የአብዲሳ አጋ ጀብዱ በሥዕል መጽሐፍ

ከመጽሐፉ የተወሰደ Image copyright MINAS HALEFOM

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ሚናስ ኃለፎም ካህሳይ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ በታክሲ ሲሄድ አንዳች አስደናቂ ታሪክ በራድዮ ይሰማል። ስለ አብዲሳ አጋ የጀግንነት ታሪክ።

ተራኪው አብዲሳ ጣልያን ሳሉ የሠሩትን ጀብዱ ያወሳል። ይህ ታሪክ ለሚናስ አዲስ እንደነበረ ይናገራል።

የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ በአማርኛ መጽሐፍ ላይ ስለ አብዲሳ አጋ አንብቧል፤ ተምሯል። በራድዮ የሰማው ታሪክ ግን ዝርዝር መረጃ የያዘ ነበር።

"አማርኛ መጽሐፍ ላይ አብዲሳ ከጣልያን እሥር ቤት በመስኮት ከማምለጣቸው ያለፈ መረጃ አልነበረም።"

ለኢትዮጵያዊያን የንባብ ወዳጆች ምርጡ መጽሐፍ የትኛው ነው?

ኮሎኔል መንግሥቱን ትግል ለመግጠም ቤተ መንግሥት የሄደው ደራሲ

ማንችስተር ዐይኑን የጣለባቸው የአቶ ምሥጢረ ኃይለሥላሴ ልጆች

የራድዮው ትረካ፤ አብዲሳ ከእሥር ቤት አምልጠው የራሳቸውን ጦር መልምለው፣ እሥር ቤቱን ሰብረው ገብተው፣ እሥረኞችን ካስመለጡ በኋላ ፋሺስቶችን እና ናዚዎችን መዋጋታቸውን ይዳስሳል።

"ይሄን ታሪክ ጭራሽ አላውቀውም ነበር። ስሰማው በጣም ተመሰጥኩ፤ ታሪኩ ልብ ወለድ ፊልም ነው የሚመስለው፤ ከሰማሁ በኋላ ጥናት ማድረግ ጀመርኩ።"

ሚናስ ጥናቱን ጨርሶ፣ የአብዲሳን የጣልያን የተጋድሎ ታሪክ ወደ መጽሐፍ ለውጦታል። "አጋ" የተሰኘው በሥዕል የተደገፈው ይህ መጽሐፍ (ግራፊክ ኖቭል) የተመረቀው ባለፈው ሳምንት ነበር።

መጽሐፉ መነሻ ያደረገው አብዲሳ ጣልያን ውስጥ ሲዋጉ ይመዘግቡት የነበረውን የዕለት ውሎ ማስታወሻ (ዳያሪ) እንደሆነ ሚናስ ይናገራል።

መጽሐፉ በብዛት ገበያ ላይ ስለሌለ ከአሮጌ ተራ በውድ እንደገዛው ያስታውሳል። ይህ ብዙዎች ስለ አብዲሳ ጥልቅ መረጃ እንዲያገኙ የረዳው መጽሐፍ የ "አጋ" መነሻም ሆነ።

Image copyright MINAS HALEFOM

"የአብዲሳን ታሪክ ወደ ኮሚክ ሥዕሎች ቀይሬ ነው የሠራሁት፤ ታሪኩ ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ከወረረችበት ጊዜ ኢትዮጵያ ነፃ እስክትወጣ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል" ሲል ያስረዳል።

በአብዲሳ የሕይወት ታሪክ እጅግ የሚገረመው ሚናስ፤ ለመጽሐፉ የሚያስፈልገውን ጥናት ካጠናቀቀ በኋላ በስድስት ወር ውስጥ ሥዕሉንና ጽሑፉን ቢጨርስም ስፖንሰር ለማግኘት ስለተቸገረ መጽሐፉን ቶሎ ማሳተም አልቻለም ነበር።

መጽሐፉ በኢትዮጵያ የሰርቢያ ኢምባሲ ድጋፍ መታተሙን ጠቅሶም፤ በቀጣይም የሚደግፈው ካገኘ መጽሐፉን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የማሳተም እቅድ እንዳለው ገልጿል።

ሚናስ እንደሚለው፤ የአብዲሳን የጀብዱ ታሪክ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ሌሎችም እንዲረዱት በማሰብ "አጋ"ን በ500 ቅጂ በእንግሊዘኛ ጽፎ አሳትሞታል። "የኢትዮጵያን ታሪክ ባህር እንደማሻገር አስበዋለሁ" ሲልም ይገልጻል።

"አብዲሳ አጋ ብዙ ሊደረጉ የማይችሉ የጀግንነት ተግባሮች ፈጽመዋል፤ ሰው ከጠላት አገር እሥር ቤት አምልጦ ሊያስብ የሚችለው የራሱን ሕይወት ስለማዳን ነው። አብዲሳ ይህን አላደረጉም። ወደ እሥር ቤቱ ተመልሰው ዩጎዝላቪያን ጨምሮ ጣልያን ስትወራቸው የነበሩ አገሮችን ታሣሪዎች አስፈትተው ተዋጉ" ሲል የሚያስደንቀውን የአብዲሳ ጀብዱ ያስረዳል።

Image copyright MINAS HALEFOM

የኢትዮጵያውን ጀግኖች ታሪክ በስፋት በታዳጊዎችና በወጣቱ ትውልድ ዘንድ አለመታወቁን ሚናስ ይገልጻል።

"ዓላማዬ ታዳጊዎችና ወጣቶች ታሪካቸውን እንዲያውቁና የኢትዮጵያም ታሪክ ድንበር ተሻግሮ በመላው ዓለም እንዲሰራጭ ማድረግ ነው" ሲልም ግቡን ያስረዳል።

ተያያዥ ርዕሶች