ከኢትዮጵያ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እስከ አውስትራሊያ ሰደድ እሳት

በሕንድ ውቅያኖስ የዲፖሌ ክስተት ባለፉት 60 ዓመታት ከታየው ከፍ ያለ መሆኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በሕንድ ውቅያኖስ የዲፖሌ ክስተት ባለፉት 60 ዓመታት ከታየው ከፍ ያለ መሆኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ

በምስራቅ አፍሪካ ቆፈናም ማለዳ፣ አልቃሻ ተሲያት፣ ጨፍጋጋ ምሽት የሰሞኑ ክስተቶች ናቸው። በኢትዮጵያም ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ሰብሎችን ለመታደግ እዚህም እዚያም ርብርብ ተደረገ ሲባል እንሰማለን።

የምስራቅ አፍሪካ ሰማይ ዝናብ አርግዟል፤ ያለማቋረጥ ይዘንባል። በዚህም የተነሳ በሶማሊያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በደቡብ ሱዳን ከተሞች ሙሉ በሙሉ በውሃ ተውጠዋል።

የአየር ጸባይ ለውጥ ላይ የሚመክረው ስብሰባ ምን ይዞ ይሆን?

በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ታንዛኒያ እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ያለማቋረጥ የጣለ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የመሬት መንሸራተት ተከስቶ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 250 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ተመራማሪዎች ቀጠናው በዚህ ዓመት ከባድ ዝናብ አስተናግዷል ይላሉ። ይህም ሊሆን የቻለው በሚቲዎሮሎጂካል ክስተቶች መሆኑን በመናገርም ለዚህም ምክንያቱ የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ግን ይህ ሳይንቲስቶች ስም ጠቅሰው፣ ማስረጃ ነቅሰው ኢንዲያን ዲፖሌ ያሉት ነገር ምንድን ነው?

ሶስት ነገሮችን ከእነርሱ ማስረጃ ውስጥ መዝዘናል።

1.የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ ምንድን ነው?

የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ (IOD) ሚቲዮሮሎጂካዊ ክስተት ሲሆን ውቅያኖሱን በሚጎራበቱና በምድር ወገብ አቅራቢያ ባሉ ሀገራት የዝናብ ስልትን ይቀይራል። ይህም ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ኢንዶኔዢያ ድረስ የተለጠጠ ሲሆን የአየር ጠባዩ እስከ አውስትራሊያ ድረስ ርቆ ይስተዋላል።

አይ ኦዲ ፖዘቲቭ ሲሆን በሕንድ ውቅያኖስ በስተምዕራብ ያለ ውሃ ይሞቃል። ይህም ከምስራቅ አፍሪካ ራቅ ብሎ መሆኑ ነው፤ ይህ ከተለመደው በላይ የውቅያኖስ መሞቅ ከፍተኛ ትነት እንዲከሰትና ከባድ ዝናብ እንዲከሰት ሰበብ ይሆናል።

ለ12 ቀናት በሰዋራ ሥፍራ የቆዩት አውስትራሊያዊት በሕይወት ተገኙ

ይህ በእንዲህ አንዳለ በሕንድ ውቅያኖስ በስተምስራቅ ያለ ውሃ፣ ከጃቫ እና ሱማትራ ባህር ዳርቻ ራቅ ብሎ፣ ከተለመደው ጊዜ በተለየ ይቀዘቅዛል። ይህ ደግሞ በተቃራኒው ተጽዕኖ ይፈጥራል።

አንድሪው ተርነር በዩኬ በሚገኘው ሬዲንግ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ባለሙያ ናቸው፤ ለቢቢሲ ሲያስረዱ "ሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ ሲከሰት፣ የዝናብ መጠኑ ከውሃው መሞቅ ጋር ይሄዳል፤ ስለዚህ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከተለመደው ከፍ ያለ ዝናብ ያገኛሉ ማለት ነው"

" በሌላ በኩል ደግሞ በምስራቅ ህንድ ውቅያኖስ፣ የባህር ወለል የሙቀት መጠን ከተለመደው በላይ ቀዝቃዛ ስለሚሆን አካባቢው ከተለመደው ያነሰ የዝናብ መጠን ያገኛል" ብለዋል።

የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ከሚከሰተው ኤልኒኖ ጋር ተነጻጻሪ ነው፤ ለዚህም አንዳንዴ የሕንድ ኒኖ በመባል ይታወቃል፤ ነገር ግን አንደ ኤልኒኖ ተጽዕኖው የገዘፈ አይደለም።

2. የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ እ... በ2019 አየል ብሎ ታይቷል

Image copyright Getty Images

ካለፉት 60 ዓመታት በተለየ ሁኔታ ፖዘቲቭ አይኦዲ ጠንክሮ ታይቷል። ኔጋቲቭ የሆነው ሲመጣ ደግሞ ውሃው በምስራቃዊ አፍሪካ ዳርቻዎች ከተለመደው በላይ መቀዝቀዝ፣ በኢንዶኔዢያ አካባቢ ደግሞ መሞቅ ይጀምራል።

የኬኒያዋ ምዕራብ ፖኮት ግዛት በመሬት መንሸራተትና በጎርፍ ከተመታች በኋላ ለማገገም እየጣረች ትገኛለች።፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ጎርፍ ይዟቸው ሄዷል። በግዛቲቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ እንደሚሆን ተነግሯል።

“ኦዲፒ ዋጋ የተከፈለባቸውን ጥያቄዎች ወደ ጎን መተው አይገባውም” ፕ/ር መረራ ጉዲና

እንደ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል መረጃ ከሆነ በደቡብ ሱዳን ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት የመኖሪያ ቀያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ሲሆኑ፣ ይህ እጣ የ273 ሺህ ሶማሊያውያንም ነበር።

በሌላ በኩል አውስትራሊያ ደግሞ ለሌላ ድርቅ እና ሰደድ እሳት እየተዘጋጀች ነው። ይህም ሕዳር ጀምሮ እስከ የካቲት ይቀጥላል ተብሏል።

ነገር ግን ሞቃታማው አየር አስቀድሞ የሰደድ እሳት እንዲከሰት ያደረገ ሲሆን በዚህም የተነሳ 4 ሰዎች ሲሞቱ ከ500 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል።

የአውስትራሊያ የረዥም ጊዜ አየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያ የሆኑት አንድሪው ዋትኪንስ እንደሚሉት ከሆነ "በአሁን ሰአት ያለውና ተጠባቂው ሁኔታ የሚያሳየን እስካሁን ድረስ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጠንካራ የሆነ ፖዘቲቭ ዲፖሌ መመዝገቡን ነው"

ነገር ግን ይህ የአየር ጠባይ ድርቅ እያመጣ ይሆን ብላ በስጋት ከምትጨነቀው ህንድ ፊት ስጋቷን ገለል ያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በተወሰኑ ሀገሪቱ ክፍል በዚህ አየር ጠባይ ምክንያት የምታገኘው የዝናብ መጠን ከፍ ስለሚል ነው።

3. የዓለም ሙቀት መጨመር የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ ክስተቶችን ቶሎ ቶሎ ንዲመጡ ያደርጋል

Image copyright AFP

ዶ/ር ተርነር እንደሚሉት ከሆነ በአይኦዲ ምክንያት የሚከሰቱ ከባድ የአየር ንብረት ጠባይ ለውጦች የግሪን ሀውስ ልቀት በጨመረ ቁጥር በተደጋጋሚ የመከሰት ፍጥነታቸው እንደሚቀጥል ይናገራሉ።

" በህንድ ውቅያኖስ ምዕራብ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት አየር ጠባይ እንደሚመለከቱ፣ ጎርፍና ከባድ ዝናብ ደግሞ የተለመደ ይሆናል። ዝናቡ በሰብል ላይ ጥፋት ያደርሳል፤ ጎርፉ መሰረተ ልማት ያወድማል" ይላሉ።

መሬት መንሸራተትና ጎርፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ጥፋት አደረሰ

" በሌላ በኩል ደግሞ በምስራቅ ህንድ ውቅያኖስ የሚገኙት ሀገራት፣ በኢንዶኔዢያ ምዕራብ የሚገኙ ደሴቶች የዝናብ መጠን በመቀነሱ ምክንያት ድርቅ ሊመዘገብባቸው ይችላል።"

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