የተቀዛቀዘችው ሐዋሳ: በሕዝበ ውሳኔው ዋዜማ

የተቀዛቀዘችው ሐዋሳ: በሕዝበ ውሳኔው ዋዜማ Image copyright Getty Images

ነገ ረቡዕ [ኅዳር 10/2012] በሲዳማ ዞን ባሉ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በሚልቁ የምርጫ ጣቢያዎች በሚከናወነው ሕዝበ ውሳኔ ዋዜማ፤ የዞኑ መናገሻ ሐዋሳ ከአራት ወራት በፊት ከነበራት የተለየ መልክ የተላበሰች ትመስላለች።

ባለፈው ዓመት ክረምት አጋማሽ ገደማ ያለጊዜው መወለዱ ቆይቶም ቢሆን በታወቀ ፈንጠዝያ እና እርሱን ተከትሎ በመጣ ዋይታ ትንቀረቀብ ነበር - ሐዋሳ።

ሐምሌ 8/2011 ዓ.ም በከተማዋ ተገኝተው የነበሩ የቢቢሲ ዘጋቢዎች ለሲዳማ ዞን ክልልነት 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በርካታ ወጣቶች መንገዶችን አና መንደሮችን በሆታ እና በዳንኪራ ማድመቃቸውን ታዝበው ነበር።

ይህ የቡረቃ ስሜት ግን ዘለግ ያለ ዕድሜ አልነበረውም፤ ዕለቱን ተከትለው የመጡ ቀናት በተቃራኒው ግጭትን እና ደም መፋሰስን አዝለው የሐዘንን ማቅ አከናንበዋታል።

በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ከተሞች ውስጥ በተፈጠረ ነውጥ በርካቶች ተገድለዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ አንዳንዶችም ተለይተው መጠቃታቸውንም ገልፀዋል።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በወርሃ ኅዳር የሲዳማ ክልል ምሥረታን የሚበይን ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያከናወን ያሳወቀው ከነውጡ መቀስቀስ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ከሰሞኑ ዳግም ወደከተማዋ ያቀኑት የቢቢሲ ዘጋቢዎች ከተማዋ የስሜት ጡዘቷ ረግቦ፤ ክርረቷ ለዝቦ ስክነት ቢረብባትም፤ ውስጥ ውስጡን የሚርመሰመስ ውጥረት ግን እንዳልተለያት ልብ ብለናል ይላሉ።

ሐዋሳ እርግጠኛነት ናፍቋታል

ለወትሮው በበርካታ ጎብኚዎች የምትመረጠው፤ በተለይ በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት የምትደምቅ፤ የምትፍለቀለቀው ሐዋሳ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መፋዘዝ፤ መቀዛቀዟን በውስጧ የሚኖሩ አና የሚሰሩ ይናገራሉ።

ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ደጋግሞ የናጣት ብሔር ተኮር ነውጥ ብዙዎችን አስበርግጎ ደጇን ከመርገጥ ይመልሳቸው እንደያዘ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም።

ግልጋሎትን ማቅረብን ሙያቸው ያደረጉ ከሦስት ዓመታት በፊት የነበሩትን ጊዜያት "ያኔማ" በሚል የቁጭት ናፍቆት ያነሳሉ።

በሆቴል፤ ወደሐይቅ ዳር ብቅ የሚሉ ጎብኝዎችን ፎቶ በማንሳት እንዲሁም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪን [ባጃጅ] በመሾፈር ሙያዎች ላይ የተሠማሩ የተለያዩ ግለሰቦች የተገልጋዮቻቸው ቁጥር ከዓመታት በፊት የሚያውቁትን ያህል ያለመሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ።

ከከተማዋ ዕጣ ፈንታ ጋር በተገናኝ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነግሶ የቆየው የእርግጠኛነት ዕጦት በሕይወታቸው ውስጥ ረዘም ያሉ ዓመታትን ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎችን ከማሳለፍ እና እርምጃዎችን ከመውሰድ ያቀቧቸው ነዋሪዎች መኖራቸው እንደማይቀር ግምቱን ያስቀመጠው በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚሠራ ወጣት ነው።

ከሕዝበ ውሳኔው ውጤት ይፋ መሆን በኋላም በከተማዋ እና በአካባቢው የሚኖረው የፖለቲካ ብሎም የፀጥታ ሁኔታ ከአሁኑ ምክንያታዊ በሆነ ልክ ሊገምቱት የሚችሉት ባለመሆኑ የውሳኔ ቁጥብነትን ቢጋብዝ እንደማይደነቅ ይሄው ወጣት ጨምሮ ይገልፃል።

በተለይ በቅርብ ጊዜያት ከሕዝበ ውሳኔው መቃረብ ጋር በተገናኘ በነዋሪዎች ዘንድ የበለጠ የእንቅስቃሴ ቁጥብነት እንደሚስተዋል የነገረን ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ሲሆን፤ ከመሸ በኋላ ያለመንቀሳቀስን የመከሩን ነዋሪም አሉ።

