የምንሊክ ሀገር አንኮበርና ታሪካዊ ቅርሶቿ

በአንኮበር የሚገኘው ቤተመንግሥትና አሁን በግለሰብ ይዞታ ስር ሆኖ የሆቴል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ቤት
አጭር የምስል መግለጫ "ቤተ መንግሥት የነበረውን ቅርጽ አስይዘው ያስገነቡት ግለሰብ ናቸው። ... ወደፊት ቤተ መንግሥቱን በቅርስነት በመጠቀም ለእሳቸው ሌላ ለመስጠት ተነጋግረናል"

አንኮበር ከአዲስ አበባ በ172 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደብረ ብርሃን በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። በወረዳዋ ከ92 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩ ሲገመት ከባህር ጠለል በላይ በ3700 ሜትር ላይ ትገኛለች።

አንኮበር በተለያዩ ወቅቶች በማዕከላዊ ከተማነት እንዳገለገለች የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ።

ከ1262 ዓ.ም ከአጼ ይኩኖአምላክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ አንኮበር መናገሻ ሆና መቆየቷን የታሪክ መጻህፍትን እና ከአባቶች የሰሙትን ጠቅሰው ሊቀ ካህናት ቃለህይወት ሃብተወልድ ይገልጻሉ።

በዚህም ከ1262 እስከ 1521 ዓ.ም ድረስ በማዕከላዊ ከተማነት አገልግላለች።

የሠላም ተጓዧ ሉሲ (ድንቅነሽ) ምን ደረሰች?

ድሬ ዳዋ ስለሚገኙት የለገ ኦዳ የዋሻ ሥዕሎች ያውቃሉ?

በመሃል ማዕከላዊነቱ ወደ ጎንደር አቅንቶ ለ200 ዓመታት ያህል አንኮበር መናገሻ መሆኗ አክትሞ ነበር።

መርድ አዝማች አምሃ ኢየሱስ መቀመጫቸውን ከዶቃቂት ወደ አንኮበር አዛውረው በድጋሚ አካባቢውን መናገሻ አደረጉት ይላሉ ሊቀ ካህናት ቃለህይወት።

ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የተለያዩ ነገስታት ቤተ መንግሥታቸውን በአንኮበር ገንብተዋል። የገነቡት ቤተ መንግሥት ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈርስ ነገስታቱም በተደጋጋሚ አሳንፀውታል፤ አድሰውታል።

መርድ አዝማች አምሃ ኢየሱስ ወደ አንኮበር አቅንተው መቀመጫቸውን በዚያው ካደረጉ በኋላ አምስት የተለያዩ ነገስታት መቀመጫቸው በዚያ አድርገዋል።

መርድ አዝማች አስፋው ወሰን፣ ወሰን ሰገድ፣ ሳህለ ስላሴ፣ ሃይለ መለኮት እና ምኒሊክ የሸዋ ንጉስ በመሆን አንኮበር ዙፋናቸውን በማድረግ መርተዋል።

በመሃል ለአጭር ጊዜ መቀመጫቸውን ወደ ቁንዲ ከቀየሩት ወሰን ሰገድ ውጭ፣ አንኮበር ሲሶ መንግስት እና የሸዋ ማዕከል በመሆን ከ1733 እስከ 1881 ዓ.ም አገልግላለች።

በዚህ ወቅትም የተለያዩ ታሪካዊ ሥራዎች በአካባቢው ተከናውነዋል።

ታሪከ ብዙዋ አንኮበር

ከአንኮበር 12 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው አልዩ አምባ የጉምሩክ ሥራ የተጀመረበት ሲሆን እስከ ዘይላ ወደብ ድረስ ይነገድበት እንደነበር የአንኮበር ወረዳ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈለቀ ምህረት ይገልጻሉ።

ቢቢሲ በስፍራው በተገኘበት ወቅት "በጊዜው ይነግዱበት የነበረበት ደረሰኞች አሁንም ድረስ በማስረጃነት አሉ" ብለዋል።

በአንኮበር ካሲት ሰቀላ ለሶስት ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት የሚከታተሉ ሰዎችም በተለያዩ የአስተዳደር ቦታዎች ይመደቡ እንደነበር ይነገራል።

የመይሳው ካሳ የልጅ ልጆች

በአንድ ወቅትም ሶስት ሃገራት ኤምባሲያቸውን በአንኮበር ከፍተው እንደነበር አቶ ፈለቀ ይገልጻሉ። "የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የጣሊያን ኤምባሲዎች በአካባቢው ነበሩ። እነዚህ አካባቢው ትልቅ ቦታ እንደነበር ያሳያሉ" ይላሉ።

በአካባቢው የተለያዩ ታሪካዊ ቁሳቁሶችም በስፋት የሚገኙበት ነው።

"በጣም ብዙ ቅርስ በአካባቢው አለ። በወረዳው ብቻ ወደ 97 የሚደርሱ አብያተ ክርስትያናት አሉ። የብራና መጽሐፍት፣ ኒሻኖች፣ የብር ከበሮ፣ የብርና የወርቅ ፀናጽል እነዚህ ሁሉ አሉ" ይላሉ።

