ቤት ሲጠብቅ የነበረው አንበሳ በፖሊስ ተያዘ

ቤት ሲጠብቅ የነበረው አንበሳ በፖሊስ ተያዘ

የናይጄሪያዋ ከተማ ሌጎስ ውስጥ ቤት ሲጠብቅ ነበር የተባለው አንበሳ ተይዞ ወደ እንስሳት ማቆያ ተወስዷል።

የሁለት ዓመቱ ታዳጊ አንበሳ ይኖርበት የነበረው ቤት ከአንድ ትምህርት ቤት በተቃራኒ ያለ ነው።

አንበሳው በማደንዘዣ ጥይት ከተመታ በኋላ ቦጊጁ ኦሙ ወደተሰኘ የእንስሳት ማቆያ እንዲሄድ መደረጉን አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት የተያዘው አንበሳ ባለቤት ማንነት ያልታወቀ ሲሆን፤ ባለቤቱ ራሱን አሳልፎ ለፖሊስ እንዲሰጥ አሊያ የእሥር ትዕዛዝ እንደሚወጣበት የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።

የሌጎስ ስቴት ኢንቫይሮሜንታል ሳኒቴሽን አባል የሆኑ ባለሙያዎችና የመንደሪቱ ነዋሪዎች ለመንግሥት አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ ነው አንበሳው በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው።

የነዋሪዎችና ባለሙያዎች ቅሬታ በተሰበሰበ ፊርማ የደረሰው የናይጄሪያ የተፈጥሮ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የዱር እንስሳት ተንከባካቢ ባለሙያዎች ልኮ አንበሳው ራሱን እንዲስት ተደርጎ እንዲያዝ አስደርጓል።

አንበሳው ይኖርበት ከነበረው ቤት ተቃራኒ አንድ የሕፃናት ማቆያ እንዲሁም ትምህርት ቤት እንዳለ የቢቢሲ የናይጄሪያ ወኪል ዳሚሎላ ኦዱሎዋ ዘግባለች።

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ለተማሪዎች ደህንነት ሲባል አንበሳው ከሥፍራው በመነሳቱ እፎይ ብለዋል።

አንበሳው ከሁለት ወራት በፊት ነው መኖሪያው ከተያዘበት ቤት ያደረገው ተብሏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