ሕዝበ ውሳኔው በሚከናወንበት ዕለት መደበኛ የሥራ እና የትምህርት ክንውኖች እንደማይኖሩ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ሰኞ ዕለት በከተማ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ሌላኛው የሕዝበ ውሳኔውን በሰላማዊ መልኩ ከማጠናቀቅ ጋር በተገናኘ የተላለፈ ውሳኔ በከተማዋ ተወዳጅ የመጓጓዣ ዘዴ የሆኑትን የሞተር ብስክሌቶች እንቅስቃሴዎች መገደብ ነው።

እነዚህ እርምጃዎች ቢያንስ ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄድበትን ሳምንት የበለጠ ረገብ እንዲሁም ፀጥ ያለ ያደርጉታል ብሎ መገመት ይቻላል።

ሕዝበ ውሳኔው ተስፋም ስጋትም አዝሏል

ሐዋሳ ከተማ በሕዝበ ውሳኔ ዘመቻ ተጥለቅልቃለች ማለት ማጋነን አይሆንም። የሚደግፉትን ወገን የሚያሽሞነሙኑ መልዕክቶች በከተማዋ መንገዶች፤ አደባባዮች እና ሕንፃዎች ላይ የተሰቀሉ በርካታ ዓይነ-ግቡ እና ግዙፍ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች አትኩሮትን ለመጥራት አይቸገሩም።

ሕዝበ ውሳኔ ተኮር መልዕክቶቹ ግን በሰሌዳዎቹ ላይ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፤ በንግድ መደብሮች ደጆች ላይ ይታያሉ፤ ከአገልገሎት ሰጭ ተቋማት ስያሜዎች ጋር አብረው ሰፍረው ይስተዋላሉ፤ ነዋሪዎች በአልባሳታቸው አሳትመዋቸው ይዞራሉ፤ አሽከርካሪዎች በመኪኖቻቸው ላይ ለጥፈዋቸው ይከንፋሉ።

ይሁንና ሁለቱንም (ዞኑ አሁን ባለው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዘቦች ክልል እንዲቀጥል የሚፈልጉ እና ዞኑ ራሱን የቻለ ክልለ እንዲሆን የሚሹ) ወገኖች የሚወክሉትን የሻፌታ ማሰሮ እና የጎጆ ምስሎች በእኩል መጠን ጎን ለጎን ተሰድረው ማግኘት የሚቻለው በከተማዋ ባሉ የምርጫ ጣብያዎች ነው።

በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች በጥቂቱ እንኳ መዟዟር የቻለ ሰው ዘመቻዎቹ በሁለቱ ወገኖች መካከል በእኩል መጠን እንዳልተካሄዱ ግምት መውሰድ ይችላል።

ሕዝበ ውሳኔው ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀው ያንቆለጳጰሱት የመኖራቸውን ያህል፤ ሕዝበ ውሳኔው ካለፈ በኋላ የሚኖረው ሕይወታቸው ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖረው በስጋት ማሰብ ማሰላሰል የነጋ ጠባ ግብራቸው መሆኑን ያጫወቱንም አሉ።

ይህ ወደፊት ችግር ሊገጥመኝ ይችላል የሚል ስጋት አሁን አቋማቸውን በልበ ሙሉነት እና በምሉዕ ነፃነት እንዳያንፀባርቁ ቀፍድዶ እንዳሰራቸው የገለፁልን ግለሰብ አሉ።

የሰላም ረሃብ

የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ሕዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ ተናግረው አይጠግቡም።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ በሰኞው መግለጫቸው ወቀት ከፀጥታ እና የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ እስካሁን ያጋጠመ እዚህ ግባ የሚባል ችግር ያለመኖሩን ተናግረዋል።

ከነዋሪዎች አንደበት ተደጋግሞ የሚሰማው ሰላምን የተመለከተ አስተያየት መታከትን የሚያመላክት ይመስላል። ከዚህ ባሻገርም ተስፋቸው በስጋት የተደቆሰባቸው ነዋሪዎችም ገጥመውናል።

አንድ ነዋሪ በከተማዋ አሁን የሚታየውን አንፃራዊ ሰላም ከወርሃ ሐምሌው ግጭት በኋላ በአካባቢው ተሰማርተው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር አስተሳስረው 'እርሱ ታዲያ እስከመቼ ነው የሚዘልቀው' ሲሉ አስተያየት ይሰጣሉ።

የምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

እርሱን ተከትሎ በአካባቢው ምን ዓይነት ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ኃብታዊ፤ ማሕበራዊ እና የፀጥታ ሁኔታ ይኖራል የሚለውን ጥያቄ ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