ስድስት መሠረታዊ ጥያቄዎች በጣና እምቦጭ ዙሪያ

አንድም በዓይን የሚታይ አረም ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንዳይተላለፍ እናደርጋለን- ዶ/ር አያሌው ወንዴ የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ
የምስሉ መግለጫ,

"አንድም በዓይን የሚታይ አረም ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንዳይተላለፍ እናደርጋለን" ዶ/ር አያሌው ወንዴ

ስለእምቦጭ አረምና ጣና ሐይቅ ከሚሰጡ ምላሾች ይልቅ የሚነሱት ጥያቄዎች ይበልጣሉ። አረሙን ለመከላከል እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች የሚጠበቀውን ውጤት እያስገኙ አይደለም። ከጥረቱ በተቃራኒ አረሙ በከፍተኛ ፍጥነት ጣና ሐይቅን ብቻ ሳይሆን አባይንም እያጠቃ ነው። ይህንን ከግምት በማስገባት የአማራ ክልል የጣና እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲን በቅርቡ አቋቁሟል። በጉዳዩ ላይ ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች እንደሚከተለው ተዳስሰዋል።

ምን ያህል ጉዳት አደረሰ?

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ በብዙሃን መገናኛ እና ማህበራዊ ድር አምባው መወያያ ርዕስ ሆነው ከዘለቁት ጉዳዮች መካከል አንዱ በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተው እምቦጭ ነው። ኑሯቸውን በሐይቁ ላይ የመሠረቱት ግን ነጋ ጠባ የሚያስቡት ስለሐይቁ እና ስለ ሐይቁ ብቻ ነው።

አረሙ ጣና ሐይቅ ላይ ከመታየቱ በፊት በ2004 ዓ.ም መገጭ በሚባል ወንዝ ላይ ቀድሞ መከሰቱን የሚናገሩት ዶ/ር አያሌው ወንዴ የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እንዴት እንደተከሰተ "ግምት" ከማስቀመጥ ውጭ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የለም ይላሉ።

"ሐይቁ በዓሳ፣ በሩዝ እና በመኖ ምርታማ የሚባለው አካባቢ ነው በአረሙ ተያዘው" ይላሉ።

አረሙ ከመስፋፋቱም ጋር ተያይዞ ጀልባዎች እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ከመሆን ባለፈ የዓሳ ምርቱም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ የከፋው ግን በአካባቢው አርሶ አደሮች እና ብዝሃ-ህይወቱ ላይ የሚያደርሰው ችግር ነው። ለእርሻ ይውል የነበረውን ቦታ ከመሸፈን ጀምሮ፤ እንስሳት ሲበሉት ጤናቸው ከመታወኩም በላይ ወተት እና ስጋቸው ያለውን ጣዕም ያጣል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ይገልጻሉ።

ከ20 በላይ ገዳማትን የያዘው ጣና ሐይቅ ከሐይማኖታዊ ሃብቱ በተጨማሪ የቱሪስቶች መዳረሻም ጭምር ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የቢቢሲ ባልደረቦች ከገዳማቱ አንዱ በሆነው እንጦስ ኢየሱስ ገዳም በተገኙበት ወቅት እማሆይ ወለተማርያምን አግኝተው አናግረው ነበር። "ጣና የገዳሙ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱም ሃብት ነው" የሚሉት እማሆይ ወለተማርያም አረሙ ገዳሙ አካባቢ አለ መባሉ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። "አረሙ ሐይቁን ሊያደርቅብን ይችላል የሚል ስጋት አድሮብናል" ይላሉ።

በሐይቁ ዙሪያ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም የሌሎች መጤ አረሞች መስፋፋትም ችግሩን አባብሰውታል።

እምቦጭ ምን ያህል እየተስፋፋ ነው?

