ከኮርኔል በኮምፒውተር ሳይንስ ፒኤችዲ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት የሆነችው ረድኤት አበበ

ረድኤት አበበ

የፎቶው ባለመብት, Rediet Abebe

የምስሉ መግለጫ,

ረድኤት አበበ

የ28 ዓመቷ ረድኤት አበበ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። ኮምፒውተር ሳይንቲስቷ ረድኤት፤ በአልጎሪዝም እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ዙርያ ትሠራለች። ረድኤት ከኮርኔል ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ፒኤችዲ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ስትሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ከሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሒሳብ ነው።

ሁለተኛ ዲግሪዋን በአፕላይድ ማቲማቲክስ የሠራች ሲሆን፤ ጥናቶቿ ኤአይን ጨምሮ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያለ ጾታና የቆዳ ቀለም መድልዎ፣ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አብዛኛውን ማኅበረሰብ መጥቀም የሚችሉበት መንገድ ላይ ያተኩራሉ። ረድኤት፤ ፍትሐዊ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ላይ የሚያተኩሩ 'ሜካኒዝም ዲዛይን ፎር ሶሻል ጉድ' እንዲሁም 'ብላክ ኢን ኤአይ' የተሰኙ ተቋሞችን ከሙያ አጋሮቿ ጋር መስርታለች። በሥራዎቿ ዙርያ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ቢቢሲ፡ ታህሳስ ከኮርኔል በኮምፒውተር ሳይንስ ፒኤችዲ ትይዣለሽ። በዘርፉ ከዩኒቨርስቲው በፒኤችዲ የምትመረቂ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ነሽ፤ እንኳን ደስ አለሽ።

ረድኤት አበበ፡ አመሰግናለሁ!

በርካታ ጥቁር ሴቶች እንደ ኮርኔል ካሉ ትልቅ ዩኒቨርስቲዎች ለምን በዘርፉ አልተመረቁም?

ችግሩ የኮርኔል ብቻ አይደለም። አሜሪካ ውስጥ ሲአርኤ የሚባል ተቋም አለ። በየዓመቱ በፒኤችዲ ተመራቂዎች 'ሰርቬይ' [ጥናት] ይሠራል። ወላጆችሽ የኮሌጅ ተማሪ ነበሩ? ዲግሪሽን በምን ጨረስሽ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ይጠይቃሉ።

ጾታና የቆዳ ቀለምም ይጠይቃሉ። ከዛ ውጤቱን በድረ ገጽ ይለጥፋሉ። ውጤቱን ሳይ. . . በየዓመቱ በመላው አሜሪካ በኮምፒውተር ሳይንስ ፒኤችዲ የሚመረቀው ጥቁር ሴት አምስት ብቻ ነው። በዓመት በኮምፒውተር ሳይንስ በፒኤችዲ የሚመረቀው ሰው ባጠቃላይ ወደ 3,000 ይሆናል።

ከዛ ሁሉ አምስቱ ብቻ ጥቁር ናቸው። ሌላው ችግር ፕሮፌሰሮች ናቸው። አሜሪካ ውስጥ ቢያንስ ከ 5,000 በላይ የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮፌሰር አለ። ከነዚህ ጥቁሮች 75 ብቻ ናቸው። ከነዚህ ጥቁር ሴቶች 20ም አይሆኑም።

ብዙ እንደኔ አይነት ሰው ወደ ፒኤችዲ መግባት ሲፈልግና የኮርኔልን፣ የፕሪንስተንን፣ የሀርቫርድን ፕሮግራሞችን ሲያይ፤ አንድ ጥቁር ፕሮፌሰር ቢኖራቸው ነው። በአብዛኛው ግን ዜሮ ነው። ስለዚህ 'ሮል ሞዴል' [አርአያ] የለም ማለት ነው። ስታመለክቺም መድልዎ አለ። ሰው የራሱን አይነት ሰው ነው መመዘን የሚችለው። ሰው ራሱን የሚመስል ሰው ይወዳል።

