የዘጠኝ ዓመቱ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ

በቀጣይ ወር በእድሜ ትንሹ ተመራቂ የሚሆነው ታዳጊ ላውረንት ሳይመን Image copyright EVN
አጭር የምስል መግለጫ በቀጣይ ወር በእድሜ ትንሹ ተመራቂ የሚሆነው ታዳጊ ላውረንት ሳይመን

ላውረንት ሳይመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ አራት ዓመቱ ነበር። ሆኖም የእድሜ እኩዮቹ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳይሆኑ እሱ በዘጠኝ ዓመቱ ዲግሪ ሊጭን ነው።

ላውረንት እንደ ማንኛውም ልጅ የአንደኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው በአንድ ዓመት ውስጥ ነበር። ወደ ሁለተኛ ክፍል ከተሸጋገረ በኋላ ግን ነገሮች ተለወጡ። በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርት ጨረሰ።

በስድስት ዓመቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የተቀላቀለው ላውረንት፤ ስድስት ዓመት ይወስድ የነበረውን ትምህርት በ18 ወር ውስጥ አገባደደ። ከዛም የስምንት ዓመቱ ታዳጊ ለስድስት ወር አረፍ ብሎ ዩኒቨርስቲ ገባ።

ከስምንት ወር በፊት ዩኒቨርስቲ የገባው ላውረንት፤ በዘጠኝ ወር የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን አጠናቆ በቀጣዩ ወር በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ይመረቃል።

ታዳጊው፤ በምን ተአምር በዘጠኝ ዓመቱ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ለመሆን አንደበቃ አያውቅም። ከቢቢሲ ጋር በነረው ቆይታም "እንዴት እንዳሳካሁት አላውቅም" ሲል ተናግሯል።

የዘንድሮ ተመራቂዎች እንዴት ሥራ ያገኛሉ?

ከበለስ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የምትመራመረዋ ኢትዮጵያዊት

ኢንጂነሪንግ፣ ህክምና ወይስ ሁለቱንም?

ላውረንት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዴት የሰው ልጆችን መርዳት እንደሚቻል መመራመር ያስደስተዋል። ለመመረቂያው የሠራውም የሰው ልጆችን የአዕምሮ እንቅስቃሴ የሚለካ መሣሪያ ነው።

Image copyright Laurent Simons
አጭር የምስል መግለጫ ላውረንት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዴት የሰው ልጆችን መርዳት እንደሚቻል መመራመር ያስደስተዋል

ከሀኪም ቤተሶች የተወለደው ላውረንት፤ ለሦስተኛ ዲግሪው ህክምና የማጥናት እቅድ አለው።

"ህልሜ ሰው ሰራሽ የሰውነት ክፍሎችን መሥራት ነው" የሚለው ታዳጊው፤ የሰው ልጆች ልብ፣ ኩላሊት ሲያስፈልጋቸው በመተካት የተሻለ ሕይወት መስጠትና እድሜያቸውን ማራዘምም ይሻል።

"ቅድመ አያቶቼን ጨምሮ የሌሎችን ሰዎችም እድሜ ማርዘም እፈልጋለሁ" ይላል።

ላውረንትን ያሳደጉት አያቶቹ ናቸው። ገና ህጻን ሳለ ጀምሮ ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ተረድተውም እንደነበር አባቱ አሌክሳንደር ሳይመን ይናገራሉ።

Image copyright Laurent Simons
አጭር የምስል መግለጫ ላውረንት ከቅድመ አያቶቹ ጋር

ላውረንት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሲጀምር፤ ልዩ ተማሪ መሆኑን አስተማሪዎቹ ለቤተሰቦቹ ገለጹ። ቤተሰቦቹ ለምን ፈጣን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። ችሎታው እነሱን ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎችንም ያስደመመ ነበር።

ከአንደኛ ክፍል ዲግሪ እስኪጭኑ ከልጃቸው ጋር የተማሩት አባት

"እቴጌ" ካንሰርን ለመታገል የተሰራ የስልክ መተግበሪያ

ታዳጊው ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ (ፎቶግራፊክ ሜሞሪ) ያለው ሲሆን፤ አይኪው ሲለካ 145 ነው። ሂሳብና ሳይንስ የሚወደው ታዳጊው፤ ለቋንቋ ግን የተለየ ፍላጎት አያሳይም።

አባቱ እንደሚናገሩት፤ አንዳንድ ቀን ትምህርት ቤት ቀርቶ ባህር ዳርቻ ሄዶ መዝናናት ይፈልግ ነበር። ዩኒቨርስቲ ሲገባ ግን የተለየ መርሀ ግብር መከተል ጀመረ።

"ሰኞ የትምህርቱን መግቢያ ይወስድና ማክሰኞ ቤተ ሙከራ ይገባል። እሮብ ቤት ሆኖ ለስምንት ሰዓት ያጠናል። ሀሙስ ለትምህርት ክፍሉ ጥያቄ ያቀርብና አርብ ይፈተናል" ሲሉ አባቱ ያስረዳሉ።

ሌሎች ተማሪዎች ይህንን ሂደት ለማጠናቀቅ ከዘጠኝ እስከ 12 ሳምንት ይወስድባቸዋል።

የክፍል ጓደኞቹ ባጠቃላይ በእጥፍ እድሜ የሚበልጡት ላውረንት፤ ትምህርቱን የሚከታተለው ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ ክፍል ውስጥ ነው።

Image copyright Laurent Simons
አጭር የምስል መግለጫ ላውረንት በውሀ ዳርቻ ሲዝናና

አባቱ እንደሚሉት፤ እንደ ሌሎች ልጆች የሚጫወትበት ጊዜም አለ። ቤተሰቦቹም ጫና አያሳድሩበትም።

ታዳጊው ኢንስታግራም ላይ 35ሺህ ተከታዮች አሉት። ሲዝናና የሚያሳዩ ፎቶዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹም ይለቃል። ለጓደኞቹ፤ በቴሌቭዥን ቃለ መጠይቅ እንደተደረገለት በኩራት እንደሚያወራም አባቱ ይናገራሉ።

ሞዛርት በአምስት ዓመቱ ሙዚቃ ያቀናብር ነበር። ፒካሶም የመጀመሪያ ሥዕሉን የሠራው በዘጠኝ ዓመቱ ነው። ቢሆንም ሌሎች በልጅነታቸው እውቅና ያተረፉ ሰዎች በእድሜ ከፍ ሲሉ ይጠፋሉ። ምናልባት ላውረንት በእድሜ ከገፋ በኋላም ስኬታማ ሆኖ እናየው ይሆን?

አባቱ እንደሚሉት፤ ላውረንት አደርጋለሁ ያለውን ነገር ሳያሳካ ቀርቶ አያውቅም።

ተያያዥ ርዕሶች