ከሁለት ሺህ እስከ 50 ሺህ ሔክታር ድረስ የሚሆነው የሐይቁ ክፍል በእምቦጭ ተይዟል የሚሉ መረጃዎች በተለያየ ጊዜ ይወጣሉ። ሐይቁ ላይ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የእምቦጭ አረም በፍጥነት እየተሰራጨ ይገኛል።

ከ60 በላይ ቀበሌዎች በሐይቁ ላይ ተመርኩዘው ህይወታቸውን ይመራሉ። እንደ ዶ/ር አያሌው ከሆነ "እምቦጭ 27 ቀበሌዎችን አዳርሷል -ገልዳ ወንዝ ከሚባለው ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ እስከ ደልጊ ድረስ።"

"ጉዳቱ እየደረሰበት ያለው በዳርቻው አካባቢ ነው። የሐይቁ አጠቃላይ ዙሪያ ብንወስድ 385 ኪሎ ሜትር ነው። ከዚህ ውስጥ በየጊዜው በመስፋፋት እምቦጩ 27 ቀበሌ ደርሷል። ይህም ወደ 190 ኪሎ ሜትር የሐይቁ ዳርቻ ማለት ነው። ይኼውም በብዛት በመካካለኛ እና በአነስተኛ ሁኔታ የተያዘ ነው።"

"በሳይንሱ የሐይቅ ዳርቻ ተጎዳ ማለት ዋናው ትንፋሹ ተጎዳ ማለት ነው። ውሃ ብቻ ነው ያለው ማለት ነው። ውሃ ደግሞ ነገ ይደርቃል" ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Kalkidan

የምስሉ መግለጫ,

ከሁለት ሺህ እስከ 50 ሺህ ሔክታር ድረስ የሚሆነው የሐይቁ ክፍል በእምቦጭ ተይዟል

የአየር ንብረት ለውጥ እና በእምቦጭ አረም ላይ ያለው ዕውቀት አነስተኛ መሆኑ ከእምቦጭ በተጨማሪ ሌሎች አረሞች እንዲስፋፉ በር ከፍቷል።

እምቦጭ ብቻ ነው ጣናን የሚያሰጋው?

የእምቦጭ ጉዳይ መፍትሔ ሳይሰጠው ሌሎች መጤ አረሞችም ጣና ሐይቅ ላይ ስጋት ደቅነዋል።

ዶ/ር አያሌው ብዙም ያልተወራላቸው እንደአዞላ እና ኢፖማ ዓይነት አረሞች መከሰታቸው ሌላ የስጋት ምንጭ ሆኖባቸዋል።

"እምቦጭ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አረሞችም ስጋት ፈጥረዋል። ለምሳሌ ለአፈር እና ለውሃ ጥበቃ ተብሎ የተተከሉ መጤ ዝርያዎች አሉ። የሁሉም የወንዞች መግቢያ በእነሱ ተሸፍኗል። ጣና ላይ ዋናው አረም እምቦጭ ቢሆንም ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉ።

"የአረም ብቻ ሳይሆን የብክለት ችግርም አለ። የባህር ዳር እና የጎንደር ከተማ ቆሻሻ ወደ ሐይቁ ይገባል። ይሄን ተሸክሞ አረሞቹን መዋጋት ተረት ይሆናል" ይላሉ።

ሐይቁ የደለል ስጋትም ተጋርጦበታል። በዚህ ምክንያት ሐይቁ ጥልቀት ከፍተኛ ፍጥነት መቀነሱ ይገለጻል።

የችግሮቹ መደራረብ እና አረሙ የጋረጠው ስጋት ለጣና ሐይቅ መፍትሔ ማበጀት ጊዜ የሚሰጠው እንዳይሆን አድርጎታል።

የምስሉ መግለጫ,

"በጥንዚዛዎች እምቦጭን ማጥፋት የብዙ ሃገር ተሞክሮ ነው"

ምን አማራጭ ማጥፊያ ዘዴዎች አሉ?

ችግሩን ለመቅረፍ የሠው ወይም የማሽን ጉልበት፣ ኬሚካል ወይንም ደግሞ እምቦጭን ሊያጠፉ የሚችሉ ሌሎች እጽዋትን መጠቀም የተለመዱ ዘዴዎች ናቸው። የተለያዩ ሃገራት ዘዴዎቹን ለየብቻ ወይንም በጋራ እንደችግሩ ሁኔታ ይጠቀሙባቸዋል።

ዘዴዎቹን በመጠቀም ለመከላከል በተለያዩ ግለሰቦች እና በተቋማት ደረጃ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው በነበሩ በጢንዚዛዎች እምቦጭን ማጥፋት የብዙ ሃገር ተሞክሮ ነው ይላሉ።

