በዓመት 29 ብር የሚከፈላቸው ኬንያውያን ታራሚዎች

በዓመት 29 ብር የሚከፈላቸው የኬንያ ታራሚዎች Image copyright Getty Images

የኬንያ ፍርድ ቤት እሥረኞች የደሞዝ ጭማሪ ይደረግላቸው ዘንድ የቀረበለትን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል።

ሦስት የቀድሞ ታራሚዎች ናቸው ከአራት ዓመት በፊት ታራሚዎች በዓመት የሚከፈላቸው ገንዘብ ኢምንት ስለሆነ የደሞዝ ጭማሪ ያሻቸዋል ሲሉ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመሩት።

ፊርማ አሰባሳቢዎቹ አሁን ኬንያ የምትጠቀምበት የእሥረኞች ሕግ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትን የሚነካ ባርነት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ኬንያዊያን ታራሚዎች በዓመት የሚከፈላቸው ከአንድ ዶላር ያነሰ ገንዘብ፤ በቅጡ እንኳ 30 ብር አይሞላም። ይህ ሕግ የወጣው ደግሞ የዛሬ 40 ዓመት በ1979 (እአአ) ነው።

ኬንያዊያን ታራሚዎች በሚሠሯቸው ከብረት የጠነከሩና ውበት ያላቸው የእንጨት ውጤቶች ይታወቃሉ። እነዚህ ምርቶች ብዙውን ጊዜ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጥቅም የሚውሉ ናቸው።

በተለይ ደግሞ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እና ፍርድ ቤቶች ምርቶቹን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ታራሚዎቹ የመኪና ሰሌዳ ቁጥር የሚፃፍባቸው ብረቶችን በመሥራትም ይታወቃሉ።

ቅሬታውን ያቀረቡት የቀድሞ ታራሚዎች፤ አሁን እሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች መሠረዊ ፍላጎታቸው አልተሟላም፤ የገላም ሆነ የጥርስ ሳሙና የላቸውም። የመፀዳጃ ቤት ወረቀትም አያገኙም ሲሉ ፍርድ ቤቱን ሞግተዋል።

ከፊርማ አሰባሳቢዎቹ መካከል አንዱ የሆነው አሎይስ ኦንያንጎ ለ16 ዓመታት በእሥር በቆየበት ጊዜ አንድም ቀን ገንዘብ እንዳልተከፈለውና የእሥር ቤት አስተዳዳሪዎች ሕግ እንዲያከብሩ እንዲገደዱ እንደሚፈልግ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

ነገር ግን ችሎቱን የመሩት ዳኛ አሁን ባለው ሕግ መሠረት ደሞዝ የመጨመር ሥልጣኑ ያለው በማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪው እጅ ነው፤ አልፎም ደሞዙ የመንግሥት ግዴታ አይደለም ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገውታል።

ከሳሾቹ ይግባኝ ጠይቀው ክሱን እንደሚገፉበት ይፋ አድርገዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