በአያያዝ ጉድለት ግን የተወሰኑት ታሪካዊ ቅርሶች ተሰርቀዋል።

"ከአስር ዓመት በፊት የብራና መጽሐፍት፣ መስቀል፣ ስንክሳር፣ ተአምረ ማርያም እና ዳዊት ጠፍቶ ነበር" ይላሉ አቶ ፈለቀ።

ህብረተሰቡን በማስተማር እና ለቅርስ ጥበቃ የሚደረገውን ጥበቃ በማሻሻል ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የቅርስ መጥፋት አጋጥሞ እንደማያውቅ የሚናገሩት ኃላፊው ይህንን በዘላቂነት ለማስጠበቅ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ ተመድቦ የሙዚየም ግንባታ ተጠናቋል።

"የሙዚየሙ ግንባታ ተጠናቋል። የሙዚየሙ መተዳደሪያ መመሪያ እስኪጸድቅ እየጠበቅን ነው" የሚሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት መኳንንቴ ናቸው።

የጣሊያኖች ጦርና ውድመት በአንኮበር

አጼ ምንሊክ መቀመጫቸውን ከአንኮበር ወደ እንጦጦ ካዘዋወሩ በኋላ የነበረው ቤተመንግሥትም በጣሊያን ወረራ ወቅት እንደወደመ ይነገራል።

በቦታው ላይ አሁን የቀድሞውን የሚመስል ቤተ መንግሥት ተገንብቷል።

አንኮበር ቤተ መንግሥት አካባቢውን ለመቆጣጠር እንዲያመች እና ነገስታቱን ከጠላት ለመጠበቅ እንዲያስችል በተራራ ጫፍ ላይ ነው የተገነባው።

በግቢው ውስጥ ንጉስ ሳህለ ስላሴ እንደ ቢሮ ይጠቀሙበት የነበረበት እልፍኝ ፍርስራሽ ይገኛል። እልፍኙን አጼ ምንሊክም ለትንሽ ጊዜ ተጠቅመውበታል።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

ሌላው በግቢው ውስጥ የሚገኝ ቅርስ በእንቁላል እና በኖራ የተሠራው የቤተ መንግሥቱ አጥር ነው። አጥሩንም ንጉስ ሳህለ ስላሴ እንዳስገነቡት የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ።

"የቱሪስት ፍሰቱ የተቀዛቀዘ ነበር። ማዕከላዊነቱ ወደ አዲስ አበባ ከመዞሩም በላይ መንገዱ አመቺ አለመሆኑ ለዚህ ምክንያት ነው" ይላሉ አቶ ፈለቀ ምህረት።

ቤተ መንግሥቱ ቀደም ሲል የነበረውን ቅርጽ ይዞ የአካባቢው ተወላጅ በሆኑት ኢንጂነር ተረፈ አፈወርቅ በድጋሚ ተገንብቷል።

"ቤተመንግሥቱን ካቋቋሙት በኋላ በርካታ ጎብኚዎች ሊጎበኙ ይመጣሉ። ከአዋሽ ደብረ ብርሃን መንገድ እየተሠራ ነው። ብዙ ኢንቨስተሮችም በአካባቢው መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እየጠየቁ ነው" ይላሉ።

ቤተ መንግሥቱ የበፊት ቅርጹን ይዞ በአዲስ መልክ ከተገነባ በኋላ ለእንግዶች ክፍት ቢሆንም ያስገነቡት ግለሰብ ሆቴል አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

በዚህ ምክንያትም የቅርሱ ቦታ አሁን ሙሉ ለሙሉ በግለሰብ እጅ ይገኛል።

"ቤተ መንግሥት የነበረውን ቅርጽ አስይዘው ያስገነቡት ግለሰብ ናቸው። በዚህ ምክንያት ገቢ ማግኘት አለባቸው። ከስምምነት ባይደረስም ወደፊት ቤተ መንግሥቱን በቅርስነት በመጠቀም ለእሳቸው ሌላ ለመስጠት ተነጋግረናል" ይላሉ አቶ ፈለቀ።

"ቤተ መንግሥቱ በግለሰቡ መሠራቱ ሁለት መልክ አለው" የሚሉት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት ናቸው። "ሁለት መልክ አለው። ባለሃብቱ ቤተ መንግሥቱን በቀድሞው ቅርጽ ባይሠሩት እንደፈረስ ይቀር ነበር። ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ በግለሰብ እጅ መግባቱ ነው" ይላሉ።

"በግለሰብ መሠራቱን መኮነን የለበትም። ታሪካዊው ቦታ በግለሰብ እጅ መሆኑ ግን ተገቢ አይደለም። ይህ ግን በፊት ነበር መሠራት የነበረበት። ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት ምክክር ያስፈልጋል። ከዞን እስከ ፌደራል ድረስ በጋራ ውይይት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