"ጢንዚዛዎቹ እምቦጭን ብቻ ነው የሚመገቡት። ሥራ የጀመርነው ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ነው። ቪክቶሪያ ሃይቅ ላይ ውጤታማ ሆኗል። ሌሎችም የአፍሪካ ሃገሮች ላይ ውጤታማ ናቸው። ምንም የጎንዮሽ ጉዳት የማያደርሱ ምንም አይነት ወጪም የማይጠይቁ ናቸው" ይላሉ።

አቶ ሙላት ባሳዝነው የሙላት ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ ድርጅታቸው ማጨድ እና አረሙን ማጓጓዝ የሚችል ማሽን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሠርቷል። "እምቦጭ መጣ ሲባል ያለንን ለማዋጣት ተነስተን የራሳችንን ሞዴል ሠርተናል። እምቦጩን የማስወገድ አቅሙ ካቀድነው በላይ ነው። ከውጭ ከመጣው የተሻለ ውጤታማ ማሽን ሠርተናል" ሲሉ ስለማሽናቸው ይገልጻሉ።

"በምርምር እምቦጭን በ24 ሰዓት የሚያደርቅ" ፈሳሽ ማዘጋጀታቸውን የሚናገሩት መሪ ጌታ በላይ አዳሙ የመድሃኒት እና ሽቶ ዕጽዋት ላይ ተማራማሪ ናቸው። "የኔ ምርምር ፈሳሽ ነው። እምቦጩ ላይ ይረጫል። አረሙ በ24 ሰዓት ይደርቃል። ተፈጥሮአዊ በመሆኑ በሃይቁ ብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት አያመጣም" ይላሉ።

ሌሎችም እምቦጭን ለማጥፋት የሚረዳ ዘዴ እንዳላቸው ወይንም እምቦጭን ተጠቅመው ጠቃሚ ምርት ለመሥራት የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ይህ ሁሉ ሆኖም ግን አረሙን ማጥፋት አልተቻለም።

አረሙን ለምን ማጥፋት አልተቻለም?

ህብረተሰቡ በጉልበት እና በገንዘብ የሚያደርገው ድጋፍ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ አረሙን በጉልበትም ሆነ በማሽኖች እንዲጠፋ እገዛ አድርጓል።

"አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት ቢሠሩም፤ ስልታችን የተጠና አለመሆኑ የልፋታቸውን ዋጋ አላገኙም" ይላሉ ዶር አያሌው።

አረሙ በንፋስ አማካይነት መንቀሳቀሱ እና በከፍተኛ ፍጥነት መዛመቱ፤ ከውጭ የመጡት ማሽኖች በየጊዜው መበላሸት እና ሐይቁ ጥልቀት በሌለው ቦታ አለመሥራታቸው ሥራውን ከባድ አድርጎታል። [አብዛኛው የእምቦጭ አረም ሐይቁ ጥልቀት በሌለው ቦታ ላይ ነው ያለው።]

ጢንዚዛዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት ቢጠናቀቅም የሚያስፈልገው የውሃ ገንዳ በፍጥነት አለመገንባቱ ሥራውን አጓቶታል። ፈሳሹን መከላከያን ወደ ሥራ ለማስገባት ያለው የጎንዮሽ ጉዳት አለመጠናቱ እና በሃገር ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ፈሶበት የተሠራውን ማሽን የአካባቢ ባለስልጣን ተረክቦ ሥራ አለማስጀመሩ መፍትሔውን አርቀውታል።

"በማሽን ብቻ ለማጥፋት የመሬት አቀማመጡ አስቸጋሪ ነው። የውጭ ማሽኖች ለመሥራት አንድ ሜትር [ጥልቀት ያለው] አካባቢ ይፈልጋሉ። የእኛ ለመሥራት 30 ሴንቲሜትር ጥልቀት ያለው ውሃ ይፈልጋል። ሆኖም አረሙ አነስተኛ ጥልቀት ያለው ቦታ ላይ በመሆኑ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል" ይላሉ አቶ ሙላት።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ዶ/ር አያሌው "አጥንተን ለተለያዩ ዘዴዎች የሚስማሙትን ቦታዎች መርጠናል። በማሽን እና በሰው መታረም በማይችል ቦታ ላይ ባዮሎጂካል [እምቦጭን የሚያጠፉ ተፈጥሮአዊ መንገዶች] ዘዴ መፍትሔ ነው። አንድ የሚባል መፍትሔ የለም። በጢንዚዛ ብቻ አጠፋን የሚባል የውጭ ተሞክሮ የለም። የተለያዩ ዘዴዎችን በጋራ መጠቀም አለብን" ብለዋል።

ምን ቢሠራ በቁጥጥር ስር ይውላል?

ትኩረቱን እምቦጭ እና ሌሎች መጤ አረሞች ላይ ያደረገው የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ በቅርቡ ተቋቁሞ የ5 ዓመት የሥራ ዕቅድ ተነድፎ ተግበራዊ ሆኗል።

የመጀመሪያው ሥራው በዓይን ሊታይ የሚችለውን አረም ማስወገድ ነው። "በሰው ሃይልም ሆነ በተለያየ መንገድ በዓይን ሊታይ የሚችለውን አረሙን ማስወገድ ነው" ብለዋል ዶ/ር አያሌው።

በዕቅዱ መሠረት ሙሉ በሙሉ በዓይን የሚታይ አረም እንዳይኖር ይደረጋል። ይህ ደግሞ እስከ ሰኔ 30/2012 የሚሠራ ይሆናል።

የምስሉ መግለጫ,

"የኔ ምርምር ፈሳሽ ነው። እምቦጩ ላይ ይረጫል። አረሙ በ24 ሰዓት ይደርቃል። ተፈጥሯዊ በመሆኑ በሃይቁ ብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት አያመጣም"

ይህንን ለማከናወን ደግሞ ሁሉንም የመከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ ለማድረግ ታስቧል።

ከውጭ ከመጡት አንጻር የተሻለ ማሽን መሥራታቸውን የሚናገሩት አቶ ሙላት፤ ከወጪ ውጤታማነት እና ፍጥነት አንጻር የሠሯቸው ማሽኖች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፍላጎት አላቸው።

በተመሳሳይ "ዛሬ ለጢንዚዛዎቹ የሚያስፈልገው ገንዳ ከተሠራ ዛሬውኑ ወደ ሥራ እንገባለን" ሲሉ ዝግጁ መሆናቸውን ዶ/ር ጌታቸው ያስረዳሉ።

"ሁሉንም አማራጮች እንጠቀማለን። ቅንጅታዊ ሆኖ በቅደም ተከተል እንሠራለን። በቀዳሚነት በማሽንና በሰው ሃይል ይከናወናል" ብለዋል ዶ/ር አያሌው።

ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት አረሙን ለማጥፋት ከህብረተሰቡ የተሰበሰበ ገንዘብን በመጠቀም ማሽኖች እና የሰው ጉልበትን በማቀናጀት ይከናወናል።

"በኤጀንሲው አስተባባሪነት አረሙ በተከሰተባቸው 4 ዞኖች 8 ወረዳዎች ከህዳር 1/2012 'እኔ ለጣና' በሚል መሪ መልዕክት ለ45 ቀናት ዘመቻ እየተካሄደ ነው። ሥነ ህይወታዊ እና ኬሚካላዊ አረሙን የማጥፊያ ዘዴዎች በጥናት ላይ ናቸው። አሁን በሰው ጉልበት እና በአራት ማሽኖች ነው የሚሠራው" ያሉት የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው ናቸው።

"50 ሚሊዮን ብር [ከህብረተሰቡ ተሰብስቦ ሥራ ላይ ከዋለው የቀረ እና በጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ የሚገኝ የገንዘብ መጠን] አውጥተን በዓይን የሚታይ ምንም አረም እስከማይኖር ድረስ እናስወግዳለን፤ የማገገም ሥራ እንሠራለን።"

"ፍሬው 20 ዓመት ሊቆይ ሲችል ጣና ግን የተመቸ ስለሆነ በፍጥነት ሊበቅል ይችላል። አንድም በዓይን የሚታይ አረም ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንዳይተላለፍ እናደርጋለን" የሚሉት ዶ/ር አያሌው ሃሳባቸውን የሚያጠናቅቁት "ውሃ እና ወንዞች ላይ ተደብቆ የሚከርም [አረም] መኖር የለበትም። 100 በመቶ ካልተወገደ ባይሠራ ይሻላል" በማለት ነው።