደው ላጩ

የቦሎቪያዋ እንደራሴ ራሳቸውን ፕሬዘዳንት አድርገው ሾሙ

የቦሊቪያው ሞራሌስ ወደ ሜክሲኮ ሊሸሹ ነው

አዲሱ አመራር ራሱን ከሞራሌስ ግራ ዘመም ደጋፊዎች ለማራቅ፤ በቦሊቪያና በቬንዝዌላ መካከል ያለውን ግንኙነት አቋርጧል። ከ700 በላይ የኩባ የህክምና ባለሙያዎችንም ወደ አገራቸው መልሷል።

በሳካባ የሆስፒታል ዳይሬክተር የሆኑት ጉዳልቤርቶ ላራ ለአሶሽየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት ሟቾቹ በጥይት ተመተው ነበር። የአይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ ሞራሌስ ወደ ቦሊቪያ እንዲመለሱ እየጠየቁ የነበሩ ሰልፈኞች ላይ ፖሊሶች ተኩሰዋል።

የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘጋቢም አምስት የሞራሌስ ደጋፊዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

ባለፈው አርብ ሰልፍ የወጡ ተቃዋሚዎቸን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሶ ነበር። ሞራሌስ በፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳያጡ ሲሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም ከሥልጣን መልቀቃቸው በደጋፊዎቻቸውን ተቃዋሚዎቻቸው መካከል ግጭት አስነስቷል።

ሞራሌስ ከቢቢሲ ሙንዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ያለፈውን ወር ምርጫ ከታዘቡት አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው እሳቸው ሊከሰሱ አይችሉም።

ሞራሌስን ተክተው ሥልጣን የያዙት እንደራሴዋ ጄነኔ አኔዝ፤ በቅርቡ አገራዊ ምርጫ እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች