ሆንግ ኮንግ በእድሜ ትንሹን ተቃዋሚ አሠረች

የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚዎች Image copyright Getty Images

ሆንክ ኮንግ፤ በእድሜ ትንሹን ግለሰብ መንግሥትን በመቃወም ከተደረገው ሰልፍ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ማዋሏ ተዘገበ።

ማንነቱ ያልታወቀው የ12 ዓመት ታዳጊ፤ የታሠረው ባለፈው ወር ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ነበር። ታዳጊው፤ በፖሊስ ጣቢያ እና በባቡር ጣቢያ መፈክሮችን መጻፉን ያመነ ሲሆን፤ በቀጣዩ ወር ይፈረድበታል።

የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ከተጀመረ ወዲህ፤ ከ5,000 በላይ ሰዎች ታስረዋል። አብላጫውን ቁጥር የያዙት እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 የሚደርሱ ታዳጊዎች ሲሆኑ፤ እስካሁን ክስ የተመሠረተበት እስረኛ ግን አልነበረም።

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ፡ «ሰልፈኛ አስመስለን ፖሊስ አሰማርተናል»

የሆንግ ኮንግ 'የተቃውሞ' ኬክ ከውድድር ታገደ

"አጭበርባሪ ፖሊሶች"፣ "ሆንግ ኮንግ ነጻ ትውጣ" የሚሉ መፈክሮችን ሲጽፍ ፖሊስ እንዳየው በክሱ ተመልክቷል። ፖሊሲ ታዳጊውን ቤት ድረስ ተከትሎ፤ በነጋታው ከቤት እስኪወጣ ድረስ እንደጠበቀውም ተገልጿል።

ታዳጊው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ፤ ፖሊሱ ካስቆመው በኋላ፤ ቤቱን ሲፈትሽ ጥቁር ቀለም እንዳገኘም ተገልጿል።

የታዳጊው ጠበቃ ጃኩሊን ላም፤ ታዳጊው አንድ ምሽት በእስር ቤት ማሳለፉ ትምህርት እንደሚሆነው በመግለጽ፤ "ፍርድ ቤቱ አንድ እድል እንዲሰጠው እጠይቃለሁ" ብለዋል።

ተቃውሞ በቻይና፡ መንግሥት 'የውጭ ኃይሎችን' እየወቀሰ ነው

''ፕሬዝደንት ትራምፕ እባክዎ ሆንግ ኮንግን ይታደጉ'' ሰልፈኞች

የሆንግ ኮንግ ታራሚዎች ለቻይና ተላልፈው እንዲሰጡ የቀረበን ረቂት ተከትሎ፤ ሆንግ ኮንግ ለወራት በተቃውሞ እየተናጠች ነው። ረቂቁ ውድቅ ቢደረግም ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው አደባባይ መውጣታቸውን ቀጥለዋል።

በዚህ ሳምንት በዩኒቨርስቲዎች በተካሄደው ተቃውሞ ላይ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስና የፕላስቲክ ጥይት ተኩሰው ነበር። ተቃዋሚዎችም ፖሊሶች ላይ ተቀጣጣይ ነገሮችና ቀስት ወርውረዋል።

እስካሁን ወደ 1,000 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከዩኒቨርስቲው ሸሽተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩት ተቃዋሚዎች ከ18 ዓመት በታች ናቸው ብሏል ፖሊስ ።

ተያያዥ ርዕሶች