ማመልከቻውን የሚያነቡት ሰዎች በሙሉ ጥቁር ካልሆኑ፤ ጥቁር ሰው ላይ መድልዎ ይኖራል ማለት ነው። ዩኒቨርስቲ ከገባሽ በኋላም ብዙ ድጋፍ ላታገኚ ትችያለሽ። ስለዚህ ይከብዳል። ብዙ ጥቁር ሴት ላያመለክት ይችላል። ካመለከቱም ላይገቡ ይችላሉ። ከገቡም ላይጨርሱ ይችላሉ። ለመጨረስም ብዙ ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል። ኮርኔል ለመጨረስ የሚፈጀው አምስት ዓመት ነው። ግን ጥቁር ከሆንሽና ድጋፍ የማይሰጡሽ ከሆነ እስከ ስምንት ዓመትም ሊፈጅ ይችላል።

የነገርሽኝን መሰናክሎች በሙሉ አልፈሽ ልትመረቂ ነው። እንደ አንድ ጥቁር ሴት ያለሽበት ቦታ መድረስ ምን ስሜት ይሰጥሻል?

መመረቂያ ጽሑፌን ሳቀርብ ስለዚህ ጉዳይ ተናግሬያለሁ። በአንድ በኩል ሳስበው ለኔ ትልቅ ነገር ነው። ለፒኤችዲ ብዙ ዓመት ነው የሠራሁት። ስለዚህ ደስ ብሎኝ ነበር። ጓደኞቼ ኮርኔል ውስጥ በሌላ ትምህርት ክፍል ያሉትን ጨምሮ ጥቁር ተማሪዎችን ጠርተው ነበር። የኔ አድማጭ ግማሹ ጥቁር ነበር። ቀኑን ማክበር ፈልገው ነበር። ፕሮፌሰሮችም ነበሩ። አብዛኞቹ ፕሮፌሰሮች ከዛ ትምህርት ክፍል የምመረቀው የመጀመሪያ ጥቁር ሴት እኔ እንደሆንኩ አላወቁም ነበር።

ምክንያቱም ስለዚህ ጉዳይ አያስቡም። እኔን ይሄ ነገር እንደሚረብሸኝ አይረብሻቸውም። ነገሩ [ከዛ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት መመረቋ] የሚያስደስት ነገር ሊመስል ይችላል። እኔ ሳስበው ግን ጥሩ ነገር አይደለም። እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ጨረስኩ፤ ግን ስንት ጥቁር ሴት ለዚ ትምህርት አመልክታ አልገባችም? ስንት ጥቁር ሴት ጀምራ አልጨረሰችም? ይሄን ሳስብ በጣም ያሳዝናል። በ2019 [እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር] የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት መመረቋ ጥሩ አይደለም።

መመረቂያ ጽሑፌን ሳቀርብ "አያቶቼ እንኳን ኮሌጅ አንደኛ ደረጃም አልተማሩም" ብዬ ተናገርኩ። እኔ ግን ሁለቱንም እንደ ሳይንቲስት ነበር የማስባቸው። የአባቴ እናት መሶብ ትሠራ ነበር። ተሰጥኦ ነበራት። መሶቦቹን ጂኦሜትሪክ ዲዛይን ነበር የምታደርገው። በጣም ያምራል። አንድ ቀንም ይህንን ዲዛይን ስትጽፍ አላየሁም። ቁጭ ብላ መሥራት ትጀምራለች፤ ትጨርሳለች።

በመደበኛ [ትምህርት ቤት] ሳይንስ ባታጠናም እንደ ሂሳብ ባለሙያ ነበር የምታስበው። የአባቴ አባት ደግሞ አርሶ አደር ነበር። ትልቅ እርሻ ነበረው። የሚያርሰው ራሱ በሠራው መሣሪያ ነበር። ትራክተር የገዛው በጣም ካረጀ በኋላ ነበር። አያቶቼ ባይማሩም እንደ ሳይንቲስት ያስቡ ነበር። አዲስ አበባ ሳድግ፤ እናትና አባቴን ሳይም ራሴን እንደ ሳይንቲስት አይ ነበር።

አሜሪካ ስመጣ ግን የተነገረኝ ጥቁር ሰው ሳይንስ አይችልም፤ ሴት ሳይንስ አትችልም ተብሎ ነበር። ኢትዮጵያ ሳድግ ግን ሴት፣ ወንድ፤ አማራ፣ ኦሮሞ ተብሎ ሳይከፋፈል ሁሉም ሳይንስ መሥራት እንደሚችል ነበር የማስበው። መመረቂያ ጽሑፌን ሳቀርብም የነገርኳቸው ይህንኑ ነው። "ሳድግ ሳይንቲስት ለመሆን አስብ ነበር። አሜሪካ መጥቼ 'አንቺ ሳይንስ አትችይም' ስባል በጣም ገረመኝ፤ አሳዘነኝም። ይሄንን ነገር መለወጥ አለባችሁ። ምክንያቱም እናንተ እንደ ሳይንቲስት ባታዩኝ እንኳን ራሴን እንደ ሳይንቲስት ነው የማየው" አልኳቸው።

የፎቶው ባለመብት, Rediet Abebe

የምስሉ መግለጫ,

ረድኤት አበበ

አርቴፍሻል ኢንተለጀንስን (ኤአይ) ጨምሮ ዘመነኛ ቴክኖሎጂዎች አካታች እንዳልሆኑ (በተለይ ጥቁሮችና ሴቶችን)፣ ኢ-ፍትሐዊነት እንደሚስተዋልባቸውም የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ። ቴክኖሎጂው አካታች መሆን ያልቻለው ለምንድን ነው?

ጉዳዩ ብዙ ችግር አለበት። ኤአይ በዳታ ላይ የተመረኮዘ ነው። አልጎሪዝም ስትሰጪ ዳታውን ይወስድና ከዳታ ውስጥ ፓተርን ያያል። እሱን ይዞ ክሬዲት ያደርጋል። ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ወደ 15 በመቶው ጥቁር ሰው ነው። ዳታውን ስታይ በጣም ትንሽ ጥቁር ሰው ነው የምታይው። ዳታው ብዙ ጥቁር ሰው አካታች አይደለም። ማሽን ለርኒንግ አልጎሪዝም 'ትሬን' ስታደርጊ [ሲሠራ]፤ የማያየውን ሰው ጉዳይ በደንብ አያጠናም።

በዚህ ተመርኩዞ 'ፕሪዲክት' ሲያደርግ [ሲገምት] ጥሩ አይሆንም። ለምሳሌ ትምኒት ገብሩ ፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂ ላይ አንድ ሥራ አላት። ፌሻል ሪኮግኒሽን ቴክኖሎጂው ያጠናው በአብዛኛው ነጭ ወንዶችን ነው። ስለዚህ ጥቁር ሴት ስትሰጪው ትክክለኛ አይሆንም። እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂን የሚሠሩ ሰዎች ጥቁሮች አይደሉም፤ ሴቶች አይደሉም። ስለዚህ ቴክኖሎጂዎቹ አካታች አይደሉም።

ለምሳሌ አማዞን አንድ መሣሪያ ሠርቶ ነበር። ጾታን መሰረት ያደረገ መድልዎ እንዳይፈጠር ተብሎ ጾታና ስም [ከመሣሪያው] ጠፋ። ግን የኮሌጅ ስም አልጠፋም ነበር። አንዳንድ ኮሌጆች ደግሞ የሴቶች ብቻ ናቸው። ስምና ጾታ ቢጠፋም የኮሌጁ ስም ፕሮክሲ ይፈጥራል። ይህንን ሳያውቁ ይጠቀሙበት ነበር። ከዛ ሴቶችን ማግለል ሲጀምር [ክፍተቱ] ታወቀና ጠፋ። ግን ይህ ቴክኖሎጂ ሲሠራ ሴት ብትኖር፣ መናገር ብትችል ይሄንን ጉዳይ ትይዘው ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ "ሂውማን ሴንተርድ ኤአይ" [ሰውን ያማከለ ኤአይ] የሚለው ሀሳብ በተደጋጋሚ ይነሳል። አሁን ባለንበት ዘመን ቴክኖሎጂ ሰዎችን እንዲጠቅም የሚደረገው በምን መንገድ ነው?

