የስዊድን ተመራማሪዎች 'ስብሰባ ህክምና ነው' አሉ

ስብሰባ ሲካሄድ Image copyright Getty Images

በስዊድኑ ማላሞ ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት፤ ስብሰባ እንደ 'ህክምና' ሊወሰድ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

በሥራ ቦታ የሚካሄድ ስብሰባ፣ ውሳኔ በማስተላለፍ ረገድ ካለው ሚና በበለጠ እንደ ህክምና የሚኖረው ዋጋ እንደሚልቅ ተመራማሪዎች በጥናት ደርሰንበታል ብለዋል።

ስብሰባ፤ ሠራተኞች ብስጭታቸውን የሚገልጹበት፣ በመሥሪያ ቤቱ ያላቸውን ቦታ የሚያሳዩበት እንደሆነም ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።

በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል ተባለ

ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሆል እንደሚሉት፤ በመሥሪያ ቤቶች የሚካሄዱ ስብሰባዎች ቁጥር ቢጨምርም፤ የውሳኔ መስጫ መድረክ የመሆናቸው ነገር እያሽቆለቆለ መጥቷል።

የስብሰባዎች ቁጥር መጨመሩ፤ በሥራ ቦታ ያለው አወቃቀር መለወጡን እንደሚያሳይ ያምናሉ። የሰዎች ውጤታማነት እንደቀነሰና በተቃራኒው አማካሪ፣ ስትራቴጂ ነዳፊ የተሰኙ ቦታዎች እየጎሉ መምጣታቸውንም ይገልጻሉ።

"ብዙ ኃላፊዎች ምን መሥራት እንዳለባቸው አያውቁም፤ ሚናቸው ምን እንደሆነ ስለማያውቁ በርካታ ስብሰባ ይጠራሉ" ይላሉ።

ሠራተኞችም በስብሰባ ላይ በማውራት ሚናቸው ምን እንደሆነ ለማግኘት ስብሰባውን እንደሚጠቀሙበት የሚገልጹት ተመራማሪው፤ እነዚህ ሰዎች ከሥራ ሰዓታቸው ገሚሱን በስብሰባ እንደሚያጠፉም ያስረዳሉ።

ሥራ ቀጣሪና አባራሪ እየሆነ የመጣው ሮቦት

ሌላው የስብሰባ ጥቅም፤ ሰዎች ቅሬታቸውን የሚገልጹበት መድረክ መፍጠሩ ነው። ፕሮፌሰር ፓትሪክ፤ ዘለግ ያሉ ስብሰባዎችን እንደ ሥነ ልቦናዊ ህክምና ይወስዷቸዋል።

"ቅሬታ መግለጫ፣ በተቀሩት ሠራተኞች ዘንድ ቦታ ማግኛ መድረክም ነው" ሲሉ ስብሰባን ይገልጻሉ።

በእርግጥ ብዙዎች በስብሰባ እንደሚሰላቹ የሚጠቅሱት መራማሪው፤ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች የስብሰባን እውነተኛ ጥቅም አልተረዱት ይሆናል ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ፤ በስብሰባ ወቅት የተሳታፊዎች እኩልነት መጠበቅ እንዳለበት ይናገራሉ። የስብሰባ ተሳታፊዎች ማንሳት የሚፈልጉት አጀንዳ መንሸራሸር እንደሚገባውም ያክላሉ።

የሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ የቱ ነው?

ስብሰባ የጥቂቶች የበላይነት የሚንጸባረቅበት ከሆነ፤ በሂደቱ አለመካተታቸው የሚሰማቸውን ሰዎች እንደሚያስቀይም ይናገራሉ።