ሺህ ቃላት ከሚናገረው ፎቶ ጀርባ ያለው እውነታ

ከዚህ ሠርሣሪ ፎቶ ጅርባ ያለው እውነታ Image copyright EENADU NEWSPAPER/A SRINIVAS

ሃይድርባድ የተሰኘችው የደቡባዊ ሕንድ ግዛት ነዋሪ የሆነችው የአምስት ዓመቷ ሕፃን ፎቶ ሰሞኑን የሃገሬውን ሰው ጉድ አሰኝቷል

ፎቶው ይህች ሕፃን ትምህርት ገበታ ላይ ያሉ እኩዮችዋን ከውጪ አጮልቃ ስትመለከት ያሳያል።

ዲቭያ አሁን በመንደሩ ታዋቂ ሆናለች፤ ዕድሜ ከሺህ ቃላት በላይ ለተናገረው ፎቶ። ዓይን-አፋሯ ዲቭያ በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት በኩል ስታልፍ ነው እኩዮችዋ ሲማሩ አጮልቃ ስትመለከት የነበረው። በአንድ እጇ ጎድጓዳ ሳህን ይዛለች።

ይህ ፎቶ ቴሉጉ በተሰኘው ጋዜጣ የፊት ገፅ ላይ ከወጣ ወዲህ መነጋገሪያ ሆነ። ርዕሱ ደግሞ የተጠማ ዕይታ ይላል። ለጥቆ የማሕበራዊ ድር-አምባው አፍ ሟሟሻ ሆነ። የሕፃናት መብት ተሟጋች ነን ያሉ ድምፃቸውን በፎቶው በኩል አሰሙ።

ይሄኔ ነው ትምህርት ቤቱ ዲቪያን በነፃ ለማስተማር የወሰነው።

የዲቪያ አባት ግን ፎቶው ባመጣው ዕድልም ሆነ ጩኸት ደስተኛ አይደሉም። «እኔና የፅዳት ሠራተኛ የሆነችው እናቷ ከፍቶናል» ይላል።

«ፎቶውን ባየሁት ጊዜ አዘንኩኝ። ዲቫያ ቀን ተሌት ተራሩጠው መፃኢ ሕይወቷን የሰመረ ለማድረግ የሚሮጡ እናት እና አባት አሏት። ጋዜጣው ግን ወላጅ አልባ አስመስሎ ነው ያቀረባት።»

አባት፤ ዲቪያ 6 ዓመት እስኪሆናት እየጠበቅኩ ነበር እንጂ የማስተማር አቅም አለኝ ይላሉ። ዲቪያ ታላቅ ወንድም እንዳላትና ሁለተኛ ደረጃ ጨርሶ ኮሌጅ ለመግባት እየተጠባበቀ እንዳለ አባት ይናገራሉ።

ዲቪያና ወላጆቿ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ይኖራሉ፤ ትምህርት ቤቱም ከቤታቸው በቅርብ እርቀት ላይ ይገኛል። አካባቢው ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሕንዳዊያን የሚኖሩበት ነው።

የዲቪያ እናትና አባት ደፋ ቀና ብለው በወር 10 ሺህ ሩፒ ያገኛሉ፤ 4 ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው። እርግጥ ትምህርት ቤቱ የመንግሥት እንደመሆኑ ለሕፃናት ትምህርት በነፃ ስለሚሰጥ መክፈል አይጠበቅባቸውም።

የዲቪያ አባት እሷና ወንድሟን ጨምሮ የሟች ወንድሙን አምስት ልጆች ያሳድጋል። «እኔ ያለፍኩበትን ስለማውቅ የፈለገ ቢሆን ልጆቼ ትምህርት እንዲነፈጉ አልፈግም» ይላል።

የመንደሩ ሕፃናት ምሳ ሰዓት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤቱ ያቀናሉ። ብዙዎቹ ጎድጓዳ ሳህን ከእጃቸው አይጠፋም። ምክንያታቸው ደግሞ በመንግሥት የሚደገፈው ት/ቤት ምሳ ለተማሪዎች ስለሚያቀርብ ከዚያ ቢደርሰን በሚል ነው።

«ዲቪያ አልፎ አልፎ ምሳ ሰዓት ወደዚያ ትምህርት ትሄዳለች። ድንገት ፎቶ ተነሳችና መነጋገሪያ ሆነች።»

ምሳ ከቤታቸው ቋጥረው የሚመጡ ስላሉ የተረፈውን የመንግሥት ምሳ ተማሪ ባይሆኑም እንኳ ዲቪያና ጓደኞቿ ይጋሩታል። በአካባቢው በመንግሥት የሚተዳደር የሕፃናት ማቆያ ባለመኖሩ ሕፃናት መንደር ውስጥ ሲዞሩ ይውሉና ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ት/ቤቱ ያቀናሉ።

አባት ላክሽማንና የአካባቢው ሰዎች የዲቪያ ፎቶ እንዲህ መነጋገሪያ መሆኑ በአንድ በኩል አስከፍቷቸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ ምንም ቢሆን ልጆቻችንን ማስተማር አያቅተንም ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ለመንግሥት ማንቂያ ደወል ነው ይላሉ። በአካቢው አንድ እንኳ የሕፃናት ማቆያ ቢኖር ዲቪያና እኩዮቿ ሳህን ይዘው የመንግሥት ት/ቤት ደጃፍ ባልረገጡ ነበር በሚል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