"ሂውማን ሴንተርድ ኤአይ" የመጣው ለዚህ [አካታች ላልሆነ ቴክኖሎጂ] እንደ መልስ ነው። ድሮ ቴክኖሎጂ 'ዴቨሎፕ' ስናደርግ መጀመሪያ የምናስበው ቴክኖሎጂ ምን ይሠራል? ምን ያህል ሳይንሱን ማሳደግ ይቻላል? ብለን ነበር። አሁን የፈለግነው ግን ከሰው መጀመር ነው። ሰው ምንድን ነው የሚያስፈልገው? ምን ሰውን የሚጠቅም ነገር መሥራት እንችላለን?

መጀመሪያ የምታስቢው ነገር ስለ ሰው ነው ወይስ ስለ ቴክኖሎጂ ነው? ይሄ ለመጀመር ጥሩ ቦታ ነው። ግን ማሰብ ያለብን ስለየትኛው ሰው እንደምንነጋገር ነው። "ሂውማን ሴንተርድ ኤአይ" ብለሽ መጀመሪያ የምታስቢው ለወንዶች ከሆነ ካለንበት ቦታ ብዙም አይለወጥም። የምናስበው ከመጀመሪያውም የተገለሉ ሰዎችን ከሆነ ግን ሊለወጥ ይችላል።

ሁለት ዓለሞችን በምናብ እንድትስይልኝ አፈልጋለሁ። አንደኛው ኤአይ በቀዳሚነት ሰዎችን የሚጠቅምበት ዓለምሁለተኛው ደግሞ ኤአይ አካታች ያልሆነበትና በመድልዎ የተሞላ ዓለም።

ሁለተኛው ዓለም አሁን ያለንበት ነው። በአብዛኛው ፓወር የሚደረገው ዳታ፣ አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ፣ በጣም የተራቀቀው ቴክኖሎጂ ያላቸው እነ ጉግል እና ፌስቡክ ናቸው። ካምብሪጅ የሚኖር ጥቁር ልጅ የቴክኖሎጂው 'አክሰስ' [ተደራሽነት] የለውም። ጉግል የሰው ዳታ ወስዶ እየተጠቀመበት፤ አልፈልግም ማለት አይችልም። ድንጋጌም የለም።

ለምሳሌ እዚ አገር ቤት ፈልገሽ ስታመለክቺ አከራዩ የኤአይ ድርጅት መጠቀም ይችላል። ድርጅቱ አልሰጥሽም ማለት ይችላል። አልጎሪዝማችሁ ምንድን ነው የሚለው? ብለሽ መጠየቅ አትችይም። 'አክሰሱ' ያላቸው ጉልበት ያላቸው ተቋሞች ናቸው። በተለይ የተገለሉ ሰዎች (ሴቶች፣ ጥቁሮች፣ ስደተኞች) 'አክሰስ' የላቸውም።

የመጀመሪያው አይነት ዓለም ላይ መድረስ የምንችል ይመስለኛል። ትምህርትና ልማት ላይ ሁሉንም ሰው ካካተትን መለወጥ እንችላለን። ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ነገር ያሳስበኛል። አንድ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር በሚቀጥለው ወር ይዘንባል ወይስ አይዘንብም?፣ ከዘነበስ ምን ያህል ይዘንባል?፣ የገበያው ሁኔታስ ምን ይመስላል? የሚለውን ማወቅ ይፈልጋል።

እኔ የማስበው. . . የኤአይ ቴክኖሎጂን ዴሞክራሲያዊ አድርገን፤ ሁሉም ሰው 'አክሰስ' እንዲኖረው ካደረግን፤ እንኳን ትልቅ ድርጅት አንድ አርሶ አደርም መርዳት ይቻላል። እስኪ አንድ አርሶ አደር 'ዌብሳይት' [ድረ ገጽ] የሚጠቀምበት 'አክሰስ' ሲኖረው አስቢው። "መሬቱ ይህን ያህል ነው፤ ይሄ [ቦታ] ሰብል ይዟል ስትይው" በጣም ይረዳዋል። እኔ ለሁሉም ሰው 'አክሰስ' መስጠት የምንችልበት ዓለምን ነው የምፈልገው።

በመላው ዓለም ማለት በሚቻልበት ደረጃ የቴክኖሎጂ ፍርሀት እየተስፋፋ ይመስላል። ሥራችንን ልንነጠቅ ነው፣ ቴክኖሎጂ ከመጠን በላይ በሕይወታችን ገብቶ እያመሰቃቀለው ነው ወዘተ. . . በተደጋጋሚ የሚስተጋቡ ስጋቶች ናቸው። በእርግጥ ታሪክን እንደ ማሳያ ብንወስድ፤ ሰዎች ለውጥ ሲፈሩ ተስተውሏል። ፈጠራዎችን እንዲሁም አዲስ ነገሮችን ባጠቃላይ ለመልመድም ጊዜ ይወስዳል። አሁን እየታየ ያለው ግን ለውጥን መፍራት ሳይሆን መሰረት ያለው ስጋት ነው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። እና በርካቶች ዘመኑን መፍራታቸው ልክ ነው? አንቺስ ያለንበት ወቅት እንዲሁም የወደፊቱ ዓለም ያስፈራሻል?

መፍራታቸው ልክ ነው። እውነት ነው ሰው ለውጥ አይፈልግም። አይወድም። እንኳን ኤአይ ሌላ ቴክኖሎጂም ሲተዋወቅ እንደዛ ነው። አሁን በኤአይ ከላይ ወደታች ማለትም የሆነ ድርጅት 'ዴቨሎፕ' [አምርቶ] አድርጎ ይሰጠናል። እምቢ ማለት አንችልም። ግን ቴክኖሎጂውን 'ዴቨሎፕ' አድርገን ሰው ላይ በግዴታ ከመጫን ትምህርቱን አስፍተን፣ ሰው የሚፈልገውን ነገር ራሱ ቢሠራ፤ ያኔ ለውጡን ይወደዋል።

ምክንያቱም ራሱ የሠራው ለውጥ ነው። ለምሳሌ አንድ ትልቅ ድርጅት፤ ይህንን መሣሪያ ሠርተናል ውሰዱት ብሎ ለአርሶ አደሮች ሲሰጥ ሊያስፈራቸው ይችላል። ልክም ናቸው። ምንድን ነው የምትፈልጉት? ምን እንሥራላችሁ? ብለን አነጋግረናቸው፣ የነሱን ሀሳብ ወስደን፤ ሠርተን ተደራሽነቱን ብናሰፋ ወይም ራሳቸው 'ዴቨሎፕ' እንዲያደርጉት ብናደርግ ችግር አይኖርም።

ድሮ 'ታይፕ ራይተሮች' ነበሩን። አሁን ሁላችንም መጻፍ ስለምንችል አያስፈልገንም። እንደዚህ ሥራ ሲለወጥ ችግር የለውም። ሥራዎች ሲለወጡ ግን ሌላ ሥራዎች እየተፈጠሩ [መሆን አለበት]። ብዙ ቦታዎች የሶፍትዌር ኢንጂነር ሥራዎች ያስፈልጋቸዋል።

ጉግል ብቻ ሳይሆን ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችም ሶፍትዌር ኢንጂነር ያስፈልጋቸዋል። ግን ለነዚህ ሥራዎች 'አክሰስ' ያለው ማነው? ሁሉም ሰው ነው ወይስ ትንሽ ሰው? ስለዚህ አንዳንድ ሥራዎችን 'አውቶሜት' ስናደርግ ሁሉም ሰው 'አክሰስ' እንዲኖረው [አስበን] መጠንቀቅ አለብን። አሁን ግን እየተጠነቀቅን አይደለም። ሰው የሚፈራውም ለዚህ ነው። መፍራታቸውም ልክ ነው። ግን መለወጥ እንችላለን። አልረፈደም።

ኤአይ በየዘርፉ እየገባ ነው። የወደፊቱን ዓለም ስናስብም በብዙ መስኮች ማዕከላዊ ቦታ ይኖረዋል። ህክምናን እንደ ምሳሌ ብናነሳ፤ ኤአይ አፍሪካ ውስጥ በህክምና ዘርፍ ምን አይነት ሚና ሊኖረው ይገባል ትያለሽ?

በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ጽሑፍ አለኝ። 'ኦንላየን' [በድረ ገጽ] ሰዎችን በመጠየቅ ሰርች ዳታ ነበረን። ከ54 የአፍሪካ አገሮች እሱን ዳታ ወሰድንና ሰው ስለ ህክምና ምን አይነት ጥያቄ እየጠየቀ ነው? 'ኦንላየን' መረጃስ እንዴት ነው የሚያገኘው? ብለን አጠናን። አፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሪፖርት አላቸው።

እና አፍሪካ ላይ ዳታ የለም ይላሉ። ለምሳሌ ኤችአይቪ ኤድስን ብትወስጂ፤ እንኳን ዝርዝር ዳታ አይደለም፤ በአንድ አገር በየዓመቱ ስንት ሰው በኤድስ ሞተ? ብለሽ ብትጠይቂ መረጃውን ማግኘት በጣም ይከብዳል። ከተገኘም ስህተት ይኖረዋል። እና እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ብዙ ዳታ ቢኖረን ጥሩ ነው። ያኔ ያለንን 'ሪሶርስ' [ሀብት] መጠቀም እንችላለን።

እኛ [ጥናቱን የሠሩት ባለሙያዎች] ማየት የፈለግነው፤ ስለ ኤችአይቪ ኤድስ ሰው ምን አይነት መረጃ እየጠየቀ ነው? እንዴት አይነት መረጃ እየተሰጠው ነው? የሚለውን ነው። ስለ አፍሪካ የህክምና ጉዳይ ሳስብ መረጃ የለም። ቴክኖሎጂ የለም። ቴክኖሎጂ ካለ ደግሞ ላይሠራ ይችላል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ መብራት ይጠፋል። [ስለዚህ] በባትሪ የሚሠራ ነገር ሊሠራ ይችላል።

ኢንተርኔት ከጠፋ 'ኮኔክሽን' የማያስፈልገው ነገር መሥራት ትችያለሽ ወይ?. . . ብዙ 'ዴቨሎፕ' ማድረግ የምንችለው ነገር አለ። አፍሪካዊ ሰዎችን ማሳተፍ እንችላለን። ብላክ ኢን ኤአይ፣ ዳታ ሳይንስ አፍሪካ እና ሌሎችም ተቋሞች አፍሪካ ላይ ይሠራሉ። ሁላችንም የምናስበው ለአፍሪካ ጉዳይ መልሱ የሚመጣው ከአፍሪካዊ እንደሆነ ነው። ከውጪ አይመጣም። መድልዎን ማቆም፣ አፍሪካን መጠበቅ እንችላለን። ትምህርቱን አስፍተን፤ ተሰጥኦው እንዲወጣና በዓለም እንዲታይ ማድረግ አለብን።

የፎቶው ባለመብት, Rediet Abebe

የምስሉ መግለጫ,

ረድኤት አበበ

የነገርሽኝ "ዩዚንግ ሰርች ክዌሪስ ቱ አንደርስታንግ ኸልዝ ኢንፎርሜሽን ኒድስ ኢን አፍሪካ" የተሰኘው ጥናት ሲሠራ ናሙና ከተወሰደባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ፤ በጤና ዘርፍ ከመረጃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያገኛችሁት ክፍተት ምንድን ነው? እንደ ምክረ ሀሳብ ያቀረባችሁትስ?

በኢትዮጵያ ምን አይተናል መሰለሽ. . . ሰዎች ነጭ ሽንኩርት፣ ማር ወይም ሎሚ ከኤችአይቪ ይፈውሳል? ከተጸለየልኝ ኤችአይቪ ይጠፋል? እነዚህ አይነት ጥያቄዎች ሲጠየቁ 'ዌብሳይት' ላይ "አዎ፤ ነጭ ሽንኩርት ኤችአይቪን ያጠፋል" ተብሎ ይጻፋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ሊያስብብበት ይገባል።

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች [በአፍሪካ] እንደዛ ነው። ሌላው ጥያቄ ስለ መገለል ነው። ኤችአይቪ በደሜ በመኖሩ ከሥራ ልባረር እችላለሁ? ሰው ያገለኛል? ብለው ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያ እያለሁ ሰዎች እንዳይገለሉ [አስተማሪ] ድራማ ይታይ ነበር። በጤና ጥበቃ [መረጃ የሚሰጡ] ንቅናቄዎች በጣም ይረዳሉ። ኢትዮጵያ ግን ብዙ ይቀራታል። ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ።